1000025832

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥንቅር ነው

የኦሮሞ ፌደራል ስርዓት አቀንቃኞች ሃዲዱን ስተው ይሁን ? የፈደራል ስርዓት እንዲከበር የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉትን በመዘንጋት ታሪካዊ ስህተት አይሆንም ? እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽና ቁምነገሮችን ይዘናል ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ👇

ብዙ ተለፍቶበት የተዘጋጀ ጥንቅር ነውና በትዕግሥት ያንብቡ!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ፕሮፌሰር እንግዲህ እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ በድጋሚ እንኳን ደህና መጡ እንላለን። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ እንግባ።

በዎላይታ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ጠንካራ ፌደራሊስት እንደሆኑ ይታወቃል፥ ለመሆኑ በሐሳብ ደረጃ የፌደራል ስርዓቱ በዎላይታ አካባቢ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘበትን ምክንያቶች ምን ምን እንደሆኑ ቢጠቅሱልን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አሁን ኢትዮጵያ ለምትከተለዉ በዋናነት ቋንቋ እና ማንነትን መሠረት ላደረገዉ የፌደራል ሥርዓት በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ነገሮች መሀከል፦

👉ሐገሪቷ የሚንሊክን ወረራ እና ጭፍጨፋ ተከትሎ በጉልበት ተፈጥራ በጉልበት መቀጠሏ ጋር ተያይዘዉ የተፈጠሩ ችግሮችን በአሳታፊነት ለመፍታትና የጋራ ሐገር ለመፍጠር በተለይ የእርስ በርስ ጦርነቶችን ለመግታት።

👉 የአስተዳደር መዋቅሮች ማዕከላዊነትን ተከትለዉ ነባራዊዉ እና ታሪካዊዉ የሕዝቦች አሰፋፈር እንዲሁም ስነ ልቦና ሆን ተብሎ በሚቃረንና የገዢውን ክፍል ዘላለማዊ ስልጣን እና ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲመች ተደርጎ እየተዋቀረ በመኖሩ ያንን ችግር ለመፍታት።

👉 የብሄሮች ቋንቋ ከጨዋታ ዉጪ የሚሆንበትን አወቃቀር መከተልና አይደለም በማዕከላዊ መንግሥት ተቋዋማት ፣ በየመንደሩም ቢሆን የሥራ ቋንቋ አለመሆናቸዉ (ቱርጁማን)፣ የፈጠረዉን ችግር ለመቅረፍና ዜጎች ከነቋንቋና ማንነታቸዉ ኢትዮጵያዉያን የሚሆኑበትን አዉድ ለመፍጠር።

👉 ኢትዮጵያ ከዜጎቿ ገሚሶቹ ልጆቿ፣ ቀሪዎቹ ጠላቶቿ፣ አንዳንዶች ደግሞ አጃቢዎቿ ሆነዉ መኖራቸዉን ለማስቀረትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ( በself rule )፣ እንዲሁም የማዕከላዊዉን መንግስት ስልጣንን እንዲጋሩ ( በshared rule ) ከእኔ አዉቅልሐለዉ ባይ ተንኮለኛ እና ወገንተኛ አሰራር ለማላቀቅ።

👉 ሕዝቦቿ ዉግንና በሌላቸዉ ጨቋኞች በየዘመኑ ሚዛን ለከፋ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ገፈፋ መዳረጋቸውን በማስቀረት የተሻለች ሐገር ለመፍጠር።

👉 የመሬት ቅርምትና ወረራ እንዲሁም ጭሰኝነት በብሄር ተለይተዉ መፈጸማቸዉ በተጨማሪ ሕዝቦች በአገዛዞች ሲስተናገዱበት እና ሲታዩበት የነበረዉ የተለያዬ ደረጃ ስለነበረ ያ የፈጠረዉን ልዩነት በዴሞክራሲያዊ አግባብ ለማስተካከል።

👉 በመንግሥታት ይፈጸም የነበረዉ የብሄር ጭቆና ከአገሪቷ አቅም ( Economic አቅም ) ከሚቀርበዉ ሁሉ እኩል ተቋዋዳሽነት ሆኖ ስላልኖረ ያንን ለማረቅ።

