1000029236

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥልቅ ዝርዝር ጥንቅር

አሁን ያለዉን ጦር የብርሃኑ ጁላ ጦር፣ የኦሮሞ ጦር እያሉ ይከሳሉ ይህን እንዴት ያዩታል? በውትድርና 117 አመታት የዎላይታን ተሳትፎና በተሳትፎ ልክ ቦታ ማግኘት እንዴት ይቀኛል ? … “ጦሩ ላይ ከማነጣጠር በበለጠ የፖለቲካ አመራሮች ላይ ማነጣጠሩ ይበጃል”፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዳንኤል ክብረት በአደባባይ፦ “የኢትዮጵያ መንግስት እምነትና ሰይፍ ያስፈልገዋል”፣ በትግራይ ጦርነት ወቅት ብዙ የዎላይታ ልጆች ጁንታ እየተባሉ በጦሩ ፊት ተረሽነዋል፣ የታሰሩና የተባረሩት ደግሞ ከመሠረታዊ ወታደር እስከ ጀነራሎች ይደርሳሉ”፣ “በአድዋ ጦርነት ወቅት ታማኝ ስለሆኑ ሚኒሊክ በመድፈኝነት ያሰለፈዉ ዎላይታዎችን ነው” … እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ አንገብጋቢ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ምላሽና ቁምነገሮችን ይዘናል፤ ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ 👇

ብዙ ተለፍቶበት የተዘጋጀ ታሪካዊ ጥንቅር ነውና በትዕግሥት እንድታነቡ እንጋብዝሃለን!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መከላከያ በቅርቡ 117 ኛ የምስረታ አመቱን እያከበረ እንደነበረ ይታወሳል ይህንን እንዴት ያዩታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በበኩሌ በቀን ደረጃ ለመከላከያ፣ ተመድቦ መከበሩ ላይ ተቃዉሞ የለኝም። አመታቱ ከፍተኛ የተዋጽ ችግር የተፈራረቀባቸዉ፣ መከላከያ አብዛኛውን እድሜዉ በርስ በርስ ጦርነት እየተሳተፈ ያሳለፈበት፣ ሐገር ከወራሪ የተከላከለበት፣ በዉጪ ሐገራት ሰላም ያስከበረበት፣ የአምባገነኖች ጠባቂ እና መፈልፈያ የሆነበት፣ በሐገር ዉስጥ ዘር ማጥፋት ደረጃ የተከሰሰበት፣ ሲፈርስ እና ሲታደስ የኖረበት፣ በግዳጅ አፈሳ ሰዉ የመለመለበት፣ የፖለቲካ ዉግንናዉ ከተቋማዊ ገለልተኛነት በልጦ የዘለቀበት ነዉና እነኝህ ሁሉ ከግምት ዉስጥ መግባት አለባቸዉ።

በተለይ በተለይ መጀመሪያ የምስረታ አመታት አካባቢ የነበረዉ በርግጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ተብሎስ መጠራት የሚችል ነው ወይ የሚለዉ መጠየቅ አለበት።

በአጠቃላይ ተቋሙ አካታችና ጠንካራ እንዲሆን እንፈልጋለን፣ ለሐገር ቀጣይነትና ለዜጎች ዋስትና ከነችግሩም ቢሆን መከላከያ ቁልፍ ሚና ያለዉ ተቋም መሆኑን እንገነዘባለንና። ደግሞ አሁን ላይ እድሜያቸዉ በ18 ዓመት በታች የሆኑ ብዙ ታዳጊዮችን በብዛት መያዙ በተለያዩ አካላት ከመነሳቱ በተጨማሪ የአደባባይ ሚስጢሪ ነዉና መታረም ያለበት ጉዳይ ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በእነዚህ 117 አመታት የዎላይታን ተሳትፎ በወፍ በረር ብንቃኝ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ታሪክ እና ዎላይታ ሚኒሊክ፣ በቀድሞ ኃይለሥላሴ፣ በደርግ፣ በኢህአዴግ እና በብልጽግና አጠቃላይ ዎላይታ ብርቱና ከድርሻዉ በላይ የሚሳተፍ፤ ግን በዛ ልክ የጦሩ አመራር እንዲሆን የማይፈለግ ሆኖ ዘልቋል ማለት ይቻላል። ከታሪክም መረዳት እንደሚቻለዉ ዎላይታ ጠንካራ ተዋጊ ሕዝብ ስለመሆኑ ታሪኩ ምሥክር ነው። ከ14 ዓመት በላይ የሆነ ወንድ ልጅ በሙሉ እንደ ዘመናዊዉ ብሄራዊ ዉትድርና አይነት ባህል ስለነበረ መዋጋት የሚችል ነው የነበረዉ፥ በየአዉደ ግምባሩ ባሳየዉም ጀግንነት መሠረት ይሾማል ይሸለማል፣ የክብር ስምም ይሰጠዋል።

