“ከዎላይታ ጋር በሰማይ በምድር አንገናኝም” ያሉ ካድሬዎች ዎላይታ ላይ የጀመሩት የበቀል በትር ምክንያት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባታል ተብሏል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች መገለጫ እየሆነ የመጣዉ ሴራ ትንተና፤ ጠልፎ መጣልና የዜሮ ድምር ውጤት ነው፡፡
በእውነተኛ የግንኙነት መሰረት ላይ በመቆም ስልጣንን ተቀብሎ ህዝብን በቅንነትና በግልፅኝነት የማገልገል ባህል በጣም ደካማ በመሆኑ በሀዝቦች መካከልም አለመተማመን እና እርስ በእርስ መጠራጠር ውስጥ እንዲገቡ ካደረገ ሰነባብቷል፡፡
ይህ ደግሞ ለተመሳሳይ አላማ ህብረተሰቡን አንቀሳቅሶ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ፈታኝ ከባቢን ፈጥሯል፡፡ ይህም ደግሞ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰዉ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ እንቅስቃሴዋ የተገደበና ወደ መፍረስ የምትመራ ክልል እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ይህችን በተፈጥሮ ፀጋ የተቸረች ክልል በመፍጠርና በመፍጠን፤ በመፍጠንና በመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ወቅታዊና የተከማቹ ተግዳሮቶችን ተሻግራ ለመጓዝ ይቸግራታል፡፡
በክልሉ የአመራሩ በጠልፎ መጣል የፖለቲካ ባህል፤ በእግር ጎታች እና ከተለመደው ለመውጣት ያለው ዳተኝነት ከኤሊ ጉዞ ወጥታ የእንቁራሪት ዝላይ እንዳይኖራት አድርጓታል፡፡
ገና ከተመሰረተ አንድ ዓመት ተኩል ያልሞላው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመፍረስ አደጋ እየገጠመው መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ለከልሉ የመፍረስ አደጋ ዋናው ምክኒያት ደግሞ ክልሉ አሁን በተደራጀው ቅርጽ እንዳይደራጅ ስሰሩ የነበሩ የሴራ ፖለቲካ አራማጅ ኃይሎች ተጠራርተው የፊት አመራር መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ሲዳማ ክልል ከቀድሞ ደቡብ ብ/ብ/ህዝቦች ክልል ተለይቶ ከወጣ በኃላ የቀሩ አከባቢዎችን በጋራ ለማደራጀት የፌዴራል መንግስት ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጭ ስልጣን ለመያዝ በሚመች መንገድ ክልል ለማደራጀት የሞከሩ ኃይሎች ክልሉ አሁን በተደራጀው ቅርጽ እንዳይደራጅ ሴራ ፖለቲካ መሠራቱን ገልጸዋል።
በተለይ ደግሞ “ከዎላይታ ጋር አንደራጅም” የሚለዉ ዎላይታ ጠል ፖለቲካ አሁን ከፊት ሆኖ ክልሉን እየመሩ ባሉ አመራሮች እስከ ቀበሌና ጎጥ ድረስ መሠራቱን በማስታወስ ገልጸዋል።
በዚህም የወቅቱ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የአሁኑ የክልሉ ከተማና መሠረት ልማት ቢሮ ኃላፊ ከዎላይታ ውጪ ከሌሎች ጋር እንደራጃለን የሚል አጀንዳ በመቅረጽ በካድሬዎቹ አማካኝነት እስከ ጎጥ ወርዶ ከማስተማሩም በተጨማሪ ሚዲያዎችን ጠርቶ የሰጡት መግለጫ ዛሬም በዩቱብ ይገኛል ብለዋል።
የአሁኑ ርዕሰ መስተዳድር ሴራ የሚጀምረዉ ክልሉ በአድስ መልክ ከመዋቀሩ በፊት ገና ፕሮጀክት ጽ/ቤት ሲቋቋም ጉራጌንና ዎላይታን በማግለል ነበር፡፡ የአደረጃጀት ጥያቄ አልፋና ኦሜጋ ህዝብ ሆኖ እያለ የህዝብ ቁጥር ማንሳት ሀጥያት አድርጎ የሚያስቡ ግለሰቦችን በመፈለግ የተለያዩ ኮሚቴ አባል ሆኖ እንድሰሩ አደረገ፡፡
በኮሚቴ ዉስጥ ለሚሳተፉ እንደ አስተዋጽኦ ልክ ሹሜት እንደሚሰጥ ቃል ተገባላቸዉ፡፡ለአደረጃጀት ዉሳኔ ልያግዙ ይችላሉ ብሎ ለገመታቸዉ ለተወሰኑ የፌደራል ባለስልጣናት፣ ለአብዘኛዉ ክልል አመራሮች እና ለሁሉም በሚባል ደረጃ በደቡብ ኢት/ያ ዉስጥ ለሚገኙ የዞን/ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪና ፓርቲ ኃላፍዎች በአርባምንጭ ከተማ የመኖርያ ቤት እንድያገኙ ተደርጓል፡፡
የዎላይታ ሪፍረንዴም እንዲሰረዝ ተደርጎ ብዙም ሳይቆይ በአቶ ብርሃኑ ዘዉዴ በኩል ዎላይታ ሪፍረንዴሙን ለራሱ ብቻዉን ክልል ለመሆን ሆን ብሎ ያደረገዉ ስለሆነ ቀሪዎቻችን ወደ ክልል ምስረታ መግባት አለብን የሚል የሴራቸዉን ዉጤት ይፋ አስደረጉ፡፡
