በደቡብ ኦሞ ዞን የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኃይለማርያበደቡብ ሮማን ፋውንዴሽን አስታወቀ።


ፋውንዴሽኑ ከአጋር አካላት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በደቡብ ኦሞ ዞን #ሐመር፣ በ#ናፀማይ እና #ቱርሚ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ 10 የአርብቶ አደር ትምህርት ቤቶች የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህ ወቅት የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ እንደገለጹት ድጋፉ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚከናወኑ የትምህርት ስራዎችን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ፋውንዴሽኑ ያደረገው በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት የተዘጋጁ 1 ሺህ 725 የማጣቀሻ መጽሐፍት፣ ስክሪፕቶና ወረቀት፣ የህትመት ቁሳቁሶች እንዲሁም ስድስት ሞተር ሳይክሎች መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ለተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የሚያገለግሉ የተለያዩ የማብሰያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
ድጋፉ በአርብቶ አደሩ አከባቢ በትምህርት ዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣና የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚረዳ አስረድተዋል።
በተለይ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበልና ተሳትፎ ለማሳደግ ፋውንዴሽኑ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው በዚህም በዞኑ ከ2 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶቻቸው ቁርስና ምሳ እንዲመገቡ ማድረግ መቻሉን አውሰተዋል።
ፋውንዴሽኑ በአጠቃላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ጥራትና ተሳትፎን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እየደገፈ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ይህንነ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ አስታውቀዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ጋያ ፋውንዴሽኑ በዞኑ በትምህርት መስክ ጠንካራ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ፋውንዴሽኑ በዛሬው ዕለት በዞኑ ለሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች ላደረገው የቁሳቁስ ድጋፍም አመስግነዋል።
የኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ባለፉት አራት አመታት በተለያዩ የትኩረት መስኮች ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቅሷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል። #Ethiopia #debubomo