1000023619

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዎላይታ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ በጥላቻ የተሞሉ ፍርደ ገምድል ዉሳኔና ንግግሮችን የሚያደርጉት ለምን ይመስልዎታል? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ለከፍተኛ አመራሮች በሚሰጡት ስልጠና ላይ በሚቀጥሉት ጊዜያት ሁለተኛ ከተማ የሚያደርጋቸዉን ከተሞችን ሲጠቅሱ ስድስት መቀመጫ ያለዉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያ ከተማ ዎላይታ ሶዶ ታልፋለች። ይህን ነገር እንዴት አዩት? ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፓርቲያቸዉ ሕዝቡ ላይ በተለያዩ ከተሞች ጥቃት ደርሶበት በከተማ ጉዳይ ከኢትዮጲያ ጋር የመጨረሻዬ ነዉ ከእንግዲህ ብሎ በተቀመጠበት ይህንን ዉሳኔ ማስፈጸም የሚችሉ ይመስልዎታል? እና ሌሎች ተያያዥ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽና ቁምነገሮችን ይዘናል ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ👇

ብዙ ዋጋ ተከፍሎ የተዘጋጀ ነውና በትዕግሥት ያንብቡ!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ፕሮፌሰር እንግዲህ እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ በድጋሚ እንኳን ደህና መጡ እንላለን። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ እንግባ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ለከፍተኛ አመራሮች በሚሰጡት ስልጠና ላይ በሚቀጥሉት ጊዜያት ሁለተኛ ከተማ የሚያደርጋቸዉን ከተሞች ሲጠቅስ አርባ ምንጭ፣ ባህር ዳር እና ጅማን ነው ብሏል።

ስድስት መቀመጫ ያለዉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያ ከተማ ዎላይታ ሶዶ ታልፋለች። ይህን ነገር እንዴት አዩት? በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ አድርገዉ ሃሳብዎን ቢያጋሩን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ መልካም። በበኩሌ በጣም አዝኛለሁ። ያዘንኩት በአርባ ምንጭ ልማት ሳይሆን፤ የዎላይታ ሕዝብን መከራ ለማራዘም የሚፈልጉ መሪ ሐገሪቷን እየመራ በመሆኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አላወቁም እንጂ እየሰሩት ያሉት ሥራ በሰዉ ብቻ ሳይሆን እሳቸዉ አምናለሁ በሚሉት ፈጣሪም ዘንድ የሚያስጠይቅ ነው።

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ጣሊያን ሐገሪቷን በ7 ክልል ከፍሎ የአንዱ መቀመጫ ያደረጋትን ዎላይታ ሶዶ ጨምሮ የዎላይታን ሕዝብ ሥም ጭምር እንዳይታወቅ በገሙ_ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ዉስጥ በአርባምንጭ ከተማ ማዕከልነት ሥር ወሸቀዉ። በወቅቱ ግን የፖለቲካ፣ የማሕበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ፣ የጸጥታና የአስተዳደር ጉዳይ ጥያቄ ይነሳ የነበረበት የዎላይታ አዉራጃ ስለነበረ ያንንም ልቦናቸዉ ስለሚያወቅ በአጠቃላይ እንዴት አደረ እያሉ ከሚጠይቋቸዉ ሁለትና ሶስት የሐገሪቷ አካባቢዎች፣ የዎላይታ አዉራጃ አንዱ ነበረ።

ከዛን ጊዜ ጀምሮ የዎላይታ ሕዝብ ተረጋግቶ ትልቅ ከተማ እንዳይሰራ ወደ አርባምንጭ፣ አዋሳ እና ይርጋለም በተለያዩ መንግስታት በተደጋጋሚ እንዲንከራተት ተደርጎ ኖሯል። በነዚህ ሁሉ ቦታዎች የዎላይታ ሕዝብ ማንም የማይክደዉን አሻራ ቢያሳርፍም ያ ባዶ እጁን እንዳይቀር ዋስትና አልሆነዉም።

