1000022522

የብልጽግና ከፍተኛ አመራር ስለ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የፖለቲካ ብልሽት ምን ይላሉ ?

አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ለህዝብ፣ ለመንግሥትና ለፓርቲ ህልውና ለማስጠበቅ በሚል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አጠቃላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተስተዋለ የሚገኘውን የፖለቲካ ብልሽት በተመለከተ ይፋ እንዲደረግ በዝርዝር መረጃዎችን አድርሰዋል። ለዝርዝር መረጃዎች አመራሩን በሚዲያችንና በተከታዮቻችን እያመሰገንን ቀጥታ ወደ ጉዳዩ እንግባ።

መረጃው “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ከማፍረስ አደጋ ማዳን ይቻል ይሆን?” እያለ ይጀመራል።

“የቀድሞ ደቡብ ክልል ከፈረሰ በኃላ የተደራጀው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እድሜው አንድ ዓመት ነው፡፡ በዚህ ክልል የሚኖረው ህዝብ በክልል አደረጃጀት ጥያቄ ምክንያት ላለፉት 5 ዓመታት ምንም አይነት የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ጥያቄዎች ሰሚ ጠፍቶ የቆየ ህዝብ ነው” ሲል ያስረዳል፡፡

እኚሁ ከፍተኛ አመራር “የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ከተመለሰ የእናንተ ጥያቄ ይመለሳል፤ ልማት ይሰራል ተብሎ በየአካባብዉ በይደር የቆዩ አጀንዳዎች ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ አዲስ የተደራጀው ክልል ጤናማ፣ ብቃትና ስነ ምግባር ባላቸው አመራሮች የተደራጀና የተመራ ቢሆን ኖሮ ክልሉ ለአገር የሚበቃ ድልብ አቅም ያለው ክልል ነበር” ይላል፡፡

“በሴራ ለእኩይ አላማ የተደራጁ ወንበዴና ስነ ምግባር የጎደላቸው አመራሮች ግን ከአገራዊ ራእይ በተቃራኒ ስለቆሙ የክልሉ ህዝብ ገና ሳይደራጅ ሌላ ሀሳብ ውስጥ እንዲገባ ተስፋ እንድቆርጥ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በይደር የቆዩ አጀንዳዎች ባለቤት የላቸውም፡፡ አሁንም በየቀኑ ሌላ ተቃራኒ አጀንዳ በመፍጠር ክልሉን የትርምስ ቀጠና እያደረጉ ናቸው፡፡ በየዞኑ አጀንዳ ተፈብርኮ የሚሰጠው በክልሉ ቁልፍ አመራሮች ነው፡፡ በአንድ ዞን ሁለት ቡድን በማደራጀት አንዱ አንዱን እየመረጀ አከባቢዎች በሙሉ የትርምስ ቀጠና ሆነዋል” በማለት የሴራ ወጥመድ አብራርተዋል፡፡

የመረጃ ምንጫችን ጨምሮ ሲያስረዳ “ለአብነት ጋሞ ዞን፣ ኮንሶ ዞን፤ ዎላይታ ዞን፣ ደቡብ አሞ ዞን፣ ጎፋ ዞን፣ ባስኬቶ ዞን፣ ቡርጂ ዞን፣ ጌዴኦ ዞን… ሁሉም ዞን ውጥረት ውስጥ ናቸው። ለዘመናት አብሮ በአንድ ዞን ተደራጅቶ የኖሩ ያሁኖቹ የአሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ የአጀንዳው ባለቤት የክልሉ ፓርቲ ሃላፊ ነው፡፡ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሪነት በጋሞ ዞን የዜይሰ እና የቁጫ ህዝቦች የመብት ጥያቄ ለማፈን በሚደረገዉ አመፃ ፖለቲካ በርካታ ንፁሃን ዘጎች ሞትና እስራት እየተሰቃዩ ይገኛሉ” ብለው ያብራራሉ፡፡

አክለውም “የቀድሞ ሰገን ዞን ተብሎ የሚታወቁ አከባቢዎች በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ የግጭቱ መሪ ስነ ምግባር የጎደለው ሴተኛ አዳሪዎችን ይዞ በየመጠጥ ቤት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሽጉጥ እያወጣና እየተኮሰ ዓመት ሙሉን የከረመዉ የክልሉ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ነው፡፡ የጎፋ ዞን በእርስበርስ ግጭትና መከፋፈል እየተተራመሰ ይገኛል፡፡ መሪ ተዋናዩ በሰማይ በምድር ከዎላይታ ጋር አንደራጅም ያለው አሁን የዲላ ክላስተር አስተባባሪ የሆነ ግለሰብ ነው” ብለዋል።

