1000021588

ፋኖ ዉስጥ “የጦና ብርጌድ ተቋቁሟል” ተብሎ በቀጥታ በአማራ ታጣቂዎች ጉዳይ ዎላይታ ብቸኛ ግብረ አበር ተደርጎ ተጠቅሷል ይሄን እንዴት ያዩታል? የአማራ ሕዝብ ከዎላይታ ወንድሞቹ ጋር የሚጋራቸዉ ጥያቄዎች የሉትም? በጦርነቱ ምክንያት መሄድ ያልቻሉ በዎላይታ አስፈላጊ ድጋፍ ተደርጎላቸው ስለሚገኙት የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ምን ይላሉ? እንደወትሮው ሁሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ለተነሱ ለዚሁ እና ለተያያዥ ጉዳዮች ምላሽ አላቸው፥ ዘገባውም ቀጥታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ዛሬ ባለፈዉ የአማራ ክልሉን ግጭት አስመልክቶ ካደረግነዉ ቃለ ምልልስ በሁዋላ ከሚዲያችን ተከታዮች የተወሰኑ ተጨማሪ ጥያቄዎች ተነስተዋል፥ እነሱን ይዘን ቀርበናል።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ደስ ይለኛል የሚዲያውን ተከታዮች ማሳተፍ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ፋኖ ወደ ታጠቀ አመጽ እንዲሸጋገር ያደረጉ ዉለዉ ያደሩ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሉም ወይ ? በርግጥ በሰላማዊ መንገድ ተደራድሮ መቀየር የሚቻል ነገር ቢኖር ፋኖ ጦርነትን ይመርጣል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የእኔ መከራከሪያ የሕዝብ ጥያቄ የለም አይደለም። ጦርነት ችግሮችን እያባባሰ ይሄዳል ነው። መፍትሔም አያመጣም፥ በተለይ ደግሞ የእርስ በርስ ጦርነት ሲደረግ በስሜት ብዙዎች የሚገቡበት ሲጠናቀቅ የሚጸጸቱበት ነው። ሌላዉ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ አንስቶ ማስመለስ አይቻልም ለሚለዉ ያም ካልሆነ እኔ ሰላማዊ ትግል ይሻላል ባይ ነኝ።

ሌላዉ ደግሞ በተለይ ከሕገመንግስቱ ማዕቀፍ የሚወጡ ጥያቄዎች በፈደራል መንግሥትም ሆነ በፋኖ ብቻ ሊመለሱ አይችሉም፤ ሁለቱ ቢስማሙ እንኳን የሚቻልበት አግባብ የለም በሐገሪቷ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መሳተፍ አለባቸዉ ነው።

ጦርነት ደግሞ ወደ መፍትሄው እያቀረበን ሳይሆን እያራቀን ይሄዳል ነው። የፈደራል መንግስት የሐገሪቷን ሕገመንግሥት አክብሮ አይንቀሳቀስም ብለዉ ያኮረፉ ኃይሎች በብዛት ባሉበት ፋኖ ሕገመንግሥታዊ ሥርአቱን በሚያጠፋ መንገድ የሚንቀሳቀስ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ለሁሉም ደግሞ ከጦርነት በሰላማዊ ድርድር ችግሮችን ለመፍታት መንቀሳቀሱ ይበጃል ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ፋኖ በአንድ ወጥ አደረጃጀት አለመታቀፉ የችግሩን እድሜ ያራዝማል ብለሃል። አንድነቱ ጥሩ ሆኖ ነገር ግን ለአንድ ወጥ አደረጃጀት የሰጠሄዉ ግምት አልበዛም?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ለምን መሰለህ ፋኖ አመራሮቹ ታዉቀዉ የሚያራምደዉ የትግል አላማ ታዉቆ ጥያቄዎቼ እነዚህ ናቸዉ ብሎ ዝርዝሩን ቢያስቀምጥ በጣም ጥሩ ነው። አሁን ባለዉ ግን የተለያዩ የፋኖ አመራሮች የሚያወሩት የተለያዬ ነገር ነው። አንዱ ሕገመንግሥት የሚያከብር ነገር ይናገራል፣ አንዱ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ማፍረስ አለብን ይላል፣ አንዱ ብሔረሰቦችን ወዳጆቼ ናቸዉ ይላል፣ አንዱ ይዝታል፣ አንዱ ስለአማራ እና አማራ ብቻ ያወራል፣ አንዱ ስለኢትዮጵያ ያወራል።

ይህ ዉዝግብ የሚያልቀዉ ፋኖ አንድ ሆኖ አላማዉን ግልጽ ሲያደርግ ነው። ሌላዉ መንግስትስ ከየትኛው ፋኖ ጋር ተደራድሮ፣ የትኛውን ይተዉ። ለፋኖምኮ የኃይል መበታተን ጥሩ አይደለም አንዳች ትልቅ ግብ አሳካለሁ ካለ ትልቅ አደረጃጀት ይጠይቃል።

