
“በማንነታቸው ምክንያት በቁጫ መዋቅሮች ያለው አሁናዊ ሁኔታ በመላው ሕዝብ ላይ ጨለማ የነገሠበት እንዲሆን አስገድዷል” ቁህዴፓ ገልጿል።
“በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቁጫ ወረዳ፣ ቁጫ አልፋ ወረዳና ሰላምበር ከተማ አስተዳደር በሀገራዊ ምክክር ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙ የፓርቲያችን አባላት አፈና፣ ድብደባና እስራት በጋሞ ዞን አመራሮች ትዕዛዝ እየተፈጸመባቸው ነው” ሲል የቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ከሷቸዋል።
ፓርቲው ማምሻውን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በላከው መግለጫ “አንድ አመራር ለቁሕዴፓ ምክር ቤት አባልነት በሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በድጋሚ ተመርጠው ፓርቲውን በማገልገል ላይ የሚገኙና የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ባሰናዳቸው የተለያዩ መድረኮች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙ በትናንትናው ዕለት በሰላምበር ከተማ ሰላምበር ሆስፒታል ፊትለፊት በደረሰባቸው ድንገተኛ ድብደባ የተጎዱ መሆኑንና በአሁኑ ሰዓት ከድብደባው በኋላ በዳምባዬ ቀበሌ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደሚገኙ መረዳት ችለናል” በሚል አሳውቋል።

“በፓርቲው አመራር ላይ የድብደባ ጥቃት የደረሰባቸው በመንግስት ጸጥታ አካላት ሲሆን ከድብደባው የተነሣ አቶ ሻምበል በጤንነት ችግር ላይ የሚገኙና የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የጠየቁ ቢሆንም ሕክምና እንዳይደረግላቸው እንደተከለከሉ መረጃ አግኝተናል” ሲሉ በመግለጫው ገልጿል።
“በሌሎች የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች ላይ የፓርቲው አባላት ወይም ደጋፊዎች፣ አሊያም የቁጫ ብሔረሰብ ተወላጆች በመሆናቸው ምክንያት ብቻ የሚከተሉት ጥቃቶች በቅርቡ ተፈጽመውባቸዋል” ብሏል።
“በጋሞ ዞን መንግስት በተደራጀ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው ስቃይና መከራ፦ የብልፅግና ፓርቲ የአባልነት መዋጮ በግዴታ ዘርፎ ማስከፈል፣ የግድ የብልፅግና ፓርቲ አባልነትንና ጋሞነትን ካልተቀበላችሁ መኖር አትችሉም ብሎ ማስጨነቅና ማዋከብ፣ ያለምንም ሕጋዊ አሠራር ጅምላ የገንዘብ መዋጮ በዝርፊያ መልክ መቀበል፣ ሕዝቡን በጅምላ እየሰበሰቡ ማዋረድ፣ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግና እናጠፋችኋለን” ማለት እንደሚገኝበት አስረድቷል።

“ፓርቲያችን ቁሕዴፓ እንደ ከዚህ ቀደሙ እነዚህን የአፈና ተግባራት እጅግ እየኮነነ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ በአጥፊዎች ላይ እንዲወስድና ከላይ የተዘረዘሩትን አስነዋሪ ተግባራት እንዲያስቆም ጥሪ ማቅረባችንንም ሆነ ድርጊቶቹን በማጋለጥ መፍትሔ መፈለጉን የምንቀጥል መሆኑን በአክብሮት እየገለፅን የቁሕዴፓ የብርታቱ ክንድ የወለደው የቁጫ ሕዝብ ነው!” ሲል ለሚመለከታቸው፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጥሪ አቅርቧል።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