1000024485

“ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ዳዉሮ፣ ኮንታ እና ጎፋ ወንድማማቾች ህዝቦች ናቸው” ለምን አሉ? ዳዉሮና ኮንታ በሌላ ክልል ዉስጥ የተደራጁት ለምንድነዉ? በሰማይም በምድርም አንገናኝም ያሉት ጭምር ዳግም አልኖርም ባሉበት ክልል ከፍተኛ አመራር እንዲሆን ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በችኮላ ወደ ሌላ መዋቅር የሄዱትን ይመልሱት ይሁን ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ክልል የተበታተኑ ህዝቦችን ወደ አንድ ሊያሰባስቡ ነው ? እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽና ቁምነገሮችን ይዘናል ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ👇

ብዙ ተለፍቶበት የተዘጋጀ ነውና በትዕግሥት ያንብቡ!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ፕሮፌሰር እንግዲህ እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ በድጋሚ እንኳን ደህና መጡ እንላለን። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ እንግባ።

እንደሚታወቀው በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ስለ ኦሞቲክ ሕዝቦች ማለትም ዎላይታ፣ ጎፋ፣ ዳዉሮ፣ ጋሞ እና ኮንታ በግል አመለካከታቸዉ ደረጃ አንድነትን እንደሚመኙ ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የእርሱዎ አስተያዬት ምንድነዉ ? ጠቅላይ ምኒስትሩ ፍላጎታቸዉ አንድነት ከሆነ በጋራ በአንድ መዋቅር ለማደራጀት እንዴት አቃታቸዉ? በእርሳቸዉ ዘመነ ስልጣን ከእነዚህ ሕዝቦች አንድነት አንጻር የተወሰኑ ዉሳኔዎች የሚያቀራርቡ ናቸዉ ወይስ የሚያለያዩ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በጣም ጥሩ እና ብዙ የአካባቢው ምሁራንም የዉይይት መነሻ ማድረግ የሚገባቸዉን ጥያቄ አንስተሐል። ምናልባት የሐገራዊ ምክክሩም አንዳች እልባት ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይም ይመስለኛል። ወደ ግል አስተያየቴ ስመለስ፣ እነኝህ ሕዝቦች ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ዳዉሮ፣ ኮንታ እና ጎፋ ወንድማማቾች መሆናቸዉ ግልጽ ነው። ከቋንቋ መቀራረብ እና ያለ አስተርጓሚ ከመግባባት ጀምሮ፣ በባህል፣ በስነልቦና በእምነት እጅግ ተቀራራቢ መሆናቸዉም ይታወቃል።

ታሪካዊ ትስስርና መከባበራቸዉም የላቀ ባይሆን በዚህ ጠባብ መልከአምድር ላይ በጋራ አይኖሩም ነበረ። እዉነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ መንግስታት እነኝህን ሕዝቦች ለማቀራረብ ሳይሆን ለማራራቅ ብዙ ሰርተዋል፥ አንድነታቸዉ በብዙ ኃይሎች የሚፈለግ አይመስለኝም። ለማቀራረብም በዎጋጎዳ ጊዜ የተደረገዉ ሙከራ ከከሸፈባቸዉ ምክንያቶች አንዱ በአካባቢው ለዘመናት የፈጸሙትን ጭቆና ጥልቀት በሚገባ ያልተረዳ አካሄድ ይመስለኛል።

በተጨባጭ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሕዝቡን አንድነት ከፈለጉ ግን ትርጉም ያለዉ እንቅስቃሴ ማድረግ ይችሉ ነበር። ለምሳሌ ዳዉሮና ኮንታ በሌላ ክልል ዉስጥ የተደራጁት ለምንድነዉ? በነጻነት የመደራደርና የመወሰን ስልጣን ቢኖራቸዉ ወደሌላ ክልል የሚሄዱ አይመስለኝም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወንድሞቻችሁን ጥላችሁማ አትሄዱ ቢሉ የሚደመጡ ይመስለኛል። አንድ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሐላላ ኬላ ከዎላይታ እራስን ለመከላከል የተገነባ አስመስለዉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወሩት አፍራሽ ንግግር ነበረ።

እርሳቸዉ በዎላይታ ምንም ሳይሰሩ በእነዚህ አካባቢዎች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መሥራታቸውም ጤናማ መልዕክት ያለዉ አይመስለኝም የአካባቢው መልማት ልማታችን መሆኑ ቢታወቅም። ምናልባት በቀጥታ ስለዚህ ጉዳይ እርሳቸዉ ሐሳብ የሰነዘሩት በጋሞ ዞን የሚታዩ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄወችን አስታከዉ ነውና እነዛ ጥያቄዎች በሕገመንግስቱ በተቀመጠዉ አግባብ መመለሳቸዉን እኔ እንደመበታተን አልቆጥረዉም።