በዚህም ጠንካራ አደረጃጀት ምክንያት ዎላይታ ሐገርነቱን አስጠብቆ ከመኖሩም ባለፈ፣ ሚኒሊክን ስድስት ጊዜ መርታቱ ሕያዉ ምስክር ነው። ይህ ታላቅ ሕዝብ ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለ በሁዋላ በኢትዮጵያ ሠራዊት ዉስጥ ምን ተሳትፎ ነበረዉ በየመንግስታቱስ ምን ተግዳሮት ገጠመዉ የሚለዉን በአጭር በአጭሩ ስንቃኝ፣ ያኔ መደበኛ ሠራዊት ባይደራጅም በአድዋ ጦርነት ወቅት ታማኝ ስለሆኑ ሚኒሊክ በመድፈኝነት ያሰለፈዉ ዎላይታዎችን መሆኑን አማኑኤል አብርሐም፣ በአረፈይኒ ሐጎስ አርትኦቱ በተሰራዉ መጽሐፉ ጽፎልናል።

በ1983 የሽግግር ጉባኤ ላይ ሻለቃ አድማሴ የተባሉ ሰው በአድዋ ከተሳተፉት ጦር ምርጥ ምርጥ የሚባለዉ ከዎላይታ መምጣቱን የሚያሳዩ የታሪክ መጽሐፍትን ማቅረብ እችላለሁ ብለዋል። ሻለቃ ጻዉሎስ ጌታቸዉ የተባሉ የጦሩ ታሪክ ጸሐፊ በደቡብ ቴሌቪዥን በአድዋ የዎላይታዎችን ጋሻ ጥይት እንደማይበሳዉም በወቅቱ በዉጪ ጸሐፊዎች የተጻፈውን ሲጠቅሱ ሰምቻለሁ።

በቀድሞ ኃይለሥላሴ ዘመን እኩልነት የማይታሰብ ቢሆንም ዎላይታዎች በወቅቱ ሰራዊት ዉስጥ ተሳትፎ ነበራቸዉ፣ ኮሪያ የዘመተዉ ቃኘዉ ሻለቃ ዉስጥም ነበሩ፣ እንደዉም አንዱ ዎላይታ ከሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር በተቀበለዉ ቦምብ፣ የራስ ደስታ ፍስሃ ጦናን የ40 ጅራፍ ግርፋት አስሰርዟል።

ደርግ ከረሸናቸዉ የቀኃሥ ጀነራሎች መሐል የዎላይታ ተወላጅ ይገኝበታል ሲባል ሰምቻለሁ። በተቃራኒው ደግሞ ከ109 የደርግ አባላት ዎላይታ አለመኖሩ ብዙ ጥርጣሬ ዉስጥ ይከታል፣ አጋጣሚ አይመስልም። ደርግ የባህር ሐይሉን ሲቆጣጠር ከንጉሱ የልጅ ልጅ ከሆነዉ ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ፣ በሁዋላ አዛዥ ያደረገዉ ዎላይታዉን ተወላጅ ሪር አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑን ነው፤ ብቃት ያለዉ መኮንን ቢሆንም ፖለቲካዉ ስለማይቀበለዉ ግን ብሄሩን ክዶ የአዲስ አበባ ኦሮ-ማራ ነኝ ብሏል ይባላል (እርግጠኛ አይደለሁም)፣ ለማንኛውም በ1981 መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ምክንያት ተይዞ ታስሮ ቆይቶ በኢህአዴግ ተፈቷል፣ አሁን በህይወት የለም።

