1000024014

የዘንድሮው ብሄር ብሄረሰቦች ቀን የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ታፍነው በሚኖሩበት ዞን እንደሚከበር መገለፁ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩ ተነግሯል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት ካለበት ከተማ ውጪ የሚካሄደውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቀ ቢሆንም የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ታፍነውና ማንነታቸው ተደፍጥጠው በሚኖሩበት ዞን ለማክበር መዘጋጀቱ “ከበዓሉ ዋናው አላማ ጋር የሚጋጭና ማንነታቸው እንዲታወቅ ለሚታገሉ ንቀት ያሳየ ድርጊት ነው” ሲሉ በአከባቢው የሚገኙ ነባር ብሄር ተወላጆች ቅሬታ አሰምቷል።

ሰሞኑን ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ በሚከበረው ለ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቀን በዓል አከባበር ቅድመ ዝግጅት ስራዎች ዙሪያ የአቢይ ኮሚቴ የስራ ተልዕኮ መገምገሙ ተገልጿል።

ይሄው ለመጀመሪያ ጊዜ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት ካለበት ከተማ ውጪ የሚካሄደውን 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተመለከተ ሁሉም ለበዓሉ ስኬት የበኩሉን እንዲወጣም ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በየአመቱ ብሄር ብሄረሰቦች የየራሳቸውን ባህልና እሴት እርስበርስ እየተለዋወጡ እንዲሁም ህገመንግስቱ ያጎናፀፋቸውን ማንነት እያንፀባረቁ የሚያከብሩት ይሄው በዓል በተቃራኒው ዘንድሮው የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ታፍነውና ማንነታቸው ተደፍጥጠው በሚኖሩበት ዞን ለማክበር መዘጋጀቱ “ከበዓሉ ዋናው አላማ ጋር የሚጋጭና ማንነታቸው እንዲታወቅ ለሚታገሉ ንቀት ያሳየ ድርጊት ነው” ሲሉ በአከባቢው የሚገኙ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰብ ተወላጆች ቅሬታ በማሰማት ላይ መሆኑ ተነግሯል።

ተወላጆቹ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም “በጋሞ ዞን ለዘመናት ማንነታቸው ባልወከሉት ታፍነው የቆዩ ቁጫ፣ ቦሮዳ፣ ጋንታ፣ ዶርዜ፣ ዘይሴ፣ ካምባ፣ ቦንኬ፣ ኦቾሎ ብሄረሰቦች የልዩ ወረዳና ዞንነት መብት በማፈን ተስፋችንን አጨልሞታል” ስሉ ሁኔታውን በምሬት አስረድተዋል።

አንድ የዘይሴ ብሄር ተወላጆች በጉዳዩ ዙሪያ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት “አሁንም ማንነታችንን በህግ እንዳይከበር በተግባር ሰው መስሎ በስውር ሲያፍኑ ሲጮቁኑ የነበሩ ግለሰቦች ስልጣን ላይ እንዲቀጥሉ መደረጉ መንግስት የማንነት ጥያቄ እንዲመለስ በፌደሬሽን ምክርቤት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ለማኮላሸት ምቹ ሁኔታ እንዳያገኙ ሁሉም ማንነቱን የሚወድ ኢትዮጵያዊያን ከጎናችን እንዲሰለፉ” በሚል ተማፅነዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ላይ ደግሞ “ለዘመናት በጉራጌ እና ካምባታ ዞን ስር የማንነት ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ የጠምባሮ፣ ቀቤና፣ ማራቆ ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተከብሮላቸው በልዩ ወረዳ እንዲደራጁ ምክርቤቱ መወሰኑ ክልሉ ከጅምሩ የማንነት ጥያቄ ላላቸው ምላሽ በመስጠት አብሮ ተከባብሮና ተቻችሎ ለመኖር ለማደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት አኩሪ ውሳኔ በመሆኑ ተደስተናል” ስሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

አንድ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህገመንግስት አርቃቂ ኮምሽን አባል የነበሩት ግለሰብ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደገለፁት የቁጫና የዘይሴ ልዩ ዞን ጥያቄ በምክርቤቱ እንዲፀድቅ ሁሉም ነገር ካለቀ በኃላ በምን አይነት ሁኔታ እስካሁን ለውሳኔ መቅረብ እንዳልቻለ አስረድተዋል።

አባሉ አክለውም “በተለይም በጋሞ ዞን ለዘመናት ማንነታቸው ታፍነው የሚገኙ የራሳቸው ማንነት ያላቸው ብሄረሰቦች መዋቅር ጥያቄ በክልሉ ብሄረሰቦች ምክርቤት ስብሰባ ላይ የማንነት ጥያቄያቸው ከተመለሰ በኃላ በቀጣይ ምክርቤት ስብሰባ ላይ ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ቢሆንም ያ ሳይሆን ቀርቷል” ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በዞኑ የሚገኙ ነባር ብሄረሰቦች ማንነታቸው እንዳይታወቅ ከፍተኛ ስቃይና አፈና እየተካሄደ መሆኑን በመግለፅ በራሳቸው ማንነት የሚኮሩ እንዲሁም የጭቁን ብሄረሰቦች ማንነት እንዲታወቅና መብታቸው እንዲከበር የሚታገሉ በሙሉ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አለማክበሩ ክልሉ ከድሮ ሴራኞች እጅ ያልወጣ ፀረ ፈዴራልሲም በሆኑ ሰዎች አስተሳሰብና ሴራ ተደራጅተው መብታቸውን የነፈጉትን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከጎናቸው ሊሰለፉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።

  • እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች
    -ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
    -ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🙏 #WolaitaTimes ሚዲያ

Ethiopia #southethiopia

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው