1000022405

ፕሮፌሰሩ ስለ ኢቢሲ ምን አሉ?

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ Ethiopian broadcasting corporation በቅርቡ በዎላይታ ሶዶ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ቅርንጫፍ እየከፈተ ነው። Etv አፋን ኦሮሞም ሥራ ጀምሯል ይህን እንዴት ይመለከቱታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ጥሩ ነው። በሚዲያ መሰረተ ልማት ደረጃ ከዛ ዉጪ ግን ጣቢያዉ ፍጹም የካድሬነት ሥራ የሚሰራና ሐቀኛ የሕዝብ ድምጽ የማይደመጥበት መሆኑ ላይ የሚቀይረዉ ነገር ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እስቲ ሚዲያዉ በዎላይታ በድጋሚ በተደረገዉ ሕዝበ ዉሳኔ ዋዜማ ላይ የሠራዉን እና ተድበስብሶ ያለፈዉን ከባድ ወንጀል እናስታዉስ፥ በተጨማሪም ማን አደረገዉ ብለዉ እንደሚያምኑ ሐሳቦትን ቢያጋሩን?

✅ ፕሮፈሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ በጣም ደስ ይለኛል፥ ይህ በብሔሮችና ብሔረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን ሕገመንግስታዊ መብት ላይ የተፈጸመ አደገኛ ወንጀል ተረስቶ እንዳይቀር በማስታወስህ አመሰግናለሁ። በዎላይታ ዞን ድጋሚ ሕዝበ ዉሳኔ ሊካሄድ በዋዜማው ማታ የተሰራዉን ወንጀል ክብደት እና አዉድ ለመረዳት የሕዝበ ዉሳኔዉን ዳራ እንደሚከተለዉ አስቀምጣለሁ።

የዎላይታ ሕዝብ ክልል ጥያቄ ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑ ቢታወቅም ስለዛ ዝርዝር ጉዳይ ማንሳት የዛሬ ርዕስ ስላልሆነ እዘለዋለሁ። ብቻ ከለዉጡ በሁዋላ በሐገሪቱ ከብደዉ ከተነሱ የፖለቲካ ጥያቄዎች አንዱ የውላይታ ክልልነት ጥያቄ እንደሆነ ግልፅ ነው።

ይህን ጥያቄ ላለማስተናገድ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አንድ ዓመት ሙሉ ሥራ ሳይሰራ ደሞወዝ ከመብላቱ በተጨማሪ የፌደራሉ መንግሥት በዎላይታ ዞን ላይ መፈንቅለ መንግሥት እስከ ማድረግ መድረሱ እና ብዙ ንጹሐን ምትክ የለሽ ሕይወታቸውን ሲያጡ ብዙዎች አካላቸዉ እንደጎደለም ይታወሳል፣ ይህም የዚሁ ጥያቄ አፈና አካል ነው።

ከዛ ሁሉ በኃላ መንግሥት በጫና የደቡብ ኢትዮጵያን ክልል ለመመሥረት፣ እርግብ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን አደረጃጀት እደግፋለሁ፤ ጎጆ ደግሞ አልደግፍም በሚል ባካሄደዉ ሕዝበዉሳኔ የዎላይታ ዞን ድምጽ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝና ድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

በዚህ ሁሉ ሂደት እንግዲህ የዎላይታ ፓርቲዎች፣ ብዙ ሊህቃንና አክቲቪስቶች በሙሉ ከተወሰኑ የብልጽግና ካድሬዎች ዉጪ ለሕዝበ ዉሳኔዉ ሂደትም ሆነ ዉጤት እዉቅና እንደማይሰጡ አሳዉቀዉ፣ አባሎቻቸዉም ሕዝቡም እንዳይሳተፍ በመቀስቀሳቸዉ በጣም ብዙ ሰዉ እነሱን ሰምቶ በመጀመሪያዉ ሕዝበ ዉሳኔ አልተሳተፈም። ፓርቲዎቹም ለዎላይታ የክልልነት አማራጭ ካላካተተ እንደማይሳተፉ ገልጸዉ ቆይተዋል ።

ነገር ግን በሕዝበ ዉሳኔዉ ጎጆ ምንን ይወክላል የሚለዉ ጥያቄ ለሕዝቡ ምንን እንደሚወክል እንዲገለጽ ቢጠየቅም መልሥ የሰጠ የመንግሥት አካል አልነበረም። በዚህ መሐል የዎላይታ ሕዝበ ወሳኔ ድጋሚ ይካሄድ ብሎ ምርጫ ቦርድ በወሰነ እና ቀን ከቆረጠ በኃላ፣ በሕግ አግባብ ጎጆ በዉስጠ ታዋቂነት የዎላይታን ክልልነት ትወክላለች የሚል መከራከሪያ ማንሳት በተወሰኑ የዎላይታ ሊህቃን ዘንድ ተፈጠረ።

በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ሐሳቡ በመዛመቱ እና ብዙ አክቲቪስቶች በመጨመራቸዉ ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልል መሆን በእጃችሁ ነው ብለዉ እንደነበረም እያመሳከሩ የሚቀሰቅሱ ሰዎች ነበሩና እዉነትም ጎጆ መዉጫ መንገድ ነው የሚለዉ በብዙ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት አገኘ።

የዎላይታ ክልልነት ጥያቄ ታፍኗል ብለዉ አኩርፈዉ የነበሩ ብዙ ሰዎችም ወደ ጎጆ መሰባሰብ ጀመሩ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ተቃዉሟቸዉን ቢቀጥሉም የተወሰነ ደጋፊያቸዉ ካለመሳተፍ ወደ ጎጆ መራጭ ተቀላቀለ፣ ብዙ እርግብን በመጀመሪያዉ የመረጠ ሰዉ የጎጆ ቀስቃሽ ሆኖ ተገኘ። በሚገርም ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሰዉ ጎጆ ወደ ዎላይታ ክልል ለመድረስ ሰላማዊ የትግል መንገድ ነው ብሎ አምኖ ቀሰቀሰ።

በሚገርም ሁኔታ አትሳተፉ ከሚሉ ሊህቃንም የተወሰኑት በመጨረሻ የሕዝቡን ሁኔታ በማየት አቋዋማቸዉን በማሻሻል “አትሳተፉ! ከተሳተፋቹ ጎጆን ምረጡ !” ወደሚል ቀየሩ።
በጣም በሚገርም ሁኔታ በዋዜማው ጎጆ ያሸንፋል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያደፋፍር ሁኔታ ተፈጠረ በሕዝቡ ዘንድ።

በሕዝበ ዉሳኔዉ ዋዜማ ምሽት ሕዝቡ ጎጆ የዎላይታን ክልል ያስገኛል ብሎ በተዘጋጀበት አስደንጋጭ፣ ሕገወጥ፣ የብሄር ጭቆና መኖሩን ያስመሠከረ፣ ብሄሮችንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም ሕገመንግሥቱን የናቀ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንኳን ጎጆ ምንን እንደሚያመለክት ለመግለጽ ፈቃደኛ ባልነበሩበት፣ አቲቪ በምርጫዉ ቅድመ ዝግጅት ላይ የምርጫ አስፈጻሚ ቃለመጠይቅ አስታኮ ጎጆ የሚወክለዉ በቀድሞዉ ክልል መቀጠልን እንደሆነ የሚገልጽ ዘገባ በመዘገብ ለሕዝበ ዉሳኔዉ የተዘጋጀዉን ሕዝብ ተስፋ አስቆረጠ።

ይህ ከባድ ዱብዳ በኢቲቪ ከመዘገቡ በፊት ተስፋዉ ለምልሞ የነበረዉ ሕዝብ፤ ኩምሽሽ አለ። የሕዝበ ዉሳኔዉ ተቃዋሚ ዎላይታዎች ብለን ነበር ሲሉ የጎጆ ቀስቃሾች አንገታቸዉን ደፉ። ምርጫ ቦርድ ዘገባው የሕዝበ ዉሳኔዉ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብሎ ከኢቲቪ ገጽ ከተወሰነ ቆይታ በሁዋላ እንዲነሳ ቢያስደርግም ያመጣዉ ለዉጥ የለም። በወቅቱ በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረዉ ተስፋ መቁረጥ አስደንጋጭ ነበረ።