በደርግ ጊዜ ብዙ ዎላይታዎች በዉድም በግድም ወደ መከላከያ ሠራዊት ተቀላቅለዋል፣ ራሺያና የመሳሰሉ ትልልቅ ሐገራት ድረስ የሰለጠኑም እንደነበሩ ይታወቃል። በሁዋላ ፖለቲካዉን ያላወቀበት ደርግ ጦርነቶች እየከበዱት ሲመጡ ከዎላይታ ተማሪና ገበያተኛ ሳይቀር በግድ እየጫነ ወስዶ ዎላይታን ወጣት የሌለባት አድርጎ ነበር፣ ወደ ሰባት አዉራጃ የበተነዉም ብዙ ወታደር ለመመልመል ነው ይባላል።

ፖለቲካዉን ያላወቀበት ደርግ ሲፈረካከስ፣ ከ500 ሺ በላይ የሰዉ ሐይል የነበረዉ ጦር ተበተነ፣ በጣም የሚገርመዉ ኢህአዴግ የተበተነዉ ጦር በየወረዳዉ እንዲመዘገብ ባደረገዉ ጥሪ መሠረት በዎላይታ ብቻ 100ሺ ሰራዊት ተመዝግቧል፣ በወቅቱ ወደ ሱዳንና ወደተለያዩ ሐገራት ተሰደዉ ያልተመለሱም ነበሩ ይባላል።

በጣም የሚያሳዝነዉ ይህ ሁሉ ሲሆን ከደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሐል አንድም የዎላይታ ተወላጅ አልነበረም፣ ጦርነቱ ያስፈልጋል አያስፈልግም በሚለዉ ላይ ዎላይታ ድምጽ አልነበረዉም። የቀድሞ ሰራዊትን መለስ ዜናዊ ለመበተን ያቀረበዉ መከራከሪያ በበኩሌ አይዋጥልኝም፣ “ሰራዊቱ አጠቃላይ ወንጀለኛ ነው።

ለምሳሌ ሶስተኛ ክፍለጦር እያንዳንዱ በኪሱ ክብሪት ይዞ ይንቀሳቀስ ነበር መንደሮችን ለማቃጠል” ይላል መለስ። የተሻለ የነበረዉ እርቅ እና የተሐድሶ ስልጠና በማካሄድ ከኢህአዴግ፣ ከኦነግም፣ ከቀድሞ ሰራዊትም በማዉጣጣት ጠንካራ ሐገራዊ ጦር ቢገነባ መልካም ነበር።

ያኔ ሕወሐት የያዘዉ ብልጫ፣ አሁን ሐገሪቷ ለገባችበት ቀዉስ የበኩሉት ተወጥቷል። ኢህአዴግ በለስ ቀንቶት አራት ኪሎ ሲደርስ፣ የነበረዉ ጦር በዋናነት የህወሃት ሲሆን የተቀረዉ የብአዴን ነበር፣ የተወሰኑ ከሻዕቢያ የተወሰዱ ምርኮኛ ኦሮሞዎች እና የደቡብ ልጆችም ነበሩ።

እንግዲህ ዎላይታ በደርግ ጊዜ በዉድም በግድም የሰለጠነ ብዙ ሰራዊት ብታፈራም የመከላከያ ሠራዊት ተሳትፎ ከዜሮ ለመጀመር ተገዳለች ማለት ነው፣ ኦሮሞም፣ አማራም፣ የተቀረዉ ሕዝብም ከኛ የተለዬ እጣ አልገጠመዉም። እንደ አዲስ ተመልማይ ጦሩን ዎላይታዎች መቀላቀል የጀመሩት በጥዋቱ ቢሆንም በሻዕቢያ ወረራ ወቅት በገፍ ዘምተዉ ጀግንነት አሳይተዋል፥ መስዋዕትነት ከፍለዋል፣ አካላቸዉን አጥተዋል።

ህወሃት በወቅቱ ብዙ ብሄሮችና ብሄረሰቦች መከላከያን ሲቀላቀሉ፣ አመራሩን በአስተማማኝ ሁኔታ ብትቆጣጠርም፣ ተራዉ ወታደር ከሌላ ቦታ እየበዛ ስለመጣ “በጦሩ ዉስጥ እግራችንን እያጣን ነው” በሚል ከትግራይ በግድ ጭምር ወጣቶች መከላከያን እንዲቀላቀሉ ታደርግ እንደነበር ይነገራል፤ ይህ እንግዲህ የአማራና ኦሮሞ ሊህቃን ለትግራይ ሕዝብ የፖለቲካ ፍላጎቶች እዉቅና ባለመስጠታቸዉ የዘለቀ ስጋት ሊሆን ይችላል።

እንግዲህ በመከላከያ የነበረዉ የአመራር ብሄር ተዋጽኦ አለመመጣጠኑ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ ከርሞ ለዉጡን ካፈነዱ ጥያቄዎች አንዱ ነው። እንግዲህ በኢህአዴግ ዘመን ዎላይታ የዉትድርና ባህል ስላለዉ፣ ሐገር ለመከላከል ካለዉ ቁርጠኝነት እንዲሁም እንደሥራእድልም በመቁጠር በብዛት ተሳትፎ ሐገሩን ይጠብቅ ነበር። በኢህአዴግ ዘመን ሐቀኛ ሪፎርም ከተካሄደ ጥሩ ቦታ ያገኛሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ብሄሮች አንዱ ነበር።

ምክንያቱም በነዚህ አመታት ብዙ የዎላይታ ልጆች በብቃታቸዉ እስከ ጀነራልነት መድረስ ችለዉ ነበር። ኦሮ-ማራ ነኝ ብሎ ከኢህአዴግ የተነሳዉ የአሁኑ ብልጽግና ስልጣኑን የተረከበዉ በሰላማዊ መንገድ ቢሆንም፤ ዘመነ ስልጣኑን ገና ከመጀመሩ፤ በጣም አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ከሁሉም የሰራዊቱ ክፍሎች በብሄር እየለዬ 40ሺ ዎላይታዎችን ብቻ መርጦ ቀነሰ፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከዳ እንጂ ያባረርነዉ የለም ብሎ የለመደዉን ዉሸት ከፍተኛ አመራሮችን ሲያሰለጥን ደግሞታል፣ በጣም ያሳዝናል።

ይህ ማለት ዎላይታ ከአብዮቱ ጀምሮም ሆነ፣ ከ1983 ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊት ያደረገዉ ተሳትፎ በዜሮ ተባዝቷል ማለት ነው። ይህ ክፉ እጣ ከትግራይ ጦርነት ጋር ተያይዞ በትግራይ ልጆችም ላይ ደርሷል። አሁን ሐገሪቷ ለገባችበት ዉድቀት የዎላይታ እና የትግራይ ልጆች ከመከላከያ በገፍ እና በግፍ መቀነሳቸዉ የአንበሳዉን ድርሻ ከተወጡ ነገሮች አንዱ ነው።

በነገራችን ላይ በትግራይ ጦርነት ወቅት ብዙ የዎላይታ ልጆች ጁንታ እየተባሉ በጦሩ ፊት ተረሽነዋል፣ የታሰሩና የተባረሩት ደግሞ ከመሠረታዊ ወታደር እስከ ጀነራሎች ይደርሳሉ። እንግዲህ ያ 40 ሺ ጦር መቀነሱ አንዱ ምክንያት የዎላይታ ልጆች ጦሩ ዉስጥ የአመራር ቦታዎችን እንዳይዙ ነበረ፣ የሐገሪቷም ጦርም ለታቀደዉ ጦርነት አመቺና ታዛዥ እንዲሆን ታማኝነቱም ለሕገመንግስቱ ሳይሆን ለአገዛዙ እኩይ አላማ እንዲሆን ነው።

