1000023761

ለመሆኑ ዘርፈብዙ ችግር የተጋረጠበት የዎላይታ ህዝብን የወከሉና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ጥቅማቸውን መርጠው ዝምታ የመረጡ 13ቱ “ተወካዮች” እነማናቸው ?

1. ዶ/ር አሰለፈች ኩቼ — ከኪንዶ ዲዳዬ ወረ፥
2. አቶ መለሰ መና — ከኦፋ ወረዳ፥
3. ዶ/ር እንዲሪያስ ጌታ — ከኪንዶ ኮይሻ ወረዳ፥
4. ወ/ሮ አልማዝ አሳለ — ከቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ፥
5. አቶ ተክለወልድ አጥናፉ — ከቦሎሶ ሶሬ ወረዳ፥

6. ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ — ከዳሞት ሶሬ ወረዳ
7. አቶ ተስፋጽዮን ሹኮ — ከሶዶ ዙሪያ 1
8, ዶ/ር ብርሃንፀሐይ አካለወልድ — ከሶዶ ዙሪያ 2
9. ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ — ከሁምቦ

10. ወ/ሮ አረጋሽ ተክሌ — ከዳሞት ወይዴ
11. አምባሳደር ተሾመ ቶጋ — ከዱጉና ፋንጎ
12. ወ/ሮ መቅደስ ደስታ — ዳሞት ጋሌ
13. ወ/ሮ እታፈራሁ ሞታ —  ዳሞት ፑላሳ። ናቸው።

እነኚህ አሁን አሁን በአከባቢው እየተስተዋለ ያለ ኢፍትሃዊነትን ለመታገልና በህዝብ ውግንና በአደባባይ ለመናገር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ በህዝብ ወክልና የገቡ ከላይ የተዘረዘሩ 13ቱም ተወካዮች እንዲሁም በየደረጃዉ ያሉ ተወካዮች የህዝብ አደራ ወደጎን በመተው ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ብቻ በማድረግ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣታቸው በታሪክ ተጠያቂ ይሆናሉ።

እንደሚታወቀው የዎላይታ ዞን በሀገሪቱ ከየትኛውም አከባቢ በላይ ወደ 2 መቶ ሺህ የሚጠጋ ከታወቁ ከፍተኛ ዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች የተመረቁ የስራ አጥ ወጣቶች የሚገኙበት፤ ፓለቲካዊ ቁውስ በፈጠረው ችግር ህፃናት በጨቅላ ዕድሜያቸው በሀገሪቱ ጎዳናዎች ሁሉ የስቃይ ህይወት እየገፉ ይገኛሉ። የወጣቱ ተስፋና የስራ ዕድል አማራጭ በግዴታም በውዴታም ውትድርና ብቻ እየሆነ ነው። በአከባቢው በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት የወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እንዱስትሪና ሌሎች ተቋማት ባለመሰራቱ ችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ አባብሶታል። ነገር ግን ያንን የህዝብ ስቃይ ለመንግሥት የሚያድስ ተወካይ የለም።

ከዚህም የተነሳ ሴቶችና ወንዶች አስቸጋሪውን ሞትና ስቃይ ፊትለፊት እየተጋፈጡ ወደተለያዩ ስደት ሀገር ያቀናሉ። ዕድል ቀንቷቸው ከሞት ተርፈው ወደ አረብ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት የገቡ የተቀረውን ቤተሰቦቻቸውን በቻሉት መጠን ያግዛሉ። ነገር ግን ጉዳያቸው በተወካዮቻቸው አይነገርም።

የህዝብ መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት አብዛኛው ይሰራል ተብሎ ቃል የተገባ ይሁን መሠረት ድንጋይ የተጣለበት ፕሮጀክት ከማስጀመሪያ ፎቶ አላለፈም። ህዝብ እየሆነና እየታዘበ ባለው ተስፋ ቆርጠው “Nu Deriyaaba Xoossi erees (የእኛን ነገር ፈጣሪ ያውቃል)” በሚል ዝምታን መርጧል። በተቃራኒው በየደረጃው ህዝብ ስም ስልጣን የያዙ እንዳልሰሙ ዝምታን መርጧል።

ሌላው ደግሞ በአከባቢው ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር ምን ለውጥ ያመጣል ተዘንግቶ በግልጽ እየታየ ባለው ሁኔታ በክልሉ በየትኛውም አከባቢ ተግባራዊ ያልሆነ በተለየ መንገድ በዎላይታ የአመራሮች ሹም ሽረት መብዛት፣ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለአከባቢው ልማት በጎ ሚና ከመጫወት ይልቅ በኢኮኖሚ ሆነ ፓለቲካ ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማድረስ ያመዘኑ እንደሆነ ይነገራል። ቢሆንም ይሄንን ፖለቲካዊ ሴራ የሚረዳ ተወካይ ህዝቡ አጥቷል።

በተለይም የብሄሩ ተወላጆች ከፌደራል፣ ከክልል እንደሁም ከዞን ጀምሮ በተመደቡበት ኃላፊነት ቦታ ተረጋግተው እንዳይሰራ በመደረጉ ይባስ ብሎ “ደቡብ ኢትዮጵያ” በሚል የተዋቀረ ትንሹ ክልል ከመደራጀቱ በፊት በትልቁ ከ56 ብሄር ብሄረሰቦች በላይ አብሮ በአንድ ክልል በነበረው አደረጃጀት ውስጥ ከህዝብ ቁጥርና ተያያዥ እውነታ አንፃር በመንግሥትና በገዢ ፓርቲ መርነትም ተገቢ ውክልናና ተጠቃሚነት የነበረ ቢሆኑም አሁን በትንሹ ክልል የነበረውን ጭምር በማጣት ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ቀውስ የተጋለጠው ከዚህ የሚመነጭ እውነታ እንደሆነ አይካድም። ነገር ግን ለምን የሚል የህዝብ ተወካይ አይታይም።

