1000026762

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥንቅር ነው

በየጊዜው የራሱን ህገመንግስት ያጎናጸፈውን ተቀዳሚ ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተገዶ በህግ ሳይሆን በከባድ መስዋዕትነት እያረጋገጠ የመጣው የዎላይታ ህዝብ የጊዜ ጉዳይ ቢሆን እንጂ ሳይመለስ የሚተኛ ይመስልዎታል ? ሀገር የነበረ ዞንነቱን እንኳን ታግሎ ያስከበረና በመዋቅር ጭቆና ምክንያት ዘርፈብዙ ስቃይ ውስጥ የሚገኝ ብሄር ቢጠይቅ ኃጢያቱ ሆነ ልክ አለመሆኑ ምኑ ጋር ነው ክቡርነትዎ ? እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽና ቁምነገሮችን ይዘናል፤ ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ 👇

ብዙ ተለፍቶበት የተዘጋጀ ጥንቅር ነውና በትዕግሥት እንድታነቡ እንጋብዝሃለን!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) በዎላይታ ህዝብ ክልልነት ጥያቄ ላይ ክልከላ ባቀረቧቸዉ ምክንያቶች ላይ አስተያዬት እንዲሰጡበት ወድደናል፥ በቅድሚያ ሰላም ነው ፕሮፌሰር?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ሰላም ነው። እግዚአብሔር ይመስገን። ቀጥታ ወደ ጥያቄዎችህ መግባት ትችላለህ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እሺ አመሰግናለሁ፥ እንግዲህ አንደኛዉ የሕዝብ ቁጥራቸው አምስት ሚሊየን ለማይሞሉ ብሄሮች ክልል መስጠት አያስፈልግም ያሉት ነው። እና በዚህ ምን አሰተያዬት አለዎት ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይህ አስተሳሰብ ከሕገመንግስቱ ከቆመበት ፍልስፍና ( Jurisprudence) አንጻር ሲመዘን በመሠረታዊ ምክንያቶች ተቀባይነት የለዉም። ክልሎች የተዋቀሩት አምስት ሚሊየን ሕዝብ እየተሰበሰበ ከሆነ፣ ኦሮሚያና አማራ ወደ ሰላሳ ሚሊየን ሕዝብ ገደማ ያላቸዉ እንዴት ሊኖሩ ቻሉ፣ ለምን ወደ አምስትና ስድስት ክልልነት አልተሸነሸኑም ?

እነ ሐረሪ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋርና ሲዳማ 6 ሚሊየን ሕዝብ ሳይኖራቸዉ እንዴት ክልል ሊሆኑ ቻሉ? ማለት የፈለግኩት የሕዝቦች ስነ ልቦና ( ከ political history ይመነጫል በዋናነት) መልከአም ምድር፣ አሰፋፈር፣ ከግምት ሳይገባ በቁጥር ብቻ የሚወሰን ከሆነ ከላይ ያነሳሁት ጥያቄ መልስ ሊሰጠዉ ይገባል። ካልሆነ ለዎላይታ ብቻ ሲሆን ቁጥር መመዘኛ ይሆናል ከተባለ የብሄር ጭቆና ነው። ምናልባት ይሄን ያሉት በጉራጌ ስለነበረ ለጉራጌም ብቻ ይህን ማለታቸዉ ተገቢ አይደለም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሁለተኛው ምክንያት ክልል ለእናንተ አይጠቅምም ብዙ ቦታ ተበታትናቹ ስለምትኖሩ የሚል ነው። ስለዚህ ምን የሚሉት ነገር አለ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይሄኛዉም ትክክለኛ ሐሳብ አይመስለኝም። የአሁኑ ግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር የዛኔ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቴ በ2012 ዓ.ም የጊፋታ በአል ላይ ለኦሮሚያ ክልል በተደረገ ግብዣ መሠረት ተገኝተዉ የመልካም ምኞት መግለጫቸዉን ሲያቀርቡ “በኦሮሚያ ከአንድ ሚሊየን በላይ ዎላይታዎች ይገኛሉ።” ብለዋል። እርሳቸዉ ፊንፊኔን የቆጠሩ አይመስለኝ።

ዎላይታዎች በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባ፣ በሲዳማ፣ በተለያዩ ደቡብ አካባቢዎች፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌና አፋር ክልልን ጨምሮ በመላዉ ኢትዮጵያ ማለት በሚቻል መልኩ በከፍተኛ ቁጥር እንደሚኖሩ ይታወቃል። ተበታትኖ ለመኖሩ ሕዝቡ industrious መሆኑ ብቸኛ ምክንያት ካለመሆኑም ባለፈ ዎላይታ ክልል በመሆኑ የሚያጡት ምንም ነገር ካለመኖሩም በላይ ዎላይታ ክልል ባለመሆኑም የሚጠቀሙት ነገር የለም።

የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሰርተዉ ሐብት አፍርተዉ የመኖር ሕገመንግስታዊ መብታቸዉ የተጠበቀ ነው። በተመሳሳይ የዎላይታ ዞንም ክልል ሆኖ መደራጀት መፈለጉ ሕገመንግሥታዊ መብቱ ነው። ስለዚህ የዎላይታ ዞን ክልል ቢሆን ከአካባቢው ዉጪ የሚኖሩ ዎላይታዎች በሕገመንግስቱ መሠረት ከተመራን የሚያጡት ነገር የለም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሶስተኛው ምክንያት የሐገሪቷ አቅም (ኢኮኖሚዉ) አይፈቅድም የሚል ነው። ይሄኛዉስ ያስኬዳል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይህም መከራከሪያ ዉሃ የማይቋዋጥር ከመሆኑም ባለፈ ሌላ የፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በመጀመሪያ Budget ድልድል መካሄድ ያለበት ብቸኛ ባይሆንም ዋነኛዉ ምክንያት የሕዝብ ቁጥር መሆኑ እሙን ነው። ኢትዮጵያ ግን ከድሮዉ የደቡብ ክልል ጀምሮ አሁን ከሲዳማ ዉጪ በክላስተር እንዲዋቀሩ የተፈረደባቸዉ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን ድህነቷን እንደሚሸከሙ የማህበር አህዮች ነው የምታያቸዉ።

ክልልነትን የተጎናጸፉ ብሄሮች በደቡብ ከሚገኙ ዞኖች የክልል በጀትንም ከግምት አስገብተን ማለት ነው። አንጻር በጀታቸዉ በብዙ እጥፍ መብለጡ ( የሕዝብ ቁጥራቸዉ ተመጣጣኝ አንዳንዴም የዞኖቹ እየበለጠ ) ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ተመሳሳይ ሕዝብ ቁጥር በመያዝ ክልል በመሆን የሚገኘዉ በጀት የበለጠ ከሆነ የትኛውም ብሄር ግልጽ ምክንያታዊና ሕገመንግሥታዊ ክልከላ እስከሌለ ድረስ ቢጠይቅ አይፈረድበትም!

የዎላይታ አይነት ሐገር የነበረ ከጭቆና ብዛት የተነሳ ዞንነቱን እንኳን ታግሎ የተጎናጸፈ ብሄር ቢጠይቅ ትክክለኛ እና ክልልም ከተፈቀደለት ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያጠናክር ነው። በተለይ የሐገሪቷ አቅም አይፈቅድም የሚለዉ መከራከሪያ ለዎላይታ አይሰራም! ቀድሞ ነገር የትኛዉ የሐገሪቷ ክልል ነው Autonomy ለማግኘት ከዎላይታ የበለጠ ምክንያት አቅርቦ ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚችለዉ? በሽግግር መንግስት እንደኔ እንደኔ ትልቁ ስህተት የነበረዉ ዎላይታ ክልል አንድ አለመባሉ ነዉ!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ አራተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) የክልል ጥያቄ የሚያነሱ የዎላይታ አመራሮችን “ለምን በእናንተ ልጅ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ጊዜ አልጠየቃችሁም” እያሉ አፍ ያስዘጋሉ ማብራሪያም እንዳይሰጡ ፊት በመንሳት ይከለክላሉ የሚል ጭምጭምታም ተሰምቶ ነበረና ለዚህስ የእርስዎ ምላሽ ምንድነዉ ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይህ ጥያቄ ጥሩ ጥያቄ ነው። በቀናነት ማወቅ ለፈለገ፤ ግን ማብራሪያን ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆን አፋኝነት ነው። እነሆ መልስ፦ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተመሰረተዉ በ1983 ኢህአዴግ ደርግን አሸንፎ ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ባረቀቀዉ የሽግግር ቻርተር ላይ ክልል 9 የነበረዉን ዎላይታን ከሌሎች 55 ብሄሮችና ብሄረሰቦች ጋር በመጨፍለቅ ነበር። በወቅቱ የክልሉን ምስረታ በእነ ወልደአማኑኤል ዱባለ የሚመራዉ የሲዳማ ልህቃን ቡድን፣ እነ ፕሮፈሰር በየነ ጴጥሮስም የተቃወሙት ነበር፤ የዎላይታ ተቃዉሞ ግን ከሁሉም የጎላና፣ ታጋዮቻችንን እነ ሰለሞን ሴታን ለእስራትና ለከፍተኛ ድብደባ የዳረገ ነበር።

በወቅቱ ዎላይታን የወከሉ ሰዎች እንደታሰሩም ይታወቃል። በዚህ ምክንያት ታሰረዉ በእስር ቤት የሞቱም እንደነበሩ ይታወቃል። ኢህአዴግ አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ሲገባ በወቅቱ የተቀሩትን ቋንቋዎች ጥናት አስጠንቼ ነው የምፈቅደዉ የእናንተ ግን የሚታወቅ ስለሆነ ያለጥናት ፈቅጃለሁ ልጆቻችሁንም አስተምሩበት ያለዉ ኦሮምኛ፣ ዎላይትኛ፣ ትግርኛ እና ሲዳምኛ ነበር።

በወቅቱ የተሻለ ዝግጅት ላይ የነበረዉ ኦነግ በኦሮሚያ 1984 ዓ/ም ላይ ሲያስጀምር፣ ዎላይታና ትግራይ 1985 ዓ/ም እንደጀመሩ መረጃዎች ያሳያሉ። እናም እንዲህ በጥዋቱ እዉቅና ያገኘዉን ዎላይትኛ ቋንቋ ለማጥፋት ዎጋጎዳ የሚባል አራት ቋንቋዎችን በመቀየጥ ተፈጥሮ እንዲጫን ሲወሰን ለተቃዉሞ የተነሳዉ የዎላይታ ሕዝብ ካነሳቸዉ ዘርፈ ብዙ እና ዘመን ተሻጋሪ ጥያቄዎች አንዱ የክልል ጥያቄ ነበር።

በዚህ የዎላይታ ሕዝብ የደቡብ ክልል እንዳይመሠረት የተቃወመ ብቻ ሳይሆን፤ ከተመሠረተም በኃላ ከክልሉ በመዉጣት ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የጠየቀ የመጀመሪያ ሕዝብ ያደርገዋል፤ ጥያቄዉ ምላሽ ባያገኝም።

ማስረጃ ካስፈለገ በወቅቱ ትግሉን የመሩት የሐገር ሽማግሌዎች ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በ2/2/ 1992 ዓ.ም በጻፉት የአቤቱታ ደብዳቤ ላይ የሚከተሉ ሐረጎች ይገኛሉ “…የዎላይታ ብሔር በራሱ መልከዓ ምድር የራሱ አስተዳደራዊ መዋቅር በክልል ደረጃ …እንዲዋቀር ይፈልጋል።… በሽግግር መንግሥት ወቅት ክልል 9 ተብሎ በአዋጅ ቁጥር 7/84 መሠረት የዎላይታን ብሔር ማዕከል አድርጎ የተዋቀረዉ መዋቅር ብቸኛና ትክክለኛ ፍትሐዊ መዋቅር ነበር።

እናም ክቡርነትዎ እንደሚገነዘቡት ሁዋላም ላይ የተነሳዉ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ቢኖርም፤ ምላሹ እንደዎላይታዉ ሁሉ ክልከላ እንደነበረ ይታወሳል። በነገራችን ላይ የሁለቱም ሕዝቦች ጥያቄ ጠንካራና ሕዝባዊ መሠረት የነበረዉ በመሆኑ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ከህዝቡ ተወካዮች ጋር ቁጭ ብሎ ለመወያዬት እና አቅጣጫ ለማስቀመጥ ተገዷል።

ለምሳሌ የዎላይታዉ ትግልና ዉይይት ከብሄራችን የሚወክሉን ምሁራን ይሁኑ የሚል አንድምታ ስለነበረዉ፤ በዚህም እድል ካገኙት መሐል አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ባሳዩት የአመራር ብቃትና ባመጡት ለዉጥ እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ ሆነዉ በኢህአዴግ አደረጃጀት፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮችና በመሠረተ ልማት ግምባታዎች ባሳዩት ብቃት የሐገሪቷ መሪ ለመሆን በቅተዋል።

እንደኛው ጭቁን ከሆነዉ ወንድም የኦሮም ሕዝብ ለተገኙት ለእርስዎም ቢሆን ስልጣን ጨብጠዉ ያስረከቡት እርሳቸዉ መሆናቸዉን ማስታወስ ለቀባሪ ከማርዳትም በላይ ነውና ትቼዋለሁ። የሲዳማም ሕዝብ በወቅቱ በአዋሳ ከተማ ከመለስ ዜናዊ ጋር በካሄደዉ ዉይይት የክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ከሲዳማ ዉጪ እንደማይሰጥና አዋሳ ከተማ ላይ የሲዳማ ህዝብ ተጨባጭ demographic change ማምጣት ላይ አተኩሮ ወደፊት ክልል እንደሚሰጠዉ ቃል ገብተዉ ሄደዋል።

ለነዚህ ሁለቱ ክልከላዎች ዋነኛው ምክንያት የኢህአዴግ አደረጃጀት ሁኔታ እንደነበረ ማንም የተወሰነ የፖለቲካ ግንዛቤ ያለዉ ሰዉ ይረዳል። ከኢህአዴግ ምክር ቤት የደቡቡ ደኢህዴን 45 መቀመጫ እንዳለዉ ይታወቃል። እናም ዎላይታ ሆኑ ሲዳማ ደቡብ ታዳጊ እንዳይባል ካደረጉ ህዝቦች ግምባር ቀደም ናቸዉ፣ ክልል ቢሆኑ ታዳጊ ናችሁ ከእንግዲህ ቢባሉ ይቀበላሉ? ኢህአዴግስ 45 መቀመጫ እናንተም ያዙ ብሎ ይሰጣቸዋል ?

ወንበሩንስ ቀንሶ ከሰጣቸዉ ትግራይስ እንዴት 45 መቀመጫ በህወሃት በኩል አገኘች መባሉ ይቀራል ? ይህስ ጉዳይ በቀላሉ ይቋጫል ? ስልጣንስ በክልሎቹ ለተቃዋሚ አሳልፎ መስጠቱን ኢህአዴግ እንደ አማራጭ ይቆጥራል? ክቡርነትዎ ለነኚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ያቅትዎታል ብዬ አላምንም።

እናም ኢህአዴግን ዉህድ ፓርቲ የማድረጉ ስራስ ቀላል ተግባር አለመሆኑስ ይጠፋዎታል ? አሁንስ ብዙ ወገኖቻችንን የበላዉ ጦርነት መነሻ አንዱ ይህ ዉህድ ብልጽግና ሲፈጠር፣ አፈንግጠዉ ከወጡ ኃይሎች ጋር መሆኑስ እንዴት ይጠፋዎታል? ብዬ እጠይቃቸዋለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ አምስተኛው ክልል ሰለተሆነ ብቻ በጀት አይጨመርም፣ ያንኑ የዞኑን በጀት ነው የምናስቀጥለዉ፣ ክልሉ የሚደጉመዉን ያንኑ ብቻ የፈደራል መንግስት ይደጉማል ብለዉ ነበረ ለዚህስ ምላሽዎ ምንድነው ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይህም በጣም ዉሸት ነው። ለምሳሌ ከዎላይታ ዞን ጋር በጣም ተቀራራቢ ሕዝብ ብዛት ያለዉና በጀቱም በትንሹ ይበልጥ የነበረዉ ሲዳማ ክልል ከሆነ በኃላ፣ በ2016 እና በ2017 ዓ.ም በተከታታይ 22.6 እና 23.4 ቢሊየን ብር ሲያገኝ፤ ዎላይታ 7.7 እና 9.6 ቢሊየን ብር ብቻ አግኝቷል። ይህ ልዩነት በዋናነት የዉስጥ ገቢ የፈጠረዉ ሳይሆን ድጎማዉ የፈጠረዉ ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደማጠቃለያ የሚሉት ነገር ካለ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እነኚህ ምክንያቶች በአጠቃላይ ዉሸትና ዉሃም የማይቋጥሩ ሊባሉ የሚችሉ ናቸዉ። መንግሥት እነዚህን ችግሮች ቆም ብሎ ቢገመግም ይሻላል። በተለይ በዎላይታ ዞን ከክልል የሚደጎመዉ በጀት በማነሱ፣ ዞኑ ከባድ ችግር ዉስጥ ነው። የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ አለመካሄዱ ትልቅ ችግር ሆኖ ቀጥሏል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

Ethiopia #southethiopia #Wolaita