ከዛ በሁዋላ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚማገድ የሰዉ ኃይል በገፍ ሲፈልግ በሚዲያ እንደሚከተለዉ ማለቱ ይታወሳል “ዎላይታ በአድዋም፣ በኃይለሥላሴም፣ በደርግም፣ በኢትዮ_ኤርትራም ግጭት ዘምቷል ታዲያ ጀግና ካልዘመተ ማን ይዘምታል?” ሲሉ ነበረ፣ ይሄ የክፋት ጥግ ነው። እዉቀትና ልምድ ያላቸዉን ገፍቶ፣ ለጋ ወጣት ለጥይት ማብረጃ ለመሰብሰብ ታሪክ ማጣቀስ ግፍ ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ የዚህ አዙሪት ማቆሚያዉ መቼ ነው ? ዎላይታንስ በተደጋጋሚ ለነዚህ የመቀነስ አደጋዎች የሚዳርገዉ ምንድነዉ ? ያዉ የመከላከያ ነገር ከሕግም አንጻር በጥንቃቄ መወራት ስላለበት፣ በአጭሩ መፍትሔ የሚሉትን ቢጠቁሙ?

✅ ፕሮፈሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ዎላይታን ለነዚህ ለፍቶ ባዶ ለመቅረት አደጋ የሚዳርጉ ነገሮች በአጭሩ ኢትዮጵያ ከሐገረ መንግስት ግምባታ አለመሳካት በተጨማሪ፣ የዎላይታ ልጆች የጦሩ አመራር እንዳይሆኑ በግልጽም በስዉርም የሚያደርጉ አሰራሮች መኖራቸዉ አንዱ ሲሆን። ሁለተኛውና ዋነኛዉ የማእከላዊዉ መንግስት ስልጣን በአስተማማኝ፣ በዘላቂ ሁኔታ መጋራት የሚያስችል ሥርአት ስላልተገነባ ነው።

በተለይ የፖለቲካ ሥልጣን አለመጋራት፣ እንደሕዝብ በማታምንበት ጦርነት እንድትሳተፍ ያስገድድሐል። የትግራይ ጦርነት ለኛም በጣም መጥፎ ነበረ፣ አንደኛ በፖለቲካ አመራር ዉስጥ የኛ ሰዉ አልነበረም፣ በጦሩ ዉስጥም ብዙ ብቃት ያላቸዉ የዎላይታ ልጆች በሴራ ጁንታ እየተባሉ ተባርረዋል፣ ታስረዋል፣ በጦሩ ፊት ተረሽነዋል።

ስለዚህ ዎላይታ የማዕከላዊ መንግስትን ሥልጣን በአስተማማኝ እና ዘላቂ ሁኔታ መጋራት የሚችልበትን ሥርአት ለመገንባት መታገል አለበት። ያ ለብዙ ችግሮች መፍትሔ ነው፥ ለኢትዮጵያም የሚበጃት ያ የአካታችነት መንገድ ነውና።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በተለይ በታሪካችን ልንሻገረዉ ያልቻልነዉን የእርስ በርስ ጦርነት፣ እንዴት መሻገር እንደምንችል አስተያይት ቢሰጡን ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እንግዲህ መነሻዉ የፖለተካ ችግር ነው፣ ስለዚህ ለፖለቲካዊ ልዩነት በተለይ መንግስት ኃይልን እንደ አማራጭ ባይወስድ፣ በተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸዉም ኃይሎችም የራሳቸዉን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ጉዳይ ከግምት ዉስጥ ማስገባት አለባቸዉ።