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በተለይም ባለፉት ስድስት አመታት በዞኑ የተከሰቱ ቁልፍ ጉዳዮችን በእያንዳንዱ ቀን ትዝብትና ይፋዊ ዘገባ እያደረሰ ያሳለፈ በመሆኑ በአከባቢው ፖለቲካዊ ትርጉም ባለው ደረጃ የቀጠለው ወከባና የውዝግብ አጀንዳ ማብዛት ጀርባ ማን አለ የሚለውን ጥያቄ ትተንና ወደኃላ በመጣውና በሄደው ላይ እንዲሁም በግለሰቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ትንታኔ ከመስጠት ይልቅ እውነተኛ ለህዝብ የሚበጀው አካሄድ የትኛው ቢሆን ይሻላል በሚለው ትኩረት ያደርጋል።

በግልጽ እያየን ባለነው ሁኔታ አንፃር በመሀል ደግሞ አንገብጋቢ ጥያቄ ያለውና ለልማት የተጠማ ህዝብ ይጎዳል የልማት አጀንዳውም በሰጡት አጀንዳ ይሸፍናል። ከዚህ ሁሉ ከእልህ የቡድን ጨዋታና ተንኮል ሴራ አካሄድ ለመውጣት በፊት የነበሩ ልዩነቶችን በውይይትና እርቅ ዘግተው ያለጥላቻ በጋራ ተጋግዘው መሄድ እንደሚያዋጣ ብዙዎች ይስማሙበታል።

ህዝቡ በእልህ የቡድን ጨዋታ ምክንያት “በፓለቲካ አካሄድ ልዩነት ምክንያት ብቻ ዳርና ዳር ሆነው የሚገኙ ወገኖች ወደ አንድነት፣ መደማመጥ፣ መተባበር እንዲሁም በጋራ ጉዳይ በሆኑ የህዝብ የልማት ፍላጎቶች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡና በአንድነት በመሰለፍ በጎ ሚና ሊወጡ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ሰብሳቢዎችን በእግዚአብሔር ተስፋ አድርጎ እየጠበቃቸው ይገኛል።

ያም ሆነ ይህ፦ አሁን አሁን በአከባቢው እየተስተዋለ ያለ ኢፍትሃዊነትን ለመታገልና በህዝብ ውግንና በአደባባይ ለመናገር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ በህዝብ ወክልና የገቡ ከላይ የተዘረዘሩ 13ቱም ተወካዮች እንዲሁም በየደረጃዉ ያሉ ተወካዮች የህዝብ አደራ ወደጎን በመተው ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ብቻ በማድረግ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣታቸውና ህዝብ በተፈነበት ወቅት ሆን ብለው ዝምታን በመመረጣቸው በታሪክ ተጠያቂ ይሆናሉ።

ለአብነትም በዛሬው ዕለት በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስብሰባ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን አመራሮችና አላማቸውን የሚቃወሙ ቡድኖች ጫና እና ከፍተኛ ስቃይ ተቋቋመው የህዝባቸውን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ ባደራጁት ፖለቲካ ፓርቲ አማካይነት አሸንፎ ፓርላማ የገቡ የቁጫ እና የዛይሴ ህዝብ ተወካዮች የግል ክብርና ጥቅም ሳያስቀድሙ ለወከላቸው ብሄር ያለምንም ማንገራገርና አለመፍራት በአከባቢያቸው የሚስተዋሉ ችግሮችን በአደባባይ ሲናገሩ በተቃራኒው ዘርፈብዙ ችግር የተጋረጠበት የዎላይታ ህዝብ የወከሉት ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ጥቅማቸውን መርጠዋል።

በመሆኑም በየደረጃው ለህዝብ ጥቅም የሚሟገቱ ተወካዮች እንዲፈጠሩ የመጣንበት መንገድ በህዝብ ዘላቂ ጥቅምና ዋስትና ሲባል ሁሉም ከእልህ፣ ከጠልፎ ከመጣልና ከሴራ ፖለቲካ ወጥቶ ሕዝቡን ማዕከል በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ስምምነት እንዲፈጥር እንዲሁም ህዝቡ ላይ የተጋረጠበትን አደጋ በጋራ ቋሞ መመከት እንዲቻል አስቀድሞ የውስጥ አንድነት ማጠንከርና ከጎረቤት እና ከሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች የነበረውን ጤናማና ዘመናትን የተሻገረ መስተጋብር አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያስፈልጋል።

በመሆኑም የዎላይታ ታይምስ እንደ አንድ በአከባቢው ጉዳይ ላይ በቅርበት እንደሚሰራና ኃላፊነት እንደሚሰማው ሚዲያ ከላይ በአከባቢው የታዘበውን መሠረታዊ ችግር የጠቆመ ሲሆን የአከባቢው ተወላጅ መብት ተሟጋቾች፣ ፓለቲካኞች፣ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የእወነተኛ ተወካይና የህዝብ ውግንና ያላቸውን ማጣት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ተወያይተውና በጋራ ተመካክረው መፍትሔ ማበጀት እንዳለበት ጥሪ ያቀርባል። #Ethiopia #Wolaita

እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች- በ #WolaitaTimes ሚዲያ, ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🙏

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው