

የዎላይታ እና ጋሞ ወዳጅነት ከፖለቲካ ባሻገር- የፖለቲካ ወጌሻ ዝግጅት ከፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ጋር🙏 ቀጥታ ወደ ዝግጅታችን👇
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የዎላይታ እና የጋሞ ሕዝቦችን ወዳጅነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሸጋገር ምን መደረግ አለበት?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት በሁለቱ ዞኖች የሚገኘዉ ሕዝብ ወንድማማችነት ዛሬ የጀመረ ወይንም የሚጀምር ሳይሆን ከጥንትም የነበረ ነው። የቋንቋዉ ተቀራራቢነት ይታወቃል፣ እንደዉም በቁጫ፣ ቦሮዳ እና ምዕራብ አባያ አካባቢ የሚነገረዉ ከዎላይትኛ ጋር በጠቅላላ አንድ አይነት ቋንቋ ነው። አንድ መታወቅ ያለበት ነገር የትኛዉም አይነት አወቃቀር ይምጣ አይምጣ ሕዝቦቹ አንድ ላይ እየኖሩ መቀጠላቸዉ አይቀሬ መሆኑን ነው። ስለዚህ በዚህ ቀጠና የሚኖረዉ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ከሶስተኛ ወገን ተጽዕኖ ዉጪ በመሆን ወንድማማችነቱን ማጠናከር እንዳለበት ማወቅ አለበት።
አሁን ላይ በተጨባጭ ወዳሉት ፈተናዎች ስንመጣ በዎላይታ በኩል የክልል ጥያቄዉ በጉልበት ታፍኗል፣ አለ በቂ ድርድር ክልል ተጭኖብኛል፣ በክልልም በፈደራልም ከስልጣን ሚዛናዊ ዉክልና አላገኘሁም የሚሉ ቅሬታዎች መኖራቸዉ ግልጽ ነው። ከዛ ዉጪ ግን በቀጥታ ይሄን የሚያደርገዉ የበላይ አካል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፣ ለራሱ አላማ።
በጋሞ ዞን ደግሞ በቁጫ እና ዶርዜ የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ደረጃ መድረሱ ይታወቃል፣ በርግጥ የሕዝቦች ሕገመንግሥታዊ መብት ላይ አስተያዬት መስጠት ድርሻችን ባይሆንም፤ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ የአካባቢው ሕዝቦች እጣ ፋንታ የተጋመደና ነገ ከነገ ወዲያም አብሮ መኖርን የሚያስገድድ ነውና ሁሉም ነገሮች በሰላማዊ ዉይይት እና በወንድማማችነት መንፈስ መካሄድ አለባቸዉ።
ሶስተኛ ወገን ሳይገባ በአካባቢው ሊህቃን የሚደረግ የሰከነ ዉይይትና ድርድር መፍትሔ የሚወልድ ይመስለኛል። አሁን አንዳንድ ሊህቃን በጠላትነት የመተያዬትና በቃላት መጎሻሸሙ በፍጹም ተገቢ አይደለም፣ አዋጭም አይደለም። በተደጋጋሚ የሚታየዉ የአመራሮች ሽኩቻም፣ የፖለቲካ ዉሳኔዎች ላይ የሚታዩ ጥርጣሬዎች በምክክር የገራ አቅጣጫ ካለመቀመጡ የሚነሱ ናቸዉ፣ አንዳንድ ፓርቲዎችም በሕዝብና ግለሰቦች ላይ እያነጣጠሩ የሚያወጧቸዉ መግለጫዎች ከችግሩ የሚመነጩ ናቸዉ።
የቁጫ ፓርቲ በዎላይታ ሶዶ ይሰበሰባል፣ የጋሞ ፓርቲ ደግሞ በዎላይታ ላይ የክስ ናዳ ያወርዳል። እነኝህ ችግሮች ከአሁኑ ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት ባካተተ ምክክር መፍትሔ ካልተበጀላቸዉ የመሥፋት እድል አላቸዉ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በአሁኑ ሰአት በተጨባጭ በክልል ደረጃ መደረግ የሚችሉ ነገሮች ምንድናቸዉ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አንዱ አንዱን መረዳት አለበት፥ ዎላይታ በክልልም ሆነ በፈደራልም ሚዛናዊ ዉክልና አለማግኘቱ ግልጽ ነው፥ ክልል በጉልበትም ተጭኖበታል፣ ይህን ያደረገዉ የበላይ አካል ነው።