👉 ዜጎች በሐገሪቱ አቅጣጫ ላይ በሚጋሩት ስልጣን በኩል፣ የወሳኝነት ሚና ያላቸዉ ባለድርሻ እንዲሆኑ ለማስቻል ተቋማት ብዝሐነትን ታሳቢ አድርገዉ እንዲገነቡ ለማስቻል።

የብሄር የጭቆናዉን ቀምበር ለመሥበር ይካሄዱ የነበሩ ሐገሪቷን እስከማፍረስ በማለም የተደረጉ ትግሎች፣ በመፈቃቀድ ላይ በሚመሰረት ፌደራላዊ አንድነት እንዲስተናገዱ ለማስቻል እና የመሳሰሉት ምክንያቶች እንደሆኑ ግልጽ ነው።

በምክንያታዊነት ተመሥርተዉ በማስረጃ አስደግፈዉ ኢትዮጵያን እንደቀኝ ገዥ ከሚመለከቱ እስከ መለስተኛ የባህልና ቋንቋ መከበርን ጨምሮ የፖለቲካ ዉክልናን የሚጠይቁ ሐይሎችን ጥያቄ በመመለስ ሐገሪቷን ለማስቀጠልም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ፈደራላዊ አንድነት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም ጭምር መሆኑ እሙን ነው፤ በሐቀኝነት በሙላት ባይተገበርም።

ዎላይታንም በዚህ ማዕቀፍ ካየን ብዙ ነገሮች እጅግ በጣም አሳዛኝና የሚያስቆጭ ሆኖ እናገኛለን። ዎላይታ ከሚኒሊክ ወረራ በፊት ሐገር ነበር። እጅግ በጣም ጠንካራ ሐገር ለመሆኑ የሚንሊክን ጦር ስድስት ጊዜ ማሸነፉ እና ወረራዉን ለሰባት ዓመታት ተቋቁሞ ከመዝለቁ ባሻገር በተቻለ መጠን ከአለም ሥልጣኔ ጋር ለመራመድ ያለ ከልካይ ይታትር የነበረ ሐገርና ሕዝብ ነበር።

ለዚህ ማሳያነት ዳልቦ የነበረዉ ስልክና ራሱ የሕዝቡ የፈጠራ ዉጤት የሆነዉን ማርጯ የሚባለዉን የመገበያያ ገንዘቡን ብቻ መጥቀስ በቂ ይመስለኛል። ከጥጥ ልብስን የፈጠረ የመጀመሪያ ሕዝብ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል። ዎላይታ ለሚኒሊክ ወረራ ዝም ብሎ አልገበረም። ሐገርነቱን ለማክሰም እና በባርነት ሊገዛዉ የመጣዉን ወራሪዉን የሚኒሊክ ጦር ለተከታታይ ሰባት ዓመታት በተካሄዱት እጅግ በጣም አሰቃቂ ጦርነቶች መሀል ስድስቱን በማሸነፍ ሐገርነቱን ማስጠበቅ ቢችልም በሚያሳዝን ሁኔታ በሰባተኛዉ ተሸንፎ ሐገርነቱን አጥቷል።

ከጦርነቱ በኃላ እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ በሚኒሊክ ጦር ተፈጽሞበታል፥ በባርነት ተቸርችራል፣ እንደ ከብት እየተነዳ መጥቶ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተበትኖ በባርነት ለመኖር እና ለስልቀጣ ለመጋለጥ ተገዷል። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ይህ ጀግናና ታላቅ ሕዝብ አንድም ቀን ባርነትን አሜን ብሎ ተቀብሎ አያዉቅም።

እራሱ ንጉስ ጦና ቆስሎ ከተማረከ በሁዋላ በተሰጠዉ ድጋሚ በሞግዚት ስር በተሰጠዉ ሹመት ተጠቅሞ ሕዝቡን ከአስከፊዉ የሚኒሊክ አገዛዝ ለማላቀቅ ድጋሚ አመጽ አካሂዶ ከሽፎበታል፤ ቀሪ ዕድሜዉን በግዞት ለማሳለፍ ተገዷል። ይህ በዘመናዊት ኢትዮጲያ የመጀመሪያ የተደራጀ በሐገረ መንግስቱ ላይ የተቃጣ አመጽ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል። አጭበርባሪ የታሪክ ጸሐፍት ከሚሉት በተቃራኒው።