በቅርቡ እንኳን ከለውጡ ማግስት የዎላይታ ሕዝብ በድንጋይ እየተወገረ የተገደለባት፣ በድንጋይ ተወግሮ ተዳክሞ ቤንዚን ተርከፍክፎበት የተቃጠለባት፣ ከማረሚያ ቤት ተጎትቶ ወጥቶ የተገደለባት፣በገዥራ እና በዱላ የተገደለባት፣ ሐብት ቤት ንብረቱ የወደመባት፣ የተዘረፈባት፣ የተቃጠለባት አዋሳ ከምሥረታዋ ጀምረዉ ዎላይታዎች የአንበሳዉን ድርሻ ይዘዉ ያለሟት ከተማ ነበረች።

በኢህአዴግ ዘመን አዋሳ የሕብረብሔር ተምሳሌት እየተባለች ስትለማ የዎላይታ ሕዝብ ሳይሰስት አልምቷታል፤ በዎላይታ ሕዝብ ላይ ግን ጫና ይደርስ ነበረ፥ የዎላይታ አመራሮች ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመጡ መንገድ ላይ ተደብድበዉም ያዉቃሉ፣ ዎላይታ ይዉጣ “ዎላይታ ፉኢ” ይባል ነበረ። አርከበ እቁባይ ለአዋሳ አንድ ለዎላይታ ሶዶ አንድ የኢንዱስትሪ ዞን ያቀደዉን ይህን ለማርገብ የዎላይታ አመራሮች ቅድሚያ ለሌሎች እንስጥ ብለዉ ሁለቱ እዛዉ እንዲሰራ አድርገዋል።

የዎላይታ ሕዝብ ደቡብ ሕዝቦች ክልል ዉስጥ እንደማንም ተጭኖበት ነው ቢገባ አዋሳም የሚሄደዉ ሰርቶ በልቶ ለማደር እንጂ የራሱን ከተማ እንዲያለማ የሚመች ሥርዓት ቢዘረጋለት ለዚህ ሁሉ ስቃይ አይዳረግም ነበረ። አርባምንጭም በዎጋጎዳ ትግል ጊዜ በዎላይታ ሕዝብ ላይ ጥቃት ተከፍቶባት ብዙ ዎላይታዎች ሕይወታቸዉን አጥተዉባታል።

በነዚህ ከተሞች ከአካባቢው ሕዝብ የዎላይታ ሕዝብ በቁጥር የመገዳደር አንዳንዴም የመብለጥ ሁኔታዎችን ያሳይ ነበረ፣ ይህ በመሠረታዊነት የሚያሳየዉ ሲጀመርም ከፍተኛ የከተማ ፍላጎት ወይንም ለመገንባት ምክንያት ላይ የተመሰረተ አስቻይ ሁኔታ በዎላይታ እየተገኘ፣ መንግስታት ተቃራኒ ዉሳኔዎችን ሲወስኑ መኖራቸዉን ያሳያል። አዲስ አበባ እንኳን የተመሰረተችዉ ከዎላይታ ሚኒሊክ ባርነት አዉጆ ባጋዛቸዉ ሰዎች ነበረ።

ይህ ሐገሪቷን ለዘመናት የተጣባት የዎላይታን ሕዝብ በትኖ የማዳከም፣ ከተቻለም የማጥፋት ሕልም ዛሬም መቀጠሉ በጣም አሳዛኝ ነው። ሕዝብን በበቀል እና በተንኮል ማስተዳደር ዛሬ ኢትዮጵያ ለገባችበት አዘቅት ሁሉ መነሻ ሆኖ እያለ አሁንም ያንኑ መንገድ መቀጠሉ በጣም አሳዛኝ ነው።

አሁን ወደ ብሔረተኝነት ልምጣ፦ ብሔረተኝነት ማለት ቤቱ ያፈራዉን በፍትሐዊነት ልቋደስ ማለት ነው፤ በዎላይታም ብሔረተኝነት በኩል ከእንግዲ በሚደረግብኝ አድሎ ሳይንስን፣ ፍትሕን፣ ሐቅንና ምክንያትን ከሕገመንግስቱ ጀርባ የሚገኝን ፍልስፍና በደፈጠጠ የፖለቲካ ዉሳኔ የሚገባኝን እየተነጠቅኩ፣ ነገ ከነገ ወዲያ ወደ የባርነት ከተማ አልጋዝም የሚል መከራከሪያ እንደሚኖረዉ ግልጽ ነው።