እኛ ግን የምናበረታታዉ ጦርነትን ሳይሆን ድርድርን ነው። የአማራዉ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ጋር ወንድማማች ነው። የወንድማማች መገዳደል ሊቆም ይገባል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የአማራ ሕዝብ ከዎላይታ ወንድሞቹ ጋር የሚጋራቸዉ ጥያቄዎች የሉትም? እንደዉም ከዚህ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል ባለዉ ጦርነት ምክንያት ወደቤተሰቦቻቸዉ መሔድ ያልቻሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተማሪዮችን፣ ብሔረ ዎላይታዉ የዎላይታ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ እየተንከባከቡ የሚያስፈልጋቸዉን እያቀረቡ አቆይተዋል። በተለያዬ ቦታዎች የሚደረገዉ የብሔር ጥቃት በዎላይታ ታይቶ አይታወቅም። እንደዉ የአማራን ሕዝብና የዎላይታን ሕዝብ ወንድማማችነት እንዴት ይገልጹታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የአማራ ሕዝብና የዎላይታ ሕዝብ ወንድማማችነት ዘመናትን የተሻገረ ነው፥ ወደፊትም የሚቀጥል ነው። ሐገር እየተጋራን የሕዝብ ጥያቄ መጋራታችንን የሚጠበቅ ነው። በተለይ የአማራና የዎላይታን ሕዝብ የሚያመሳስላቸው ሁለቱም በመላዉ ኢትዮጵያ በስፋት ተሰራጭተዉ የሚኖሩ መሆናቸዉ አንዱ ነው። ከቅርብ አመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በሚደርሱ የብሔር ተኮር ጥቃቶች በጋራም በተናጠልም ሰለባ ሲሆኑ ታይቷል።

በተደጋጋሚ ስለዚህ ሁለቱም ሕዝቦች በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ ሐብት ንብረት የማፍራት ሕገመንግሥታዊ መብታቸዉ መከበሩ የጋራ ጥያቄያቸዉ ነው። በነገራችን ላይ ከራሳቸዉ ክልል እና ዞን ዉጪ በብዛት የሚኖሩ እንደ አማራ፣ ዎላይታ፣ ትግራይ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ኦሮሞ፣ ሐዲያ፣ ካምባታ እና የመሳሰሉት ስለነዚህ ወገኖቻቸዉ እጣ ፋንታ ተወያይተዉ የጋራ አቋም መያዝ አለባቸዉ።

የሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ተግባር በእዉነቱ ሐቀኛ የሐይማኖት አባትነት የታዬበትና የአማራንና የዎላይታን ዘላቂ ወንድማማችነት ያረጋገጠ እጅግ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። ስለ ጥቃት ያነሳሄዉ የዎላይታ ሕዝብ አብሮ በመኖር የሚያምንና ለዛም ከሱ የሚጠበቀዉን የሚወጣ ነው፤ ወንድማማች ሕዝብ በእዉነቱ መጠቃቃት የለበትም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በቅርቡ በመንግሥት ሚዲያዎች በተላለፈዉ ዶክመንተሪ ፋኖ ዉስጥ የጦና ብርጌድ ተቋቁሟል ተብሎ በቀጥታ በአማራ ታጣቂዎች ጉዳይ ዎላይታ ብቸኛ ግብረ አበር ተደርጎ ተጠቅሷል ይሄን እንዴት ያዩታል? እርስዎ ፋኖ በሌሎች ክልሎች ብዙ ደጋፊ የለዉም ብለዋልና።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በርግጥ መንግስት የሕወሓት ና ኦነግ_ሸኔ ግብረ አበር ሲለን ከርሞ አሁን ደግሞ የፋኖ ማለቱ በአገዛዙ ዎላይታ ተፈርጆ መቀጠሉን ያሳያል ባይ ነኝ። ብዙ ደጋፊ ፋኖ የለዉም ያልኩት ፋኖ አንድ ወጥ አደረጃጀት ፈጥሮ አቋሙን ግልጽ ባለማድረጉና የተለያዩ አመራሮች የማይናበብ ነገር ስለሚያወሩ ነው። ከዛ በተረፈ በፋኖ በኩል የጦና ብርጌድ የሚባል የዎላይታ ልጆች ያሉበት ጦር አለ ስለሚባለዉ እዉነቱን ፋኖ ያዉቃል እኔ አላዉቅም።

አንድ ግን አጽንኦት ሰጥቼ የምናገረዉ በኢትዮጵያዉያን መሐከል የሚደረግ ድርድር እንጂ ጦርነት አልደግፍም። የአማራ ሕዝብና የዎላይታ ሕዝብ ወንድማማችነት ግን ያለ እና ተጠናክሮ መቀጠልም ያለበት ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።

WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia #Wolaita #Tigray #Amhara #Oromia👇

ዘገበው በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የቀረበ ነው