የኢትዮጵያ ሐገረ መንግስት በፈጣሪ የተሠራ ሳይሆን በሰዉ የተሰራ ነውና ጉድለቶችን ማረምና የተበደሉትን የመካስ፣ ያልተካተቱትን የማካተቱ መንገድ ይበጃል፣ በተለይ ድብብቆሽ አያዋጣም። የኢትዮጵያ መንግስታት ለዘመናት የሚመጻደቁት፣ ተበድረዉ በገዙት የጦር መሳሪያ ነው፣ ይህ አሳፋሪ ነው፣ የሚፎክሩትና የሚሸልሉትም በአብዛኛው የፖለቲካ ጥያቄ አለን በሚሉ ሕዝቦች ላይ ነው።

አንዳንድ ጊዜ የብሔር ጥያቄዎችን ላለመመለስ የሚሰጡት ምክንያት የሐገሪቷ የኢኮኖሚ አቅም አይፈቅድም የሚል ነዉ፤ ነገር ግን ችግር ሲፈጠር ተበድረዉ የመዋጋት ችግር የለባቸዉም መንግስታቶቻችን። መዉጫዉ መንገድ ሁሉን አቀፍ ድርድርና ዉይይት እንዲሁም ምክክር ነው። ብሔራዊ መግባባትን፣ በሕገመንግስት ደረጃ በማረጋገጥ፣ ሕገመንግስታዊነትም እንዲሰፍን በማድረግ ነው።

በተለይ የፖለቲካ አመራሩ አካታችነት ቸል ሊባል አይገባም። ለዚህ ሁሉ ግን የበለጠ ድርሻ ያለዉ መንግስት ነው፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተለያዬ የፖለቲካ እምነት አለ፤ ያ እንዴት ይስተናገድ የሚለዉ ቁልፍ ጉዳይ ነው፣ የማንም ድምጽ መገፋት የለበትም።

አሁን ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዳንኤል ክብረት በአደባባይ፦ “የኢትዮጵያ መንግስት እምነትና ሰይፍ ያስፈልገዋል “የሚል ዲስኩር ከጦርነቶች በፊት ያቀርብ ነበረ፣ ከአንድ የፖለቲካ እምነት ዉጪ ያለዉን በሰይፍ ለማጥፋት የሚያልም ሰዉ ነው፣ እንደዚህ አይነት አስተሳሰቦች እያሉ ሰላም የሚወርድ አይመስለኝም በተለይ በመንግስት የሥልጣን ቦታ።

ይህ ግለሰብ በቅርቡ “ጦሩ ዉስጥ በግና ተኩላ ተቀላቅሎ ነበረ… እግዚአብሔር ደጎችን ስለሚቀና ያ ጦርነት መጣ” በማለት የራሱና የመሰሎቹ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የፈጠረዉን ጦርነት በእግዚአብሔር ላይ አሳብቧል።

በተጨማሪ ጦርነቱን እንደ እድል ቆጥራል፣ አብሮ ሐገሩን በጋራ ሲጠብቅ የነበረዉን ሰራዊት ተኩላና በግ ብሎ ከፋፍሏል፤ ያም የሚያሳየዉ ተኩላዉ እራሱ መሆኑን ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ አንዳንድ አካላት አሁን ያለዉን ጦር የብርሃኑ ጁላ ጦር፣ የኦሮሞ ጦር እያሉ ይከሳሉ ይህን እንዴት ያዩታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይህ ትክክለኛ ካለመሆኑም በላይ አሰፈላጊም የሆነ አባባል አይደለ በተለይ የመከላከያ ጉዳይ ጥንቃቄ ይፈልጋል። መቼም ቢሆን መከላከያ ጠንካራ እንዲሆን ነው መፈለግ ያለብን፣ ጦሩን የሚከፋፍል መርዝ መርጨት ተገቢ አይደለም፤ መከላከያ ችግር ቢኖርበትም ለሐገሪቷ ሕልዉና አስፈላጊ ነው።