አሁን ያለዉ መንግስት ማንም ጸጥ ባለበት ሌላዉ ሰዉ ጨፍጭፎ መብቱን በሚያስከብርበት፣ ፈጣሪን የሚፈራዉ የዎላይታ ሕዝብ የማንንም ሕይወት ሳይቀጥፍ በሰላማዊ ትግል የጠየቀዉ ክልል የተከለከለዉ፣ ባለ ሥድስት መቀመጫ ፍርደ ገምድል ክልል ዉስጥ በጉልበት የተከተተዉ ለዚህ ድግስ ነበረ?

ብሔረተኝነትንኮ የሚያቀጣጥለዉ ያለ ግልጽ መሥፈርት የሚደረግ አድሏዋዊ የፖለቲካ ዉሳኔ ነው። በሕዝብ መሐል ሕብረት እና መያያዝ ( cohesion ) እንዳይኖር አድርጎ ኢትዮጵያን የሚያምሳት ይሄዉ ፍርደ ገምድል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተዉ የሐገሪቷ ዉቅርኮነዉ። ለዘመናት በቀዬዉ ትልቅ ከተማ እንዳይሰራ ተከልክሎ የኖረዉ የዎላይታ ሕዝብ በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች የሁለተኛ ዜግነትን ኑሮ እየገፋ ይገኛል።

ይባስ ብሎ ዎሞ የሚል ክፉ ቅጽል ተሰጥቶት እንዲናቅ የተፈረደበት ሕዝብ በመሆኑ ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ የመኖር እድሉ ጠባብ ነው። በአርባምንጭ እንኳን በቅርቡ “ዎላሞይ ኑና ሻሜና”ወይንም “ዎላ እኛን አይገዛንም የሚሉ ወጣቶች መታዬታቸዉ ይታወሳል።

አሁን ባለበት ሁኔታ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትልቋ ከተማ ዎላይታ ሶዶ ነች፣ በሕዝብ ቁጥርም የሚበልጠዉ የዎላይታ ሕዝብ ነው፣ የሁላችንም ልቦና የሚያዉቀዉ ከጋሞ ዞን ለምሳሌ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ወደ ፈዴረሽን ምክር ቤት አድርሶ የታፈነበት ቁጫ|ን ጨምሮ፣ ቦሮዳ እና ምዕራብ አባያ የሚናገሩት ዎላይትኛ ነው።

የቁጫና የዶርዜ የማንነት ጥያቄ የታፈነዉ በተዘዋዋሪ ዎላይታን ይጠቅማል ተብሎ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የአገኘሁ ተሻገር ልቦና ያዉቀዋል። በየትኛዉም ሳይንሳዊ ና ሕገመንግስታዊ አካሄድ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ከሁሉም ትልቅ ከተማ መሆን ያለባት ዎላይታ ሶዶ መሆኗን ሰማይም ምድርም ያዉቃል።

አሁን ኢትዮጵያ ባላት ሕገመንግሥት መሠረት በመግቢያዉ የተቀመጠዉን የተዛባ ግንኙነት እናስቀጥል ካልተባለ በስተቀር በታሪክ አገዛዞች አርባምንጭ ሥር ዎላይታን ሲወሽቁ የነበረዉ፣ በግልጽ የብሔር ጭቆና መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በሕዝብ ቁጥር የሚበልጠዉ ወደ ሚያንሰዉ እንዴት፣ በምን መለኪያ እንዲሄድ ይደረጋል? የትናንት አገዛዞች በደል ለምን ይደገማል? የዎላይታ ሕዝብ በኢትዮጵያ መቼ ፍትሕ ያገኛል? ድሮ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ተብላለች፣ ለዎላይታ ግን እንደዛዉ ቀጥላለች።