በአድዋ ጦርነት ከተሰለፉ የዎላይታ ጦር መሪዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ሐጤሮ ሐኒቼ ሁዋላ ላይ ባስነሳዉ ግርግር ጨቋኙን ስርዓት ማስደንገጥ ቢችልም እሱንና ወገኖቹን ለከፋ መከራ ዳርጎ ወገኖቹን ለትግል አነሳስቶ ቢያልፍም ዋነኛ ህልሙ ሳይሳካለት ቀርቷል። ታዲያ እስከዛሬ ለሚደረገዉ የዎላይታ ሕዝብ ትግል እርሾ መሆኑ ሳይዘነጋ። ከዛን ጊዜም ጀምሮ የዎላይታ ሕዝብ ሲታገል ነው የኖረዉ ለብሔራዊ ክብር፣ ሕልዉና እና ለመብቱ።

የፌደራል ሥርዓቱን ጨምሮ አሁን ላለዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሠረት ነው በሚባለዉ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅትም ሰለሞን ዋዳ እና ለንደን ካንኮ የተባሉ ሁዋላ ላይ በደርግ የተቀጩት የዎላይታ ብርቅዬ ልጆች ግምባር ቀደም ተሳታፊ መሆናቸዉ በብዙዎች ተጠቅሷል። ከዛ በተረፈ በዎላይታ አካባቢ ለዘመናት በተንሰራፋው ድሕነት ምክንያት የመከላከያ ሠራዊት አባል መሆን ብዙዎች የሚመርጡት የሥራ ዕድል ከመሆኑም ጋር ተያይዞ የሐገሪቷ አገዛዞች ብዝሐነትን ላለማስተናገድ ወይንም በሸፍጠኛ መንገድ በማስተናገድ በሚፈጥሯቸዉ የእርስ በርስ ጦርነቶችም ልጆቹ በማያምኑባቸዉ ጦርነቶች ሲማገዱ ኖረዋል።

መሰል ጦርነቶችም እንዲቀሩ፣ የፖለቲካ ጥያቄ የሚያነሱ ሕዝቦች በጨቋኝ አገዛዞች ሲቀጡ የኖሩበት ዘመን እንዲያበቃና እንዳይመለስም ጭምር ነው፤ የፌደራል ሥርአቱ በዎላይታ ድጋፍ ያገኘዉ ማለት ይቻላል። ይሄ ማለት ግን የፌደራል ስርዓት ከዎላይታ አንጻር በሙላት ካለመተግበሩም በተጨማሪ በከፊልም እንዲተገበር የተደረገዉ በዎጋጎዳ ጊዜ በተደረገ ብርቱ ትግል ነው። ከዛ ባለፈ ሥርዓቱ እንከን የለሽ ነው የሚል ገታራ አቋም ግን በዎላይታ በኩል የለም ማለት ይቻላል። ብዙ ማሻሻያዎች ያስፈልጉታል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ከሕገመንግስታዊነት አንጻር በኢሕአዴግ ዘመን የነበሩ ክፍተቶች እንደነበሩ እና በዋናነትም በብዙዎች ትግሎች ሲካሄዱ የነበረዉም ሕገመንግሥቱ እንዲከበር እንደነበረ ይታወሳል፣ የአሁኑ መንግስት ሕገመንግሥቱን ባልቀየረበት ሁኔታ በሪፎርም የሕዝቡን ጥያቄዎች እመልሳለሁ እያለ ሐገሪቷ በዚህ ደረጃ እንዴ በታሪኳ ያላየችዉ እልቂት እና መተላለቅ ሰፈነባት ? በዛዉም አያይዘዉ የነዚህ ሁሉ ችግሮች መነሻ ሕገመንግሥቱ ነው የሚሉ ሰዎች አሉና ለዚህ አስተያየቶት ምንድነው ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔ ሕገመንግሥቱን እንደ ቁራንና መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ነዉ ብለዉ ከሚያምኑ ተርታ ባልሰለፍም መከበር እንዳለበት ግን በጽኑ አምናለሁ። በኢትዮጵያ ታሪክ ሰላም የሚባለው በአንጻራዊነት ይህ ሕገመንግሥት የተተገበረበት የኢሕአዴግ ዘመን እንደሆነ ታሪክ ምስክር ነው።