ለምሳሌ እንደ ዎላይታ አላግባብ የተቀነሱ የሠራዊት አመራሮች እንዲመለሱና ተገቢ ቦታ እንዲያገኙ እንፈልጋለን፣ መካስና መቋቋም ያለባቸዉም እንደዛዉ። ከዛ በተረፈ መከላከያ የበለጠ አካታች እና የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን እንፈልጋለን። ወንጀል የሠራ ይጠየቅ እንጂ ለመከላከያ መጥፎ በጅምላ አንመኝም።

የእርስ በርስ ጦርነቶች ጦሩን ያዳክማሉና መቆም አለባቸዉ፣ ችግራቸዉ ፖለቲካ ነዉና ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋል፥ ጦሩ ላይ ከማነጣጠር በበለጠ የፖለቲካ አመራሮች ላይ ማነጣጠሩ ይበጃል።

ጦሩም ለገባበት ችግር ዋናዉ መነሻ የፖለቲካ ብልሽት ነው፣ ስለዚህ ፖለቲካዉ ከተስተካከለ ጦሩም ይስተካከል፥ ከዛ በተረፈ ግን ስለመከላያ ጉድለቶቹንም በጠቅላላ በአደባባይ ማስጣት አያስፈልግም ጥንቃቄ ያስፈልጋል፣ ሐገሪቷ የዉጭ ወረራ ከገጠማትስ ብሎም ማሰብ ያስፈልጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ከፖለቲካ ዉግንና ነጻ የሆነ ጦር ገንብተናል የሚሉት ተራ ዲስኩር መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው። በትሹ ግን የጦሩ አመራር ወደቀልቡ ከተመለሰ በራሱ ሕጋዊ ስልጣን ማሻሻል ያለበት ለ Counter insurgency ከባድ መሳሪያዎችን ማለትም ድሮን፣ ታንክ፣ የጦር ጀቶች እና የመሳሰሉትን መጠቀም በ civil ሕዝባችን ላይ
ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነውና ያ አፋጣኝ የፖለቲካ መፍትሔ ይፈልጋል ጦርነቱ ማለት አለበት።

በአንድ ወቅት በወለጋ በመንግሥት የአየር ድብደባ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሴት ልጅ ተገደለች፣ ከሳምንታት በሁዋላ ቀድማ የተፈተነችዉ የማትሪክ ዉጤት ሲለቀቅ 4 ነጥብ አምጥታለች፥ መሰል አጋጣሚዎች ብዙ ናቸዉ። ይህን ስል አንድ ጊዜ ኢታማዦር ሹሙ “ለገጠመኝ ኃይል መሳሪያ ልመርጥለት ነው ?” ያሉበት መልስ ጠፍቶኝ አይደለም።

እኔ እያልኩ ያለሁት ጦርነቶቹ በታጣቂ ቡድኖች በኩልም ብዙ የሰዉ ኃይል ስለሚሰለፍባቸዉ፣ ለመከላከያም ከባድ መሳሪያ አትጠቀም ማለቱ ከባድ እንደሆነም ይገባኛል፤ ነገር ግን የተሻለዉ አማራጭ ለችግሮቹ ፖለቲካዊ መፍትሔ የፖለቲካ አመራሩ እንዲፈልግ ማመላከት ያስፈልጋል።

ለፖለቲካ ችግሮች መንግስት፣ ፖለቲካዊ መፍትሔ ፈልጎ መከላከያንም ከርስ በርስ ጦርነት ማሳረፍ አለበት። በየጊዜው ለዉጡን ጠብቁ እያለ በገፍ የሰዉ ኃይል ለመከላከያ ከመመልመልም ይታደገዋል። ለዉጡ ምን ጎድሎት ነው፣ በወታደር የሚጠበቀዉ ብሎም መንግስት መጠየቅ አለበት። በበኩሌ የትኛውም የታጠቀ ቡድን ወደ ድርድር ቢመጣ ደስተኛ ነኝ፣ የፕሪቶሪያም ስምምነት ወደተግባር መቀየር አለበት እላለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

#Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Ethiopiadefenceforce

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን። 👇

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥልቅ ዝርዝር ጥንቅር