የጁንታ ደጋፊ ናቸው” በሚል በተወሰደው እርምጃ የዎላይታ ብሄር ጀኔራሎች ከሶስት ወደ አንድ ብቻ ዝቅ መደረጉ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩ ተነግሯል።
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

ባለፉት ስድስት አመታት “የዎላይታ ብሄር የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ መኮንኖችና ጀኔራል መኮንኖች ተሳትፎና ውክልና ያመናመነው ሪፎርም ተደርጓል” በሚል አንድ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንን ገልጸዋል።
“ለስሙ ሪፎርም ተብሎ በየሚዲያ የህዝብን ትኩረት ለማስቀየስ ነጋ ጠባ ሲነገርለት የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ሪፎርም ለዎላይታ ተወላጅ የሰራዊት አባላት፣ መኮንኖችና ጀኔራሎች ተሳትፎና ውክልና ከሪፎርም በፊት ከነበረው እንድመናመን አድርጎታል” ሲሉ አንድ ከፍተኛ መኮንን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ቅሬታ ገልጸዋል።
መኮንን ለአብነት በሚል ሲገልፅ፦ “ለማነጻጸር ያህል የሲዳማ ብሄር ጀኔራሎች ቁጥር ከሪፎርም በፊት ሶስት ነበሩ፤ ከሪፎርም በኋላ አምስት ደርሰዋል፡፡ የሀዳያ ተወላጅ ጀኔራሎች ቁጥር ከሪፎርም በፊት ሁለት ነበሩ ከሪፎርም በኋላ አራት ደርሰዋል” ብለዋል።
“የዎላይታ ብሄር ጀኔራሎች ቁጥር ከሪፎርም በፊት ሶስት ነበሩ አሁን በተጨባጭ ያሉ ጀኔራሎች ቁጥር አንድ ብቻ ነው፡፡ ለምንድ ነው ቁጥራቸው የወረደው ከተባለ የጠ/ሚኒስትር ዐብይና የሚመሩት ብልጽግና የነደፉት ሪፎርም የዎላይታ ተወላጆችን የጁንታ ደጋፊ ናