በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ አመራርና ተቋማዊ የእድገት ጉዞ ወደለየለት አዘቅት እየተንደረደረ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው የተቋሙ ሠራተኞች ገለጹ።
“ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ አመራር እና ተቋማዊ የእድገት ጉዞ ወደለየለት ከፍተኛ አዘቅት እየተንደረደረ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ታማኝ የመረጃ ምንጮች ለዎላይታ ታይምስ ገልጸዋል።
በየኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ የሚመራው የአመራር ስብስብ “ስትራቴጂክ ጉዳዬች ላይ ትኩርት ሰጥቶ ከመስራት ይልቅ ለግል ጉዳዬቻቸው ቅድምያ የሰጡ ናቸው” ብለዋል የመረጃ ምንጮች።
ዶ/ር ጉቼ ጉሌ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንቶች በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በተጠባባቂነት የአመራር ምደባ ከተሰጣቸው ጊዜ ጀምሮ አንዳች ፋይዳ ያለው ተግባር ሳይሰሩ አንድ ዓመት ማለፉን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ሌት ተቀን እረፍት ለሚነሳቸው እና ከእንቅልፍ ለሚያባንናቸው «የሙዝ እርሻ ልማት እና ንግድ ሥራ» እንጂ የዩኒቨርሲቲው ዋና ዋና ተግባራት ለሆኑት መማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት እንዲሁም አስተዳደራዊ እና ተቋማዊ የልማት ሥራዎች ግድ እንደማይላቸው የቅርብ ሰዎቻቸው ጭምር ይናገራሉ።
የኢዜማው አለቃ እና የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ምልምል የሆኑት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ እርሳቸውም እንደ አለቃቻው ነፍጥ አንግባው ጫካ ባይገቡም ግንባር ቀደም አፍቃሪ ኢዜማ መሆናቸውንና በአርባ ምንጭና አካባቢው ባሉ ሰፋፊ የሙዝ እርሻ ጫካዎች ሙዝ ሲተክሉ እና ሲያስተክሉ የሰነበቱ “ምሁር ልማታዊ ባለሀብት” እንደሆኑ ይወራል።
ግለሰቡ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሀ ሀብት ምህንድስና መስክ በመምህርነት ቆይታቸው ከመንግስት ሰዓት ሰርቀውም ሆነ ትርፍ ሰዓታቸውን ተጠቅመው በግል ሀብት ማፍራታቸው በአንዳንድ ወዳጆቻቸው ሚደነቅ እና የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም፤ በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ግን ስለሙዝ እርሻ እና የንግድ ስራዎቻቸው ስለሚቀላጠፍበት ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ከማውራት በስተቀር እንደ ተቋም በሁሉም ስትራቴጂያዊ የሥራ ዘርፎች አቅደው የፈጸሙት ተግባራት የለም፣ እንዲፈጸምም አመራር አልሰጡም፤ ይህም ተቋሙን በአፈጻጸም ከሚጠበቀው በታች እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል በማለት የመረጃ ምንጮቻችን በምሬት ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በግብርናው የልቀት ማእከል ለመሆን ራእይ መያዙን የዘነጉት ዶ/ር ጉቼ በተቋም ደረጃ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ የግብርና ልማት መልካም ስራዎች እንዲቆሙ በማድረግ «የግል እርሻ ልማት ስራ» ላይ ብቻ መጠመዳቻው ግን እጅጉን እንዳሳዘናቸው እና የተቋሙ መጻኢ ዕጣፈንታ እንደሚያሰጋቸው ምንጮቻችን ለሚዲያችን ገልጸዋል።
በኢዜማው አለቃ እና በትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ መታመናቸውን በሚያሳብቅ መልኩ ማንም ምንም እንደማያመጣ እና ከኃላፊነት እንደማይነሱ በተደጋጋሚ በገሀድ ሲናገሩ እንደሚደመጡ እንዲሁም “ከህግ አግባብ ውጪ ያለውድድር” የተሰየሙበት የፕሬዝዳንትነት ሹመት የማያስጨንቃቸውና ግድየለሽ መሆናቸው ተቋሙን ከያዘው ራእይ እና ተልዕኮ በማላቀቅ ከተወዳዳሪነት ውጪ እያደረገው ይገኛል ብለዋል ምንጮቻችን።
“ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ አመራር እና ተቋማዊ የእድገት ጉዞ ወደለየለት አዘቅት እየተንደረደረ መሆኑ እንዳሳሰባቸው ለሚዲያችን የገለጹት ታማኝ የመረጃ ምንጮቻችን፤ ግለሰቡ ግን አሁንም በግል ውጤታማ የሆኑበትን የሙዝ እርሻ ልማት እና ንግድ ሥራዎችን በተቋም ደረጃ ለማስፋት ዕቅድ መያዛቸውን ጠቁመዋል።
ለዚሁ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዲሆን በት/ት ሚኒስቴር እና በገንዘብ ሚንስትር ትዕዛዝ በቦዲቲ፣ በአበላ አባያ እና በአረካ ከተሞች የሕንጻ ግንባታቸው ተጀምሮ እንዲቋረጡ የተደረጉ የካምፓስ ማስፋፊያ ይዞታዎችንና አዲሱ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ተጠባባቂ ሆነው በዩኒቨርሲቲው ከተመደቡ ጊዜ ጀምሮ ስራ ያቆሙ የምርምር ማዕከላትን በኪራይ በመጠቀም መሆኑ ተመላክቷል።
የዳውሮ ታርጫ ካምፓስን ጨምሮ ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠሩ ነባር ግንባታዎች ሆን ተብሎ ትኩረት እንዲነፈጋቸው እና እንዲቋረጡ መደረጉ ሳያንስ ገንዘብ ሚኒስትርን ሎቢ በማድረግ አዲስ ከሚጀመሩት የግንባታ ፕሮጀክቶች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት መመዝበር እና የግል ሙዝ እርሻን ማስፋፋት ሌላኛው ስውር የሀብት ምንጭ እንደሚሆን ተጠባቂ ነው ብለዋል መረጃውን ያጋሩን አካላት።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተቋም አፍራሽ ስውር ተልዕኮ አንግበው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ግድ የለሽ ተግባራቸው ያሳያል ያሉት የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ መረጃ ምንጮቻችን፤ በትምህርት ሚኒስትር የከፍተኛ አመራሮች ምደባ እና ስምሪት መመሪያ መሰረት አስቸኳይ ውድድር ወጥቶ ህግ ተፈጻሚ እንዲሆንና ፕሬዚዳንቱ ወደሚወዱት የሙዝ እርሻ ልማት እና ንግድ ሥራቸው እንዲመለሱ የመረጃ ምንጮቻችን አስተያየት ሰጥተዋል።
በተግባር አፈጻጸም ተቋሙን የኋሊት እየጎተቱ ያሉ ምክትሎቻቸው፦ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በበርካታ ብልሹ አሰራር የሚታሙት የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተክሌ ሌዛ “በደባ እና በተሰረቀ የሴኔት ድምጽ” የያዙትን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዲለቁ፤ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አክበር ጩፎ እንዲሁም የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዘውድነህ ቶማስ ተጠባባቂ ሆነን መስራት ከጀመርን ስድስት ወር አልፏል ያለ ውድድር ወደ ሙሉ ይጽደቅልን” የሚሉትን የቦርድ ተማጽኗቸውን ትተው በጊዜ ወደ መማር ማስተማር ሥራ እንዲመለሱ እንዲሁም የተቋሙ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ምሁራን ሁሉ ለህግ ተፈጻሚነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ከባለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ በተቋሙ ሲፈጸም የቆየውን ከፍተኛ ምዝበራ እና ተቋም የማዳከም ስውር ሴራ በተጨባጭ መረጃዎች አስደግፈን “የምርመራ ዘገባ” በተከታታይ የምናቀርብ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ልናሳውቃችሁ እንወዳለን።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
#Ethiopia #southethiopia #Wolaita_sodo