1000021475

በብልፅግና አስገዳጅ ህግ፣ በወባ ወረርሽኝ ሞት እንዲሁም በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዎህዴግ በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል።

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግምባር የሥራ አስፈፃሚ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በሦሥት የተለያዩ አንኳር ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በላከው መግለጫ ተገልጿል።

ዎህዴግ በመግለጫው “በዎላይታ ውስጥ በሁሉም ወረዳዎች የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈና የበርካቶች ህይወት እንዲናጋ ምክንያት መሆኑን እንዳሳሰበው የዎህዴግ የሥራ አስፈፃሚ ገልጾ መንግስት የሚከተለው የጤና ፖሊሲ የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ እንኳን የሚያስችል አቅም የሌለው መሆኑ ማሳያ ነው” ብለዋል።

“በተጨማሪም መንግስት የጤና ባለሙያ ደመወዝና ጥቅማጥቅም በጊዜ ባለመክፈሉ፣ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢዎችና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፊታሎች ምንም ዓይነት መድኃኒት ባለመኖራቸው ምክንያት በወባ የተያዙ ሰዎች መዳን እየቻሉ በመድኃኒት እጥረት እየሞቱ መሆኑ እጅግ በጣም ያሳዝናል ያሳፍራልም። ስለሆነም መንግስት በአስቸኳይ የህዝባችን ሕይወት እንዲታደግ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ከዚህ ውጭ በህዝባችን ላይ በሚደርሰው አደጋ መንግስት ራሱ ተጠያቂ መሆኑን ዎህዴግ ያስገነዝባል” ስል ገልጸዋል።

“ትምህርት ለአንድ ሀገርና አከባቢ እድገት ወሳኝ ሲሆን በአግባቡ ካልተያዘ ለውድቀትም መነሻ በመሆን የሚያገለግል መሳሪያ መሆኑ ይታወቃል ይሁንና ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በዎላይታና አከባቢው የተማረ ኃይል እንዳይፈጠር ታቅዶ የሚሰራ በሚመስል መልኩ የትምህርት ሥራ ከመውደቁም በላይ የ2017 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ በከተሞች ከሚገኙ ከግል ትምህርት ቤቶች ውጭ እስካሁን አለመጀመሩ እጅግ የሚያስደነግጥና የሚዘገንን ተግባር ከመሆኑም ባሻገር ዎላይታ ከዚህ በፊት የሚታወቀው “ትምህርት ለልጄ” ፕሮጀክት ከሽፎ ትውልድ እየጠፋ መሆኑ እና በትውልድ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑ ታውቆ በአስቸኳይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ ዎህዴግ በጽኑ ያሳስባል” በማለትም አስጠንቅቀዋል።

“ለብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ግንባታ ተብሎ ዎላይታ 350 ሚሊዮን ብር እንዲያዋጣ ግዴታ ተጥሎብናል ያሉ የዎላይታ ዞን አመራርና የወረዳ አመራሮች በእያንዳንዱ አርሶ አደር ላይ 1200 ብር እንዲከፍል አስገዳጅ ህግ በማውጣት ብሎም ትዕዛዝ ተቀብሎ የማይሰጠውን ግለሰብ እስከማሰር የደረሱበት መንገድ ፓርቲው ከአባላቱ ሰብስበው መገንባት የሚገባውን ህንፃ በመላው ዎላይታ ላይ እንደ ሜዶንና ፋሪስ ህግ ጭኖ አርሶ አደሮቻችንን በቁጣ አለንጋ መግረፍ ከሞራልም ከሰብዓዊነትም ያፈነገጠ ተግባር በመሆኑ በአስቸኳይ ቆሞ ፓርቲው ከአባላቶቹ ብቻ ድጋፍ እንዲሰበስብ እንዲደረግ ዎህዴግ በጥብቅ ያሳውቃል” ስልም ዎህዴግ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በላከው መረጃ ገልጸዋል።

“በመጨረሻም ከላይ የተጠቀሱ ጉዳዮች ለነገ የማይባሉ እና ህዝባችንን ለከፋ አደጋ የሚዳርጉ አደገኛ ድርጊቶች በመሆኑ መንግስትና የሚመለከተው አካል ወቅቱን የጠበቀ የእርምት እርምጃ ወስዶ ሕዝባችንን እንዲታደግ እየጠየቅን በአንጻሩ ህዝቡም ለመብቱ መከበር ከራሱ የሚጠበቅበትን ሰላማዊ ትግል እንድያደርግ ዎህዴግ ያሳስባል” አስረድተዋል።