“ጌዲኦ ዞን ለሁለት ተከፍሎ እየተናጠ ነው፡፡ መሪው የክልሉ ፕረዝዳንት ሲሆኑ በህዝብ ተጠልቶ በምርጫ ጭምር ተሸንፎ ብልጽግናን የጣላውና ያዋረደው አቶ ሃይለማርም ተስፋየን አስተባባሪ አደርጋለሁ በሚል እና በህዝብ ቅቡልነቱና በእውቀቱ ተወዳዳሪ የለሌለው ዶ/ር አባባዬሁ ታደሰን “አነሳለሁ” በሚል ቅዠት ጌዴኦን እያበጣበጠ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የክልሉ ምክትል ፕረዝዳንት ሆኖ የመጣው ሽማግሌም ገና ከመምጣቱ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ የጎሳና የቤተሰብ አደረጃጀት ፈጥሮ ዎላይታ ዞንን እያተራመሰ” እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

“እነዚህ አካላት ጸረ ብልጽግና ናቸው ሲባል በብዙ ማሳያ ስሆን በቀን 8/02/2017 የተጠቃለለው የብልጽግና ፓርቲ ሥልጠና በክልሉ ሶዶ ማዕከል የተጠቃለለ ብሆንም ሰልጣኞች በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር እንዳይቀይሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሰጠው ማጠቃለያና ከስራ ስምሪት ተቃራኒ በሆነ መልኩ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አሰልቺና ከስልጠና ርዕስ ጋር የማይሄድ ማጠቃለያ በመስጠት ሀገራዊ የፓርቲ ስልጠና አቅጣጫውን ስቶ እንድጠናቀቅ አድርገዋል” በማለት ትዝብታቸውን አጋርተዋል፡፡

“በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰሩ በተለይ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ ኢንሼቲቦች አንድ እንኳን በክልሉ ዉጤታማ ልሆኑ አልቻለም፡፡ በግል ባለሀብቶች ደረጃ የተሰራውን የእርሻ ልማቶች መጎበኘት ማንን ለመሸወድ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ የሽወዳ ፖሌቲካ ዲስኩር ህዝቡን ከደኢህደን ፖሌቲካ በላይ አንገሽግሾታል” ብለዋል፡፡

እኚሁ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ለህዝብ፣ ለመንግሥትና ለፖርቲ ህልውና ለማስጠበቅ በሚል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እየተስተዋለ የሚገኘውን የፖለቲካ ብልሽት ይፋ እንዲደረግ በላከልን መረጃ፦ “የኮንትሮቫንድ ንግድ ቀጥተኛ ተሳትፎ፣ በከበሩ ማዕድናት (በድንጋይ ከሰል) እና በሌሎች ኢንቨስትመንት ዘርፎ የሚታየው ሌብነት፣ ዝርፍያና መሰል ተግባራት በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አመራርና በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ ቅንጅት በዲላና በኮንሶ መስመር ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ሆኗል፡፡ በከፍተኛ አመራሩ አማካይነት በየሆቴሉ የሚደረገው ብልግና ለማንም የተሰወረ አይደለም” በሚል ገልፆታል፡፡

“በክልሉ ህዝብ ዘንድ መጠራጠር፣ መተማማትና የባለቤትነት ስሜት እንዳይሰማቸው ፍትሃዊነት የጎደለ ውሳኔዎች፣ ግልጸኝነት የጎደለው አሰራር የራስ ቡድን በማደራጀት በቡድን አማካኝነት የደቦ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መቃቃርን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርጉት በአንድ በኩል የራሳቸውን የግል ጥቅም ለማግበስበስ፣ በሌላ በኩል አገራዊ ሪፎርም ወደ መሬት እንዳይወርድና ተንገራግጮ እንዲቆም የተሰለፈ ብልፅግና ፓርቲ አደራና ሹመት የተሰጠዉ ግን አደራዉን ከነመፈጠሩ የዘነጋዉ የደቡብ ክንፍ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም” በማለት አረጋግጠዋል፡፡

በማጠቃለያው ሀሳባቸውም፦ “የክልሉ ህዝብ ሰላምና ልማት እንድያገኝ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻቸው እንድመለስላቸው ከሁሉ በላይ የህዝቦች አንድነት ተጠብቆና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይህ ፀረ ህዝብ፣ ጸረ ለውጥ፣ ፀረ ብልጽግና ፀረ-ህብረትና ፀረ-አንድነት የሆነ ሴረኛ ሃይል ልስተካከል ይገባል፡፡ ካልሆነ….. ጨው ለራስ ካለ ይጣፍጥ!” የሚል የማሳሰቢያ፣ የማንቂያ እንዲሁም በክልሉ እየተስተዋለ ያለው ሁኔታ በአስቸኳይ በሚመለከታቸው አካላት ማስተካከያ እርምጃ እንዲደረግበት ለህዝብም ለመንግሥትም ወደ አደባባይ አውጥተዋል። #Ethiopia #SouthernEthiopiaregion #Wolaita #Gofa #Gedio #Gamo #Burji #Konso #Arizone #Kore #Alezone #Basketo