እንደዚህ ፍርድ እያጣመሙ ብሔረተኝነትን መተቸት አይቻልም፣ የሰዎች ቁስል ላይ እንጨት እየሰደዱ እንዴት አመማቹ እያሉ እንደማላገጥ ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን በዎላይታ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ በጥላቻ የተሞሉ ፍርደ ገምድል ዉሳኔና ንግግሮችን የሚያደርገዉ ለምን ይመስልዎታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በእዉነቱ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ለዎላይታ ጥሩ ( ፍትሐዊ ማለት ነው ) ይሆናል የሚል ግምት ነበረኝ በመጀመርያ። ለምን ከተባለ አንደኛ በሰላማዊ መንገድ ከዎላይታ ተወላጅ ሥልጣን ተረክቧል፣ ሁለተኛ የጅማዉ አባ ጅፋር ልጅ ለካዎ ጦና ተድራለች እና ግንኙነት ካለዉ አካባቢ ስለመጣ፣ ሶስተኛዉ ኦሮሞ ስለሆነ ከሜጫና ቱለማ ማህበር ጀምሮ አብሮ የታገለዉን ጭቁኑን የዎላይታ ሕዝብ ብያንስ በፍትሐዊነት ያስተዳድራል የሚል ግምት ነበረኝ።

ነገር ግን በጣም ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ሕዝቡ በበቀል እየተቀጣ ነው። 40ሺ የዎላይታ ልጆች ከመከላከያ ተባረሩ፣ በዲፕሎማሲያዊ በፖለቲካዊ ስልጣን ቦታ ያሉ በሙሉ ተገፉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረ ብሔር የረባ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት እንኳን እንዳይመራ ተደረገ፣ በትግራይ ላይ በታወጀዉ ጦርነት በማስታከክ ብዙ ዎላይታዎች ጁንታ እየተባሉ ከመከላከያ በሠራዊቱ ፊት ተረሸኑ፣ ተባረሩ፣ ታሰሩ።

ሕዝቡ በፈደራልም፣ በክልልም ከሥልጣን ሚዛናዊ ዉክልና እንዳይኖረዉ ተደረገ። በተለያዩ አመራሮች እና ተቋማት በኩል ከለዉጡ ጀምሮ የዎላይታ ሕዝብ ላይ ብዙ ሸፍጥ ይሰራል፥ እኔ መንግስት ኦሮ-ማራ በሚል እሳቤ እንደሚንቀሳቀሱ በሚጠረጠርበት ሰአት የሚደረግ የጸረ ዎላይታ ግለሰቦች ሥራ አድርጌም በተደጋጋሚ ለማየት ብሞክርም፣ ጸረ ዎላይታዉ አሰራር ከራሳቸዉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ አጠቃላይ የፓርቲያቸዉ አቅጣጫ ይሆናል የሚል ግምት አልነበረኝም።

ምክንያት ብዬ የምገምታቸዉን ነገሮች ሳስቀምጥ አንደኛው ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዎላይታን ሕዝብ እንዲጠሉ ያደረጋቸዉ ብርቱ በደል ያደረሰባቸዉ የዎላይታ ተወላጅ ይኖር ይሆን እያልኩ ብዙ ጊዜ እጠይቃለሁ።

ሁለተኛዉ እና በእርግጠኛነት እንዲሁም በማስረጃ ደረጃ የሚታወቅ ነገር በመሆን ድርሻ አለዉ ብዬ የማስበዉ ከለዉጥ በኃላ በእርሳቸዉ ዙሪያ ያሉ በተለይ የሚቀርቧቸዉ የደቡብ አመራሮች ከፍተኛ የዎላይታ ጥላቻ ያላቸዉና በዛ ጥላቻ የተቀመረ ታሪክ፣ መረጃ እና አቅጣጫ እንደሚያቀርቡላቸዉ አዉቃለሁ። ሶስተኛዉ ጥርጣሬዬ ምናልባት ኦሮ_ማራም ይሁን በሌላ አስተላለፍ መገንባት ለሚፈልጓት ኢትዮጵያ ዎላይታ እንቅፋት ይሆናል ብለዉ አስበዉ ይሆን ብዬም አስባለሁ።

