1000023854

“ህዝብን እንዲወክሉ ተመርጠው የተከበሩ የሚል ስም አግኝተው ራሳቸውን የወከሉ ተወካዮች” የመረጣቸው ህዝብ ጥያቄ አልቆ ነው እንዴ ዝም ያሉት ? በሚቀጥለዉ ምርጫ ምረጡኝ እያሉ ሊመጡ ነው? እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት በዚሁ በፓለቲካ ወጌሻ መደበኛ ዝግጅት ላይ የተጠቀሱና ተያያዥ ጉዳዮችን ዘርዘር አድርገን እናወጋለን። ተለፍቶበት የተዘጋጀ ነውና በትዕግሥት ያንብቡ!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በአሁኑ ወቅት ዎላይታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13 ተወካዮች አሏት፥ ለምንድነዉ እነኝህ ተወካዮቻችን ምንም አይነት ጥያቄ የማያነሱት? የመረጣቸዉ ሕዝብ ጥያቄ የለዉም ይሁን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ሕዝቡማ ብዙ ጥያቄ አለዉ፣ ተወካዮቹ አይጠይቁም እንጂ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዎላይታ ተወካዮች፣ በጣም አቅም ያላቸዉም ቢኖሩም ዝም ብለዉ ወንበር ያሞቃሉ። ሕዝቡ የፌደራል አመራር በመጣ ቁጥር የሚጠይቃቸዉ ጥያቄዎች ለምን በእንደራሴዎቹ እንደማይጠየቅ አይገባኝም፣ የሐገሪቷ አቅጣጫ ላይምኮ ድርሻችንን መወጣት አለብን።

በአምስት አመት ቆይታ ፓርላማ ላይ አንዴም የሕዝቡን ጥያቄ የማያነሳ ሰዉ ቀጥሎ ምረጡኝ እያለ ወደ ሕዝቡ መምጣት የለበትም፣ ሕዝቡ ወንበር አሙቁልኝ ብሎ ነዉ እንዴ የመረጣቸዉ። በክልል ምክር ቤቶችም በተመሳሳይ ኢ_ፍትሐዊ ነገሮችን መሞገት ያስፈልጋል። በእዉነቱ ዝምታቸዉ የጤና አለመሆኑ ነው የሚሰማኝ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት የተለዬ የሚደርስባቸዉ ጫና ይኖርባቸዉ ይሆን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በርግጥ ሁሉም የብልጽግና ፓርቲ አባላት ናቸዉ። ከዛ ባለፈ ግን ባለፉት ሶስት የሕዝብ ተወካዮች የሥራ ዘመናት በተለይ ለዎላይታ ተወካዮች ጥሩ አይመስሉኝም። ከነሱ በፊት ለምሳሌ አለምጸሐይ ኤልያስ ተመራጭ ሆና የዎላይታን የክልል ጥያቄ በቀጥታ ጠይቃ ነበረ፤ ፓርቲው ባለፈዉ ምርጫ አላወዳደራትም። በክልል ምክር ቤትም ያኔ በጋራ ከምክር ቤቱ እራሳቸዉን እስከማግለል የደረሱ ተወካዮች ነበሩ፣ በዛም ላይ ብዙ ሰዉ ተቀይሯል። ሳስበዉ እነኚህ ነገሮች ከጠየቃቹ ይህ ይደርስባቿል የሚል መልዕክት አስተላልፎላቸዉ ይሆን እላለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደረጃ ብቻ ማየቱ ነጥለን ማየቱ ጎዶሎ አይሆንም?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሱማ ነዉ እንጂ፣ ጎዶሎ ነው። ሶስቱ የመንግስት አካላት አሉ፣ ሕግ አዉጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ ከዚህ ዉስጥ እንግዲህ ሕግ አዉጪ ነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት። ምሁራን check and balance የሚሉት ነገር አለ፤ አንዱ ከአንዱ ጋር ያለዉን ስልጣን የመከፋፌል እና አንዱ አንዱን የመቆጣጠር መሥተጋብር ሲገልጹ ፣በእኛ ሐገር እንግዲህ ተፋልሶ አለ።

የሕግ አስፈጻሚዉ ግምባር እየተነበበ ነው የተቀሩት የሚሰሩት። አስፈጻሚው አካል በከፍተኛ ሁኔታ ጠቅልሎ የሚገዛበትና ለይስሙላ የሚሰበሰብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም የሕዝብን ጥያቄ በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ማሰማት እራሱ ከፍተኛ ጥቅም አለዉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የአስፈጻሚውን አካል ፈላጭ ቆራጭነት ማጋለጥ ከተቻለም መገደብ ስለሚቻል የሕዝብን ዉክልና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። 13ቱም ተወካዮቻችን 5ቱንም አመት አንዳች ሳይተነፍሱ፣ ቆይተዉ በሚቀጥለዉ ምርጫ ምረጡኝ ሊሉን አይገባም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስብሰባ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን አመራሮችና አላማቸውን የሚቃወሙ ቡድኖች ጫና እና ከፍተኛ ስቃይ ተቋቋመው የህዝባቸውን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ ባደራጁት ፖለቲካ ፓርቲ አማካይነት አሸንፎ ፓርላማ የገቡ የቁጫ እና የዛይሴ ህዝብ ተወካዮች የግል ክብርና ጥቅም ሳያስቀድሙ ለወከላቸው ብሄር ያለምንም ማንገራገርና አለመፍራት በአከባቢያቸው የሚስተዋሉ ችግሮችን በአደባባይ ሲናገሩ በተቃራኒው ዘርፈብዙ ችግር የተጋረጠበት የዎላይታ ህዝብ የወከሉት ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ጥቅማቸውን አስቀድሞ ዝምታ መርጠዋል። በሌላ በኩል በአከባቢው የምንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ኃላፊነት እየተወጡ አይደለም። እንደው የቁጫ እና ዘይሰ ተወካይ አይነት የህዝብ ውክልና ያላቸውን እንዴት እንዴት ማስመረጥ ይቻላል? እስኪ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅለል ያለ እይታ ቢያጋሩን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የዘይሴ እና የቁጫ ተመራጮች ያደረጉት ተጋድሎ ታሪካዊ የሚባል ነው። በአንጻሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ የማለባበስና ሕገመንግሥትን አለማክበር የተንጸባረቀበት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ብዙ ስለሆንን መደፍጠጥ እንችላለን ማለታቸዉ ሕገመንግሥት የማያከብር አባባል ነው። ተቋማትን የናቀ አባባል ነው፤ ሕዝቦች ሲደፈጠጡ ተቋማት ጸጥ ብለዉ ይመለከታሉ? የፌደሬሽን ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸጥ ብለዉ ማየት የለባቸዉም።

ሌላዉ እነኝህ የዘይሴና የቁጫ ተወካዮች ያሳዩን ነገር፣ የተወሰነ ተቃዋሚዎች በፓርላማ መቀመጫ ካገኙ እራሱ መፍጠር የሚችሉትን ተጽዕኖ ያሳዬ ነው። በዎላይታም ቢሆን ሕዝቡ በእዉቀት እና ማስረጃ ላይ ተመሥርተዉ የሚሟገቱለትን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መምረጥ እንዳለበት ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች- በ #WolaitaTimes ሚዲያ, ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🙏

Ethiopia #southethiopia #Wolaita

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው