
ምርጫ ቦርድ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ጨምሮ በ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የእግድ ውሳኔ አስተላልፏል።
በሌላ በኩል አገዳ የተጣለባቸው ፓርቲዎቹ እርምጃው “በሰላማዊ ትግል የሚታገሉ ፓርቲዎችን ከሰላማዊ ትግል ለማውጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው” በሚል ተቃውሞ አስገብተዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በጠቅላላ ጉባኤ፣ በኦዲት እና በሴት አባላት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ምክንያት ቦርዱ በተለያዩ ጊዜ በአስራ አንድ ፓርቲዎች ላይ የዕግድ ውሳኔ መስጠቱን አስታውቋል።
የዕግድ ውሳኔ የተሰጣባቸው ፓርቲዎች የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጌዲኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የጋምቤላ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክቲክ ኅብረት እና አገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ናቸው ።
በፓርቲዎቹ ላይ የተሰጠው የዕግድ ውሳኔ ውጤት ቦርዱ የተለየ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ፤ ለጊዜው ፓርቲዎችን ከማናቸውም ሕጋዊ እንቅስቃሴ ታቅበው እንዲቆዩ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
የዚህን የኮሚሽኑ ውስኔ ተከትሎ እገዳ ከተጣለባቸው ፓርቲዎቹ አንዱ የሆነው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ፍሰሃ፤ በፓርቲያቸው ላይ ውሳኔው የተላለፈው “የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች አባላትን መረጃ አላቀረበም” በሚል ምክንያት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ይህን መረጃ እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ ደብዳቤ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም እንደደረሳቸው የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ ሆኖም ፓርቲያቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የአባላቱን መረጃ ለመሰብሰብ “በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዳልፈቀደለት” አስረድተዋል። ፓርቲው ይህንኑ ችግሩን ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁንም አመልክተዋል።
“ፓርቲው ሀገር አቀፍ ፓርቲ ነው። ሰዎች ተንቀሳቅሰው፤ አባሎቻችን ጋር ሄደው መረጃ አሰባስበው ነው ይዘው የሚመጡት። ‘አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ አይፈቅድልንም፤ የሁለት ዓመት ጊዜ ይሰጠን። ሀገሪቷ ከተረጋጋች በኋላ እናመጣለን። የቦርዱን ትእዛዝ እና መመሪያ እንቀበላለን’ብለናቸዋል”ሲሉም አዲስ ትውልድ ፓርቲ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ማብራሪያ አስታውሰዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ቦርድ የእገዳ ውሳኔ ማስተላለፉ፤ “በሰላማዊ ትግል የሚታገሉ ፓርቲዎችን ከሰላማዊ ትግል ለማውጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው” ሲሉ አቶ ሰለሞን ተችተዋል። የገዳ ስርአት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሮበሌ ታደሰም የምርጫ ቦርድ ውሳኔ “የሰላም ትግሉ ላይ በር መዝጋት ነው” በማለት የተቃውሞ አስተያየታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሰጥተዋል።
ፓርቲያቸው ግንቦት 20፤ 2015 ጠቅላላ ጉባኤ ማድረጉን የሚገልጹት አቶ ሮበሌ፤“ለፓርቲው 12 አመራር ለመምረጥ 30 እጩ ማቅረባችሁ ተገቢ አይደለም” በሚል ምክንያት ፓርቲው በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉን አስረድተዋል። አቶ ሮበሌ ይህንን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ“ትክክል ያልሆነ”ሲሉ ነቅፈውታል።
አቶ ሮበሌ የሚመሩት የገዳ ስርአት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ እና የአገው ለፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 12፤ 2017 ዓ.ም የምርጫ ቦርድን የእግድ ውሳኔ በመቃወም ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባታቸውን ገልጸዋል። ሶስቱ ፓርቲዎች ለምክር ቤቱ ያስገቡት ደብዳቤ፤ የእግድ ደብዳቤው መስከረም 26፤ 2017 እንደደረሳቸው ይገልጻል።
ምርጫ ቦርድ “ወቅቱን ባልጠበቀ እና ጊዜን በማይዋጅ ሁኔታ ደብዳቤዎችን እየጸፈ በሰላማዊ ትግል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ላይ ችግር እየፈጠረብን ድርጅታዊ ስራዎችን ለመስራት ተቸግረናል” ሲሉም ፓርቲዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት “መድረክ በመፍጠር” ከቦርዱ ጋር “መፍትሔ እንዲያፈላልግ” ፓርቲዎቹ በደብዳቤው ጠይቀዋል።
የሶስቱ ፓርቲዎች ደብዳቤ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መድረሱን፤ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የጋራ ምክር ቤቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ከሶስቱ ፓርቲዎች የቀረበለትን አቤቱታ ተመልክቶ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍም ሰብሳቢው ጠቁመዋል። #Ethiopia