በዘንድሮው ምርጫ በዎላይታ አካባቢ ለመሳተፍ የተዘጋጁ ፓለቲካ ድርጅቶች የምርጫ ህግን ተከትሎ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የሚያግዙ ተቋማትን በማደራጀት ከምርጫ ቦርድ የተጣለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን በደቡብ ክልል ምርጫ ቦርድ የዎላይታ ዞን ምርጫ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ገለፀ።
በዞኑ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህግና ደንብ ተገዢ እንዲሆኑ የሚሰራ የፓርዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቁሞ የምክር ቤቱ አባል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች የምክር ቤቱን የአሠራር ደንብ ተፈራርመዋል ።
ምክር ቤቱን ለማቋቋም የተጠራውን ስብሰባ በንግግር የከፈቱት የዎላይታ ዞን ምርጫ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ሻንካ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዜጎች ፍላጎቴን ያሟላልኛል ፤ የሀገሪቱን ሰላም ፣ የህዝቦቿን አንድነት ፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና እድገት ያረጋግጥልኛል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ በነፃነት መርጠው ወደ ስልጣን እንዲመጣ ማድረግ እንዲችሉ ከመንግሥትና ከገዢው ፓርቲ የታየውን ቁርጠኝነት በመጠቀም የዘንድሮውን ምርጫ እጅግ ዴሞክራሲያዊ ፣ ተዓማኒ ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ለማድረግ በስፋት ተንቀሳቅሷል ብለዋል ።
የጋራ ምክር ቤቱ አባል ከሆኑና በዎላይታ ዞን ከሚንቀሳቀሱ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመጡ ተወካዮች መካከል የእናት ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ወ/ማሪያም ልሳኑ ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እያቀናች መሆኑን ያረጋገጠልኝ የጋራ ምክር ቤቱ መቋቋም ነው ብለው ገዢው ፓርቲም ለዴሞክራሲ ማበብ ምክንያት ለመሆን ቁርጠኛ ሆኖ በመገኘቱ በእናት ፓርቲ ስም ምስጋና አቅርበዋል ።
የዎላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አድማሱ አወቀ በበኩላቸው እንደ ፖለቲካ ፖርቲ ብልጽግናም የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚስችል ሰፊ ራዕይ ይዞ ፤ ፕሮግራምና ፖሊሲ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በምርጫው አሸንፎ መንግሥት ለመመሥረትም ፅኑ ፍላጎትና ብቃትም እንዳለው የፓርቲው አመራሮች ጠንቅቀን ስለምናውቅ ፤ በሀገር ደረጃ የለውጡ አመራሮችና ድርጅታችን የዜጎች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማክበር ካለዉ ቁርጠኛ አቋም አንፃር ማንም የብልፅግና አመራር ፣አባልም ሆነ ደጋፊ በየአካባቢያቸው በሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ከታየ አስፈላጊውን የህግ እርምጃ የሚወስድ ምርጫ አስፈፃሚ የሰላምና ፀጥታ ግብረ ሀይል እስከታችኛው መዋቅር ስለተደራጀ ፓርቲዎች ለሚያጋጥማቸው ችግር መሰል ተቋማትን በተገቢዉና በእምነት እንዲገለገሉ ሲሉ የፓርቲያቸዉን አቋም ገልፀዋል።
አባላቱ በምክር ቤቱ የአሠራር ደንብ ላይ ከተወያዩ በኋላ የተለያዩ ኮሚቴዎችን አቋቁመው የስምምነት ፊርማቸውን አኑረዋል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።