ምክነያቱም እነኝህ ሕዝቦች የማንነት ጥያቄያቸዉ ተመልሶም ቢሆን ከአጠቃላይ የሕዝቦቹ ተቀራራቢነት አዉድ ዉጪ አይሆኑም፣ ይልቅ የማንነት ጥያቄዎቹን ማፈን ብዙ ቁስሎችን ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች በሕገመንግስቱ አግባብ ተመልሰዉ ሕዝቦቹ ቢመካከሩ ብዙ ነገሮችን ለማስተካከል አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በተጨባጭ ለእነዚህ ሕዝቦች የሚጠቁሙት አቅጣጫ ምንድነዉ? ተነጥለዉ በጋራ ክልል ይመስርቱ ? ወይስ ምን የሚሉት ነገር አለ ? ሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በጋራ በአንድ ክልል መኖራቸዉ የሚፈጥረዉ ችግር አለ ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ምሁራን ጥልቅ ዉይይት ማድረግ አለባቸዉ ባይ ነኝ። በግሌ ግን አንደኛ ዳዉሮና ኮንታ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መመለስ አለባቸዉ ባይ ነኝ፥ በዛዉም ደግሞ ሌሎች ብሔርና ብሔረሰቦች ጋር በጋራ መኖራቸዉ ችግር የሚፈጥር አይመስለኝም። ከዛ በተረፈ በድርድር ክልሉን እንደገና በጋራ ማቋቋም አለብን።

ይሄንን ወንድማማቾች ክልል የሚመራ አመራር ደግሞ አሁን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየታየ የሚገኘው አይነት ለራሱ ብቻ እያለ ሌሎች የሚገባቸውን እንዳያገኙ የሚያደርግ አድሏዊነት የሞላበት ሳይሆን ሁሉንም ህዝቦች እንደየሚገባቸው በፓለቲካው፣ በኢኮኖሚው እና ማህበራዊው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኝነት ያለው መሆን ይኖርበታል።

እነኝህ ሕዝቦች ከቋንቋ እና ባህላቸዉ ሳይነጠሉ በጋራ ከተማ መገንባት የሚችሉ ይመስለኛል። ለምሳሌ የአሁኑ የአስተዳደር እና የፖለቲካ ማዕከል የሆነችዉ እንዲሁም ከሕዝቦቹ ብቻ ሳይሆን ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዞኖች በሕዝብ ቁጥር የሚበልጠዉ ዞንም ዋና ከተማ የሆነችዉን ዎላይታ ሶዶን በጋራ በሁለተኛ ደረጃ ከተማነት በባህር ዳርና መቐለ ልክ ቢያለሙ ሁሉም ተጠቃሚ ናቸዉ፣ ባህልና ቋንቋቸዉን አስጠብቀዉ ሊኖሩባት ይችላሉ።

ዎላይታ፣ ዳዉሮ፣ ጋሞ፣ ጎፋ እና ኮንታ ህዝቦች በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሥነ ልቦና አንድነታቸዉ ጉልሕ ስለሆነ በሌሎች ቦታዎች እንደሚታዬዉ ሰዶ ማሳደድ አይኖርም፥ በደምብ ዉይይት ተደርጎ የሚደራጅ መዋቅር ዘላቂ ነዉና።

ሌላዉ እነኝህ አካባቢዎች በጋራ በመቀናጀት የመሠረተ ልማት ችግሮቻቸዉን በተፋጠነ ሁኔታ ሊፈቱ ይችላሉ፤ የቱሪስት መስህቦቻቸውን በጋራ በማስተዋወቅ አንዱ ጋ የመጣ ቱሪስት ሌላዉንም እንዲጎበኝ በማድረግ የተሻለ ገቢ ማግኘት ይቻላል። ሕዝቦቹ አንድነታቸዉን በማጠናከር በተናጠል የሚከብዷቸዉን ችግሮች በጋራ በቀላሉ ሊፈቱ ይችላሉ።