ይህን ያደረገዉ ማነዉ ? ያዉ scenarios የሚለዉ ቃል ወደፊት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን መላምት ማስቀመጫ ካልሆነ በፊልምና ድራሜ አልያም በስነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ተፈጽመዉ አድራጊያቸዉን መለየት ሳይቻል ሲቀር ደራሲዉ በምዕናቡ ሊያስብ የሚችላቸዉን ነገሮች ለመገመትም ጥቅም ላይ ይዉላል። እንግዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ድራማ ነውና የተወሰኑ senarios አስቀምጠን እንይ፦

  1. ኢቲቪ ዉስጥ የሚገኝ deep state ነው? deep state which acts as state with in state. ይህ ሊሆን እንደሚችል ለመጠራጠር በቂ ምክንያቶች አሉን። ለምሳሌ ያዉ የሐገራችን ተቋዋማት ፈደራል ሥርዓት እንከተል እንጂ አካታችነት በዞረበትም አያልፉምና አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ቋንቋቸዉ በዋናነት የአማርኛ ከመሆኑና በሌሎች ምክንያቶች የአሀዳዊነት ፖለቲካአራማጆች የተሞሉ መሆናቸዉ ይታወቃል። ለአሃዳዉያን ካምፕ ደግሞ የዎላይታ ኦቶኖሚ ማግነት የእግር እሳት ነው።

ሌላዉ ከዚህ በፊት ለምሳሌ “ንጉስ ጦና አድዋ አልዘመተም መሀል ሐገሩን ሲጠበቅ ነበር” ተብሎ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተዘግቦ ነበር፤ ሆኖም ከፍተኛ ተቃዉሞና ብዙ ጥያቄ በማስነሳቱ፣ በ2014 ዓ.ም ዘምቷል ብለዉ ወደ ዎላይታ ሶዶ መጥተው ሌላ ዘገባ ሰርተዋል። እንግዲህ ይህ በመንግሥት ተቋዋም በመሠግሠግ የሚሰራ ሸፍጥ ነው።

  1. ብልጽግና ፓርቲ መራሹን መንግሥትን ወይንም የአስፈጻሚዉ አካል ቁንጮዎችን ነው?

ለዚህ ጥርጣሬ የሚዳርገን አንድ ተራ ጋዜጠኛ ደፍሮ እንደዚህ አይነት ከባድ ወንጀል የሆነ ዘገባ ይሰራል ወይ? የጣቢያዉስ አሰራር ዘገባዉ ከመቅረቡ በፊት ዉድቅ ያላደረገዉ ለምንድነው?

የጋዜጠኛዉ ሆነ ጣቢያዉ ምንም አይነት ተጠያቂነት ባለመኖሩ፣ በነጻ መቀጠላቸዉም ይህን ጥርጣሬያችንን ያጎላል።

  1. በምርጫ ቦርድ እራሱ ?

በሁለቱም ሕዝበ ዉሳኔዎች ምርጫ ቦርድ ያፈጠጡና ያገጠጡ የብሄር ጭቆናዎችን ሲፈጽምና ሲያስፈጽም ከመቆየቱም ባሻገር የዎላይታን በጎ ገጽታ ለማጠልሸት ከፍተኛ አድሎዎችን ሲፈጽምና እና መሰረተ ቢስ ዉጀላዎችን ሲያሰራጭ ነበር። ለምሳሌ ሕዝበ ዉሳኔዉ ትርጉም የለሽ መሆኑን እያወቁ ማስፈጸም፣ ፈደሬሽን ምክር ቤትን መጠየቅ የሚችሉትን ጥያቄ መጠየቅ አለመፈለግ፣ ሕዝቡ ቋንቋዉን በሚችሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች እንዳይ ገለገል መከልከል፣ አለሥራቸዉ መታወቂያ ፈታሽ መሆንና የያዛችሁት ስድስት ወር ያልሞላዉ አዲስ መታወቂያ ነው በማለት እንዳይመርጡ መከልከል። ሌላዉ ቃለመጠይቅ የተደረገለት ግለሰብ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚ የሆነ መሆኑ ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 ስለአብሮነታችሁ እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia #Wolaita #Etv #Ebc

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተሰራ ዘገባ ነው