በመቀጠልም ለክልሉ ማዕከልነትም ዉድድር ሳያስፈልግ በዉሳኔ እንድሆንና ለዛ እንድያግዝ ቀደም ተብሎ በተሰጡ ስጦታዎችና ቃል በተገቡ ሹሜቶች የሰከሩ አካላት ነጠላ ዜማቸዉ እንድዘፍኑ ተደረገ፡፡ ሆኖም ግን በፌደራል መንግስት ብርቱ ክትትልና ድጋፍ አሁን ያለዉ አደረጃጀት ከኔ ዉስንነቱም ተፈጠረ፡፡
በአደረጃጀቱ አልሳካ የተባለላቸዉን በበቀል ለማካካስ የሚያስችል የስልጣን ክፍፍል እና የተቋማት ድልድል እንደፈለጉ አደረጉ፡፡
ከጋሞ ዞን ዎላይታ ጠል አመራሮች ጋር ጥብቅ ግንኙነት የፈጠሩት የወቅቱ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የአሁን የክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የውሃ ማዕድንና እነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አዳኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ ፊት “ከዎላይታ ጋር በሰማይ በምድር አንገናኝም” እስከማለት ያሰሙትን የዎላይታ ጠልነት የነበረውን አገላለጽ በማሳያነት አንስተዋል።
በተጨማርም ከቀድሞ ደቡብ ኦሞ ዞን አሪ ዞንን ለመገንጠል በማሰብ ተዋልደዉና ተዋደዉ ለዘመናት አብሮ የኖሩ ህዝቦችን በማፋጀት በርካታ ንፁሃን ዜጎች በጠራራ ፀሀይ እንድሞቱና እንድፈናቀል እንድሁም ዎላይታ ከህወሀት ጋር አብረዋል በሚል ፈጠራ ወሬ 38 ንፁሃን ዜጎች እንድገደሉ ያደረገዉ የቀድሞ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የአሁኑ የክልሉ ብልፅግና ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ለማሳያነት ማቅረብ ይቻላል፡፡
በዚህም ከዎላይታ ውጭ ክልሉን ለማደራጀት ተማምሎ የሰሩ እና ያልተሳካላቸው የዎላይታ ጠል ጽንፈኛ ካድሬዎች እነሱ በማይፈልጉት መንገድ በብልጽግና እሳቤ የተደራጀውን ክልል ለመምራት ተጠራርቶ ራሳቸውን የፊት አመራር አድርገው ማደራጀታቸውን ገልጸዋል።
የአሁኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይህን ተግባር በመፈጸም የአምበሳ ድርሻውን ይወስዳል ብለዋል፡፡
በዚህም እነሱ በማይፈልጉት መንገድ የተደራጀውን ክልል አፍርሰው ቀደም ስል አስበውና አቅደው በመስራት ያልተሳካውን ከዎላይታ ውጭ ክልሉን አፍርሰው ለማደራጀት እየሠሩ መሆናቸውን አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል ሲሉም አስረድተዋል።
ዎላይታ ሶዶ የክልሉ የፖለቲካና አስተዳደር ማዕከል ቢሆንም ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም ሶዶ እንደማይቀመጥና ሁሉም ስብሰባዎችና ስራዎች አርባምንጭ ላይ እንድሆን መደረጉን እንደማሳያነት አንስተዋል።
አርባምንጭ ላይ የምገነቡ ግንባታዎች የበጀት ምንጩ የክልል ሆኖ ግን በጀቱን በቀጥታ ባልሆነ መንገድ ለጋሞ ዞን በመስጠት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው ለዚህም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር 500 ሚሊዮን ብር በአደባባይ ቃል ገብቶ በመስጠት እየሰራ መሆኑንም አብራርቷል።
በተመሳሳይ መንገድ ከክልሉ ዋና ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ወጥቶ በአርባምንጭ ከተማ ይከበራል የተባለው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ወጪው ከክልሉ ካዝና ሆኖ የጋሞ ዞን ተወላጅ የሆኑ የክልሉ አመራሮች ብቻ ተደራጅቶ እንድሰሩ መደረጉንም ክልሉን የጋሞ ዞን መዋቅር አድርጎ እየሠሩ መሆናቸውን ጠቅሷል።
የዚህ ሁሉ ችግር ክልሉ አሁን ከተደራጀበት ከብልጽግና እሳቤ አደረጃጀት ፈርሶ ቀደም ሲል ዎላይታ ጤል ካድሬዎች ባቀዱት ልክ ለማደራጀት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ይህ ሴራ በፌደራል መንግስት ጣልቃ ተገብቶ ካልተስተካከለ ክልሉ ላይ የመፍረስ አደጋ መጋረጡን የፓርቲዉ ከፍተኛ አመራሩና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል ምሁር በሰጠው ማብራሪያ ገልጸዋል።