በኢኮኖሚ በፖለቲካም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ተጨባጭ ለዉጥ በማምጣት ከሐገሪቷ የድርሻቸዉን እንዲቋደሱ በር ሊከፍትላቸዉ ይችላል። በአንጻሩ ግን በተናጠል በመጓዝ በዞንነት አቅም ተወስነዉ ይቀራሉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ይህንን ወንድማማችነት በጽኑ አለት ላይ ለመመሥረት ድርሻዉ የማን ነው ? ከማን ምን ይጠበቃል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ሕዝቡኮ በየቤቱ የሚወያይበት ርዕስ ነው። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አደባባይ አወጡት እንጂ ስለዚህ ጉዳይ፤ አሁን የእናንተ ሚዲያ እነዚህን ሕዝቦች ጉዳይ አጀንዳ ማድረጉ ጥሩ ጅምር ነው። ከነዚህ አካባቢዎች የወጡ ምሁራን በያሉበት ሊወያዩበት ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ የተናገሩት ነገር አያስጠይቅም ማለት ነዉ።

ስለዚህ በድፍረት መድረኮችን በማዘጋጀትም መወያዬት ያስፈልጋል። ሶስተኛ ወገን ሳይገባ ዉይይቶች በአካባቢው ምሁራን ዘንድ መደረግ አለባቸዉ። የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨረስቲና የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲም በዚህ ጉዳይ ላይ በጋራ መድረኮችን ማዘጋጀት አለባቸዉ።

ይፈራ የነበረዉ መንግስት ነው፥ ስለዚህ መንግስት ስለሕቦቹ አንድነት ጥሩ አመለካከት አለኝ ካለ፣ የተቀረነዉ በዚህ ዙሪያ ጥረቶች የማናደርገዉ ለምንድነው ? መስነፍ አያስፈልግም ይህ ታሪካዊ እድል ነው። ይህ ወንድማማች ሕዝብ በጋራ የሚኖርበትን ቀመር በጋራ ማበጀት አለበት።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በዎጋጎዳ ጊዜ የተቀሰቀሰዉ ግጭት በቅርቡ ከዎላይታ ጋር አንደራጅም ያሉም አመራሮች ነበሩና መሰል ችግሮች እንዳይደገሙ እና አፍራሽ እንቅስቃሴዎች እንዳይከሰቱ ምን ጥንቃቄ መደረግ አለበት ይላሉ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ያለ በቂ ምክክር እና ስምምነት ማንም ማንም ላይ የሚጭነዉ ነገር መኖር የለበትም! ከዛ በተረፈ ግን ያደሩ ብሶቶች የሚፈነዱበት እድልም እንዳይሆን የተሳሳቱ እርምጃዎች መኖር የለባቸዉም። ለምሳሌ በዎጋጎዳ ጊዜ የዎላይታ ሕዝብ ያመጸዉ በቋንቋ ምክንያት ብቻ አልነበረም፣ ያደሩ ብሶቶችም ነበሩት።

አሁንም ምናልባት ክልሉ ሲመሠረት የዎላይታ ፖለቲከኞች በሙሉ ስምምነት ያልተሳተፉበት ምክንያት በዎላይታ ተወላጆች ላይ በሌሎች አካባቢዎች የተደረገዉ መጠነ ሰፊ ብሔር ተኮር ጥቃት ነው። ስለዚህ ሕዝቦቹ ያደረ ብሶት ሊኖራቸዉም ስለሚችል በጥንቃቄ በጋር እና አሳታፊ የምሁራን ዉይይትና ድርድር ነው ነገሮች አቅጣጫ መያዝ ያለባቸዉ። በመጨረሻ ካስፈለገ እስከ ሕዝበ ዉሳኔ ድረስ መሔድ አለበት።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ የሕዝቦቹ አንድነት ምን አይነት ቢሆን ይሻላል የሚለዉን ትተን ግን በግርድፉ የሕዝቦቹ አንድነት ምን ፋይዳ የሚኖረዉ ይመስልዎታል ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በጣም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። በጋራ የጋራ ትልቅ ከተማ ሊሰሩ ይችላሉ፣ በጋራ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ይችላሉ፣ በጋራ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ድርሻቸዉን ከሐገሪቷ ማግኘት ይችላሉ፣ አንዱ ከአንዱ ጋር በመደጋገፍ አንዱ ለአንዱ ከቆመ ለጥቃትና ለመገለል አይዳረጉም። በእዉነቱ ፋይዳዉ በጣም ትልቅ ነው፣ በጋራ ከተሠራ በጣም ለሕዝቦቹ የተሻለ እድል ከፊታቸዉ አለ። በግል የዎላይታ፣ የጋሞ፣ የዳዉሮ፣ የጎፋና የኮንታ አንድነትን በጥልቅ ሕዝባዊ ዉይይት ምክክር እና ስምምነት እንዲደረግ እደግፋለዉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

#Ethiopia #southethiopia #Wolaita #gamo #gofa #Kontazone #Dawuro

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ዘገባ ነው