
“ዘርፈብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ማህበራዊ መድልዎ በጋሞ ዞን አመራሮች እየደረሰ ነው” ስል ቁህዴፓ ከሰሰ
ፓርቲው በዛሬው ዕለት ባወጣው አጭር መግለጫ “በጋሞ ዞን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አበረታችነት በቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) አባላት ላይ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝታችኋል በሚል የበቀል ጥቃት እየተፈጸመ ይገኛል” በሚል ገልጿል።

ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ፓርቲው በላከው በዚህ መግለጫ፦ “አብነቶቹ ብዙ ቢሆኑም በአንዳንድ የፓርቲያችን አባላት ላይ የተፈጸሙት ተግባራት አስቀያሚና በብርቱ መወገዝ ያለባቸው ናቸው” ብሏል።
“በቁጫ ወረዳ ጎይላ ቀበሌ አቶ ደረጀ ዳንጋሮ የተባሉት የፓርቲያችን አባል በደረቅ ጣቢያ ላይ በቀበሌው ሚሊሺያ አባላት ታግተው ለረዥም ጊዜያት እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን ለዚህ የቀረበውም ምክንያት የቁሕዴፓን ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ተካፍለሃል የሚል ነው፥ አቶ ደረጀ ዕሁድ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በቀበሌው ሊቀመንበር እና በሚሊሺያ አባላት በጋራ ብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) ከፍለህ መውጣት ካልቻልክ እንገድልሃላለን የሚል ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል፤ ዎላይታና ጋሞ ወደ ጦርነት እንዲገቡ አድርገሃል የሚል የቧልት ዓይነት ውንጀላም ቀርቦባቸዋል” ስል መግለጫው ያትታል።
ፓርቲው አክለውም “በክልላችን የአስተዳደር ዋና ከተማ በሆነችው ዎላይታ ሶዶ ከተማ መስከረም 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄደው የቁሕዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ከቁጫ ገላ እና ጎይላ ቀበሌዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል ብለው የአካባቢው ገዢዎች በጠረጠሩአቸው ግለሰቦች ላይ ቀጥሎ የተዘረዘሩት አስነዋሪ ተግባራት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ” በሚል ጋሞ ዞን አመራሮችን ከሷቸዋል።
መግለጫው ለአብነት በዚህ ምክንያት ሰብዓዊ ጥሰትና ህገወጥ ድርጊት የተፈፀመባቸውን አባላትን ስጠቅስ፦ አቶ ለማ መንገሻ ታስረው 50 ሺህ ብር እንዲቀጡ የተጠየቁ ሲሆን ለጊዜዉ 4 ሺህ ብር፤ አቶ ደምሴ ዳንጋሮ 100 ሺህ ብር እንዲቀጡ፤ ወጣት እንድሪያስ ኢያሱ ታስሮ 12 ሺህ ብር እንዲቀጣ፤ አቶ በላይ በለጠ ታስረው 16 ሺህ ብር እንዲቀጡ፤ አቶ ዳኜ ዳርጋሶ ታስረው 1 ሺህ ብር፤ ወጣት ታምራት ዘለቀ ታስሮ 2 ሺህ ብር፤ አቶ ስምኦን ደግሰው ታስረው 2 ሺህ 7 መቶ ብር፤አቶ ዝናቡ መኩሪያ ታስረው 1 ሺህ 1 መቶ ብር፤ አቶ ስንታየሁ ሼንደሮ ታስረው 4 መቶ ብር፤ አቶ ታረቀኝ ዳታ ታስረው 1 ሺህ ብር ተቀጥተዋል፤ አቶ ዛሳ ዛማላ ታስረው 2 መቶ ብር፤ ወጣት ቶማስ እስራኤል ታስሮ 2 መቶ ብር ተቀጥቷል” በማለት እያንዳንዱን ዘርዝሯል።
ክስተቱን ፓርቲው እንደመረመረው፦”አብዘኞችን ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች እና የመንግሥት ሠራተኞችን ጨምሮ ለማሰር እና ለመቅጣት እየፈለጓቸው እንደሆነ በመግለፅ የብዙዎቹ የሐሰት ክስ ርዕሶች የሚከተሉት እንደሆኑም አረጋግጠናል በሚል ሲያብራራ፥ በዎላይታ እና ጋሞ መካከል ጦርነት አውጃችኋል እንዲሁም የዎለይታ ዲቻ እግር ኳስ ቡድን T-Shirt ማሊያ ለብሳችኋል” የሚል እንደሆነ አስረድቷል።
ፓርቲው በመግለጫው “የአካባቢው የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች፣ በነዚህ ውንጀላዎች ሰዉ ከቤት ውጪ የትም እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ የፓርቲያችንን አባላት፣ ደጋፊዎችና የቁጫ ብሔረሰብ አባላትን ብቻ በመነጠል የመንቀሳቀስ ነጻነታቸውን በመንፈግ ላይ ናቸው፤ በተጨማሪም፣ በሦስቱም የቁጫ ሕዝብ መዋቅሮች በሚገኙ ቀበሌያት ተመሳሳይ ወንጀሎች በሰዎች ላይ እየተፈጸሙ ይገኛሉ” ብሏል።
በመጨረሻም “ቁሕዴፓ እንደዚህ ዓይነቱን ከባድ የአስተዳደር መላሸቅና የሥርዓተ መታጣት እየኮነነ ለችግሮች መፍትሔ እንዲመጣና ሕግ እንዲከበር እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ ሰላማዊ ትግሉን አጠንክሮ እንደሚቀጥልና ለቁጫ ሕዝብም አለኝታነቱን በድጋሚ እንደሚያስመሰክር ቃል በመግባት አምባገነንነትንና ሥርዓት አልበኝነትን በብርቱ እንደሚዋጋ በመግለጫው አረጋግጧል። #Ethiopia #Kuchazone #Gamozone