ወደ ዘመነ ብልጽግና ቀዉሶች ስንመለስ፣ በመጀመሪያ ለለዉጡ መነሻ የሆነዉ የ #Oromoprotest ምክንያታዊና ብሶቶቹም በተጨባጭ የኢሕአዴግ ኢ_ሕገመንግሥታዊ አካሄዶች ምክንያት የተፈጠረ ነው።

የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን መነሻ ይሁን እንጂ ብሶቱ ያደረ ነው። የኦነግ ተገፍቶ ከሽግግሩ መዉጣት፣ በጦሩ ላይ የተወሰደ ኢ_ሞራላዊ እርምጃ (ካምፕ የገባ ሠራዊት ላይ መተኮስ)፣ የኦሮሞ ተማሪዮችንና ሊህቃንን ማሳደድ (በስዬ አብርሃ ገለጻ የእስር ቤቶችን ቋንቋ ወደ ኦሮምኛ መለወጥ)፣ ኦህዴድም ቢሆን ከኦሮሞ ሕዝብ ብዛት አንጻር በተለይ በፌደራል መንግስት ቁልፍ የሚባሉ ሥልጣኖችን (የፖለተካ፣ የመከላከያ እና የደኅንነት ስልጣን) አለማጋራት፣ አዲስ አበባ ፊንፊኔነቷን ጠብቃ አለመገንባቷ፣ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ከአዲስ አበባ በጉልበት እንዲነሳ የተደረገበ እና ለይስሙላ የተመለሰበት አግባብ፣ እነዚህ እና የመሳሰሉ ምክንያት የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላዉ የበለጠ ተጨቁኛለሁ ብሎ ያምን ነበር፣ በአንጻራዊነት እዉነት እንደነበረዉም መካድ አይቻልም።

እናም ይህንን ሐቀኛ እና ምክንያታዊ የሕዝብ ብሶት የኦሮሞ ሊህቃን የመሩበት መንገድ የተሳሳተ ይመስለኛል፣ በተለይ የኦሮሞ ሕዝብ የፌደራል ስርዓቱን ታግሎ ማምጣቱንና የትግራይ እና የዎላይታም ሕዝብ በመርህ ደረጃ ከኦሮሞ ወገኖቹ ጋር ብዙ ነገሮችን የሚጋራ መሆኑን የዘነጉ አካሄዶች ተፋፋሙ። በተለይ በሕወሓት የደኅንነት ና በአንዳንድ የመከላከያ አመራሮች የሚወሰዱ ጸረ_ሕገመንግሥታዊ እርምጃዎች ማፈናቀልና የመሳሰሉት ነገሩን አባባሱት።

በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የኦሮሞ ሊህቃን ኦሮ_ማራ የሚባል ጥምረት ለመመስረት ብዙ የቀኝ አክራሪ ኃይሎችን መቀስቀሻዎች ገዙ። የሚገባኝን ድርሻ ላግኝ ሕገመንግሥቱ ይከበር የሚለዉ የሕዝቡ ትግል ተጠልፎ እገሌ ይዉረድ፣ እገሌ ካልጠፋ፣ #ወያኔ ካልጠፋ ማለት ተጀመረ። በተለይ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተመቻቹ ዴሞክራሲያዊ የዉይይት መድረኮችም ብዙ ቁም ነገሮች ቢነሱበትም አሁንም የመጠፋፋት ሱስ የተጠናወታቸዉ ኃይሎች እንቅፋትነት እርሳቸዉ ለሐገር ሰላም ብለዉ ስልጣን ለቀቁ።

የመጣዉም መንግስት ሪፎርም አደርጋለሁ በሚል ተስፋ እንዲሁም የቀድሞ መንግስት የሰራቸዉን ሥራዎች ሁሉ በመወንጀል ብዙ ደጋፊ አሰባሰበ (ያጠፉትንም፣ የተበደሉትንም፣ ሽብርተኞችንም ጭምር ያካትታል) ፣ በተለይ ኦሮ_ማራ የሚለዉ አሰራር ሁለቱም በየፊናቸዉ ያቀዱትን አቅደዉ ያዝረከረኩትን አዝረክርከዉ የሚያረጉት እንቅስቃሴ ሐገሪቷን በብርቱ ጎድቷል፣ ከፋፍሏል፣ አገዳድሏል።