ዎላይታ ክልልም ሆኖ ቢሆን ከአካባቢው ሕዝብ ጋር መኖሩ አይቀርም፣ ወንድማማችነቱ ከመዋቅር በላይ ነው። በጋሞ በኩል ከዎላይታ ጋር አንደራጅም ያሉ አመራሮች ነበሩ ያ አርቆ አሰተዋይ አለመሆንን ያሳያል፣ ዎላይታን የተሳደቡ ወጣቶች በተደጋጋሚ አይተናል፣ በሽማግሌዎች እና በአመራሮችም በፍጹም ከእነሱ የማይጠበቅ ነገር ሲባል ሰምተናል።
በዎላይታም በኩል አንዳንድ ምሁራን ከእነሱ የማይጠበቅ ነገር ሲሉ ተደምጠዋል፥ በማሕበራዊ ሚዲያም የቁጫና ዶርዜን ጉዳይ የሚያራግቡ አሉ። መሰል ነገሮች መፍትሔ የሚያመጡ አይመስለኝም። በተጨባጭ ለዉጥ የሚያመጣዉ ግን ሁሉን አቀፍ ዉይይትና ድርድር ነው፣ የዛኔ የሶስተኛ ወገን በመሓላችን በፍጹም ገብቶ የማያደፈርሰዉ፣ ዘላቂ ወዳጅነት እንመሰርታለን።
በተጨባጭ ዎላይታ ሶዶና አርባምንጭ በክልሉ የሚኖራቸዉ ቦታ እንዴት ተያይዘዉ ያድጋሉ የሚለዉንም መወሰን ይቻላል። በምክክር ጽኑ ወዳጅነት፣ የአንዱ ችግር የሌላዉ፤ የአንዱ ሰኬትም የሌላዉም የሚሆንበትን አዉድ መፍጠር እንችላለን። ይህ ሕዝብ ተለያይቶ መኖር አይችልም፣ ተጣልቶ ሳይሆን ሳይጣላ ተመካክሮ ወንድማማችነቱን በጽኑ አለት ላይ ይመስርት።
በአሁኑ ሰዓት የሚደረገዉ የእዉር ድምብር ጉዞ ነው፣ ግልጽ በጋራ የተስማማንበት አቅጣጫ ባለመኖሩ ጥርጣሬዎች እየሰፉ ናቸዉ። ክልሉም የተቋቋመዉ በምክክር ሳይሆን በመፋጠጥና በመፈራረጅ ዉስጥ ነው። የኢትዮጵያ ፖለተካ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ዛሬ በትንሹ እጃቸዉን የሰደዱ ሶስተኛ ወገኖች፣ ነገም ሌላ አተካራቸዉን አምጥተዉብን ይህንን ምስኪን ወንድማማች ሕዝብ እንዳይጎዱት እፈራለሁ።
ነገሮችን በምክክር መቋጨት ከተቻለ ደግሞ አንዱ ለአንዱ አለኝታ ይሆናል። ወደድንም ጠላንም በዚህ ወንድማማች ሕዝብ መሐል፣ በመፈራረጅና ጣት በመጠቋቆም የሚደረግ እንቅስቃሴ መጨረሻዉ ብቻ ሳይሆን መንገዱም እራሱ የዉድቀት ነው። ይህ ቋንቋ፣ ባሕልና መልከአ ምድር ያጋመደዉ ሕዝብ ግንኙነት፣ ዘላቂ ወንድማማችነትን ያማከለ መሆን አለበት።
በምክክር የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ከተቻለ፣ በጋራ በተሻለ ሁኔታ መልማትና አንዱ ለአንዱ ድጋፍ ሊሆን ይችላል፣ በጋራም በተናጠልም በወንድማማችነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይቻላል፣ የሚጠቅመንም ያ ብቻ ነው። የዎላይታ እና ጋሞ ሕዝቦችን ዘላቂ ወንድማማችነት ያላገናዘበ የየትኛዉም ወገን አካሄድ አያዋጣም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
WolaitaTimes ሚዲያ, ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ 🙏 ስለአብሮነታችሁ እናመሰግናለን🙏

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን። #Gamozone #Wolaita #Ethiopia #southethiopia
በጋዜጠኛ ናትናኤል ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተሰናዳ ዘገባ ነው