
በዎላይታ ዞን የመምህራን ደሞዝ አሁንም አልተከፈለም፤ ትምህርትም አልተጀመረም ቢባልም “ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውን ነው የምናውቀው” ሲሉ አቶ ጎበዜ ጎዳና ምላሽ ሰጡ
በሌላ በኩል ደመወዝ የተከለከሉ መንግሥት ሠራተኞች ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ሲል ከድለላ ጀምሮ እስከ ጉልበት ሥራ ያገኙትን ሁሉ እንደሚሰሩ ጠቅሰው “በልተን ማደር አለብን በሚል ወደ ቢሮ አይገቡም፤ በአንዳንድ መ/ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሠራተኞች አይታዩም፥ ቁጭ ብለን ከምንሞት ብለው ቢሮ ዘግተው ወደ ገጠርና ሌሎች አካባቢዎች ሄደዋል“ ብለዋል።
በዎላይታ ዞን ከመምህራን የደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ የ2016 የመማር ማስተማር ሥራ እንደታጎለ ነው ዓመቱ ያለቀው፡፡ የመምህራኑ ጥያቄ አሁንም መፍትሄ ባለማግኘቱ ችግሩ ወደ 2017 ዓም ተሻግሯል መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዞኑ አብዛኞቹ አካባቢዎች ከግል ትምህርት ቤቶች በስተቀር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እስከአሁን ትምህርት አልተጀመረም።
የቀጠለው የመምህራን ደሞዝ ጥያቄ በዎላይታ ዞን ከመምህራን የደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ የ2016 ዓም የመማር ማስተማር ሥራ እንደታጎለ ነው ዓመቱ ያለቀው። የመምህራኑ ጥያቄ አሁንም መፍትሄ ባለማግኘቱ ችግሩ ወደ 2017 ዓም መሻገሩ ነው የሚነገረው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁን ላይ በዞኑ አብዛኞቹ አካባቢዎች ከግል ትምህርት ቤቶች በስተቀር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እስከአሁን ትምህርት አልተጀመረም፡፡
ዶቼ ቬሌ ያነጋገራቸው በዞኑ ዳሞት ወይዴ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ሁለት የተማሪ ወላጆች በወረዳው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ትምህርት አለመጀመሩን አረጋግጠዋል። አንዳንዴ ተማሪዎች ቤት አንቀመጠም በሚል ትምህርት ቤት ደርሰው እንደሚመለሱ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ “ነገር ግን መምህራኑ ባለመግባታቸው ልጆቻችን ትምህርት ሊጀምሩ አልቻሉም፡፡ አንዳንድ ወጣቶችም ትምህርት እስኪጀመር በማለት የቀን ሥራ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደዋል“ ብለዋል፡፡
በዎላይታ ዞን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የመምህራንም ሆነ የሌሎች መንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ በወቅቱ አይከፈለም፡፡ ዘግይቶ ቢከፈልም የደሞዛቸው ከ20 እስከ 50 በመቶ ብቻ እየተሰላ እንደሚያገኙ ነው የሚነገረው፡፡ የዞኑ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር መምህርት ባዩሽ ዘውዴ የመምህራን የደሞዝ ጥያቄ አለመፈታት የትምህርት ሥረዓቱን እየረበሸ ይገኛል ይላሉ፡፡
የመምህራን ደሞዝ በመቶኛ ተቆራርጦ መከፈሉ አግባብ እንዳልሆነ የጠቀሱት ሊቀመንበሯ“ ይህ ሠላሳ ቀን የሚመገብ ገንዘብ አይደለም፡፡ ሥለሆንም ቶሎ መፈታት ይገበዋል“ ብለዋል።
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዎላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጎበዜ ጎዳና የመምህራኑ ጥያቄ ተገቢነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ እኛ እንደመምሪያ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውን ነው የምናውቀው ያሉት ሃላፊው“ ነገር ግን እስከአሁን ትምህርት ቤቶች አልተከፈቱም በሚል በሪፖርት የደረሰን ነገር የለም ብሏል፡፡
አቶ ታደሰ ሻንካ በዎላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ ላለፉት 26 ዓመታት በወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት በድጋፍ ሰጪ ሠራተኛነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ “የሚከፈለኝ ደሞዝ አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው“ የሚሉት አቶ ታደሰ“ እሱንም ቢሆን በወቅቱ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከአምስት ቤተሰቦቼ ጋር ችግር ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ቤተሰቦቼን ለመመገብ ለጊዜው የመንግሥት ሥራውን በመተውና ወደ ገጠር በመግባት የጉልበት ሥራን አማራጭ አድርጌ እየሠራሁ እገኛለሁ” ብለዋል፡፡
በዚሁ የዎላይታ ዞን የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት ደምሴ ቶጋ በወረዳው ለሦስት ወራትና ከዚያ በላይ ደሞዝ ሳይከፈል እንደሚቆይ ይናገራሉ፡፡ ደሞዝ ቢከፈልም በመቶኛ ተሰልቶ በግማሽና ከዚያ በታች እንደሚደርሳቸው የጠቀሱት ደምሴ“ አሁን ላይ እኔን ጨምሮ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ አማራጭ ኑሮ ለመፈለግ ተገዷል፡፡ እኔም የቤተሰቤን ረሀብ ለማስታገስ ስል ገጠር ገብቼ ካዛቫ መትከል ጀምሪያለሁ ” ብለዋል ፡፡
በመንግሥት ተቋማት ላይ ያሳደረው ተፅእኖ
በዎላይታ ዞን በሚገኙ 17 ወረዳዎች የሠራተኞች ደሞዝ ክፍያ አለመፈጸም የጤና ተቋማትን ጨምሮ በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያቤቶች ላይ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ አብዛኛው ሠራተኛ ተስፋ በመቁረጥ በሥራ ገበታው ላይ እንደማይገኝ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች በዚህም የተነሳ አንዳንድ መሥሪያቤቶች በከፊል ሌሎቹ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል ብለዋል፡፡
“ሠራተኛው ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሲል ከድለላ ጀምሮ እስከ ጉልበት ሥራ ያገኘውን ሁሉ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ“ በልተን ማደር አለብን በሚል ወደ ቢሮ አይገቡም፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ መሥሪያቤቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሠራተኞች አይስተዋልባቸውም፡፡ ምክንያቱም ቁጭ ብለን ከምንሞት ብለው ቢሮ ዘግተው ወደ ገጠርና ሌሎች አካባቢዎች ሄደዋል“ ብለዋል፡፡ #Ethiopia #Wolaita