በተለይ የትግራይ እና የዎላይታ ሰዎችን እንደ ጠላት በመፈረጅ የሚካሄደዉ ጸረሕገመንግሥታዊ አካሄድ ሐገሪቷን ለእንዲህ አይነት ዉድቀት እና ድቀት እንደሚዳርግ ብዙዎች አልተገለጠላቸዉም ነበረ። ከተቋማት በዘረኛ መንገድ ሰዎችን መቀነስ ሐገርን ለዉድቀት ዳርጓል። የኦሮማራ ኃይሎች በጋራ እና በተናጠል የጸረትግራይ ኃይሎች የኩሽ ኃይሎች፣ በንግድ የተሻለ ተሳትፎ ያላቸዉ ኃይሎች (የኢኮኖሚ አሻጥር እንዳይሰሩ ሊሆን ይችላል) እና ጸረዎላይታ ኃይሎችን አሰባስበዋል።

ስልጣን በዚህ ጸረሕገመንግሥታዊ አግባብ ለማከፋፈል ሞክረዋል፣ ይህም ተቋማትን አሽመድምዶ ሕዝቡን ከፋፍሏል፣ በሐገሪቷ ከመቸዉም ጊዜ በላይ ጥርጣሬና ጥላቻን አንግሷል፣ social fabric በጣጥሷል። በተለያዩ አካባቢዎች ግጭትና መፈናቀሎችን፣ መንግስታዊ ሽብሮችን እንዲሁም የእርስ በርስ ጦርነቶችን ወልዷል። በተለይም ኦሮማራ አጋር አድርጎ ያሰባሰባቸዉ የአማራና የኦሮሞ ኃይሎች በመፎካከር በሚወስዷቸዉ እርምጃዎች በመንግሥት አመራሮች መሐል ከፍተኛ ጥርጣሬ ዘርቶ እስከማገዳደልም ደርሷል።

ይሕ ሕግ የማይገዛዉ አመራር ና አሰራር፣ በተለይ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም ልዩነቱ ተካርሮ ብዙ የአማራ አመራሮች በመተፋታቸዉ ፣ክልሉ ወደ ጦር አዉድማነት ተቀይሯል። እንግዲህ ይሕ ከሕገመንግስቱ ያፈነገጠ የብልጽግና አካሄድ የፈጠረዉ ቀዉስ ነው። መርሕና ሕግ የማይገዛው ብልጽግና የኤርትራንም ጉዳይ በሴራናበደባ በመያዙ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዳለች።

የትግራይም ጦርነት ከመጋረጃ ጀርባ የሚደረጉ ወንጀሎች አደባባይ የተሰጡበት ነው የነበረዉ፣ የሕወሓት እብሪትና ወንጀል፣ የሻዕቢያ ጣልቃ ገብነት፣ የጦሩ ሪፎርም ክሽፈት፣ የሕግ አስፈጻሚዉ አካል አግላይነት፣ የአማራ ክልል የሕገመንግስት ጥሰት፣ የመንግስት ሚዲያዎች እና ጀሌዎቻቸዉ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያደረጉት የጅምላ ፍጅት ቅስቀሳዎችን ማንሳት ይቻላል።

ከላይ የጠቀስናቸዉ የተለያዩ አካላት የሰሯቸዉ ወንጀሎች ሁሉ ሕገመንግስቱን በመጣስ የተደረጉ ናቸዉ ማለት ይቻላል። በተለይ ትግራይ ይህ የተለያዩ ብሔሮችን የሚያሳትፍና ሥልጣን የሚያጋራ ሥርዓት ለማምጣት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላለች፤ የብልግና አካሄድ ይህንን መስዋዕትነት ከቁብ የሚቆጥር አልነበረም።