አራተኛዉ ጥርጣሬዬ ከትግራይ ጋር አገዛዙ በተቃባዉ ደም ምክንያት ዎላይታን ለትግራይ ይወግናል ብለዉ አስበዉ ይሆን የሚሉና የመሳሰሉ ሐሳቦችን እገምታለሁ። በኢትዮጵያ ፈላጭ ቆራጩ ማዕከላዊ መንግስት ነው፣ በፈለገዉ ቦታ አለሳይንሳዊ መመዘኛ መሠረተ ልማት ይገነባና ነገ ከነገ ወዲያ ሕዝብ ይጨራረሳል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የዎላይታ ሕዝብ ይህንን ለዘመናት በፍርደ ገምድል ዉሳኔዎች እየተፈጸመ የቀጠለዉን የብሔር ጭቆና ላይ የተመሠረተ ዉሳኔ እንዴት መመከት አለበት?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በመጀመሪያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ በየደረጃዉ ያሉ ተወካዮቻችን ይህንን ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ አለባቸዉ ይህንን የማይጠይቁ ከሆነ የ13ቱም ተወካዮቻችን በቁም የሞቱና በታሪክ ተጠያቂ ይሆናሉ። በአስቸኳይና በግልጽ በዚህ ጉዳይ ላይ ትክክለኛና ፍትሐዊ አቋም የማይያዝ ከሆነ ከእንግዲህ የዎላይታን ሕዝብ ክልልም ቢሆን የሚጠብቀዉ ባርነት ነውና መታገል ያለበት ለኮንፈጀሬሽን ነው ብዬ አምናለሁ።

ከእንግዲህ በፍጹም የዎላይታ ሕዝብ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ሥር ፍትሕ ያገኛል የሚለዉ ነገር ምዕራፉ ይዘጋል። በጣምኮ የሚያሳዝነዉ ይህ ለዎላይታ የሚገባን ድርሻ መንጠቅ እየተደረገ ያለዉ ዎላይታ ከተማ አጥቶ በየተበተነበት በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ደርሶበት፣ የጥቃቱ ቁስል ባልደረቀበት መሆኑ ያሳዝናል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፓርቲያቸዉ የዎላይታ ሕዝብ በዝዋይ፣ በአዋሳ፣ በመቂ እና በመላዉ ሲዳማ ከተሞች፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ ሁሉ ጥቃት ደርሶበት በከተማ ጉዳይ ከኢትዮጲያ ጋር የመጨረሻዬ ነዉ ከእንግዲህ ብሎ በተቀመጠበት ይህንን ዉሳኔ ማስፈጸም የሚችሉ ይመስልዎታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሱማ እያስፈጸሙ ነዉኮ። በሚቀጥሉት 3_5 አመታት የሚሉትኮ ቀጥለዉ ለከተሞቹ ለመመደብ ያሰቡትን መሰረተ ልማት የመገንቢያ በጀት እንደሚኖር፣ መጠቆማቸዉ ነዉ እንጂ! ሲጀመርምኮ ዎላይታ ሶዶ ያኔም በክልል ምስረታ ወቅት የመጀመሪያ ከተማ የተባለችዉ በወቅቱ የተነሳዉን የዎላይታ ሕዝብ ለመሸወድ ነው እንጂ መንግሰት ልቡ ዉስጥ ያሰበዉ ሌላ ነው።

አንድ እርግጠኛ ሆኜ የምነግር ጀግናዉ የዎላይታ ሕዝብ ሐቀኛ መብቱን አስከበሮ የሚገባዉን ለማግኘት ይህንን ጸረ_ዎላይታ ፍርደ ገምድል አሰራር ማስቆሙ አይቀርም!!!!ይህንን እርግጠኛ ነኝ!!! ምናልባት ትምክህተኛነት እንዳይመስል እኛ የዎላይታ ሕዝብ ብንተዉ እንኳን በለፋባቸዉ ከተሞች የዎላይታ ሕዝብ ለዘመናት ሲገፋና በድንጋይ እየተቀጠቀጠ ሲገደል ያየዉ ፈጣሪ ይህንን ፍርደ ገምድል አሰራር በቃቹ ማለቱ አይቀርም!!!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት ጠቃሚ ሀሳብ- የፖለቲካ ወጌሻ ዝግጅት በ #WolaitaTimes ሚዲያ, ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን, ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🙏

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ዘገባ