ዎላይታም ቢሆን በአንጻራዊነት ከተተገበረዉ ፌደራል ሥርዓት ከሌሎች የደቡብ ሕዝቦች ጋር በግምባር ቀደምነት ተቋዳሽ የሚሆንበት እድል ያገኘዉ ብዙ መስዋዕትነት ካስከፈለዉ የዎጋጎዳ ትግል በሁዋላ ነው፤ ብልጽግና ይህንንም ከቁብ አይቆጥረዉም በአካሄዱ። እነኝህ በብርቱ ትግል በኢትዮጵያ ሐገረመንግስት ግምባታ አቅጣጫ ላይ የበኩላቸዉን የሚያበረክቱበትን መንገድ የተጎናጸፉ ሕዝቦችን ነጥሎ ማግለል፣ ለሐገሪቷ ውድቀት መነሻ ነው ብዬ አምናለሁ። ኢትዮጵያ የበለጠ አካታች መሆን ሲገባት ብልጽግና የሰራዉ የበቀልና የንቀት እንዲሁም የጥላቻ መንገድ ሐገሪቷን እዚህ ቀዉስ ዉስጥ ከቷታል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ይህ መንግስት ሐቀኛ የፌደራል ሥርዓት ተግብሬአለሁ ይላል እና እንዳሉት የፌደራል ሥርዓቱን ትግበራ በብርቱ የሚሻዉ የዎላይታ ሕዝብ ከዚህ መንግስት የሚፈልገዉን አግኝቷል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በአጭሩ አላገኘም። ጭራሽ እንደጠላት ተፈርጇል፣ ተጠቅቷል። ለምሳሌ በፈለገዉ የሐገሪቷ ክፍል የመኖር መብቱ ተገፎ ተጠቅቷል፣ የክልል ጥያቄዉ ታፍኗል፣ በአዲሱ ክልል ያለ ድርድር በጫና እንዲገባ ተደርጓል። ከሥልጣን አንጻርም ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረ ብሔር ደህና የሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንኳን እንዳይመራ ተደርጓል። በፈደራልም፣ በክልልም ሚዛናዊ ዉክልና ተነፍጓል (የትግራይም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው )።

በዚህ መንግስት ዘመን በሐገሪቷ አቅጣጫ ላይ በዉሳኔ የሚሳተፍበት መስመር ተዘግቷል። ይህ ሁሉ ወድመትና እልቂት ሲካሄድ መተንፈሻ መንገድ እንዳይኖረዉ ተደርጓል። በነገራችን ላይ 40ሺ የዎላይታ ልጆች ከመከላከያ የተቀነሱት በትግራይ በሚካሄደዉ ጦርነት ላይ ጥያቄ የማያነሳ ጦር ለመፍጠርም ጭምር ነዉ፣ ሕወሓት በመከላከያ ተስፋ ከቆረጠባቸዉ ምክንያቶች አንዱ ያ ነው። ሌላዉ የትግራይ ተወላጆች ቅነሳና የጀነራል ሰአረ መኮንን ግዲያ ሊሆን ይችላል።

በዚህ በጉልበት በተመሠረተዉ ክልል እንኳን የመጀመሪያ ከተማ ተብሎ የነበረዉን መልሶ ብልጽግና ክዶታል፣ ክህደት ልማዱ ስለሆነ ብዙም አይገርምም። ስለዚህ በፍጹም ፍትሐዊ የፌደራል ሥርአቱ አተገባበር ሰፍኗል የሚባለዉ ተራ ቀልድ ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደዉ በግርድፉ የዎላይታ ሕዝብ በሕገመንግስቱ ላይ ቢደረግ የሚደግፋቸዉ ማሻሻያዎች ምን አይነት ናቸዉ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በጣም ብዙ ሊሆን ይችላል፣ እንደየ ሁኔታዉ ሰጥቶ በመቀበል መርሕ የሚቀየሩ አቋሞችም ስለሚኖሩ እሱን እንተወዉና ግን የእኛ ጥያቄ ከማሻሻያዉ በፊት ያለዉም ቢሆን በሐቀኛነት ይተግበር ነው። ፈላጭ ቆራጭነት እና አግላይነት እንዲሁም ለሕገመንግስት መንግስት አለመገዛቱ ከባድ ጥፋት አድርሷል።

አግላይነት እዉቀጥ እንደ ቁምጣ የሚያጥራቸዉን ሊህቃን የበቀል ጥም ሊያረካ ይችል ይሆናል፤ ሐገሪቷን ግን እያፈራረሰ ነው። ኢትዮጵያ ዉስጥ አንዱ የሠራዉን ሌላዉ የሚያጠለሸዉ ከዚህ መገለል ከሚፈጥረው የበቀል ስሜት የተነሳ ነው፣ የመበቃቀል አዙሪት ማብቃት አለበት፤ ዛሬ የሚሰራ ተንኮል ነገ ሌላ ተበቃይ ትዉልድ ይፈጥራልና። ማናችንም ማናችንንም በዘላቂነት ማንበርከክ አንችልምና የመናናቅ ፖለቲካ ቢያበቃ ይበጀናል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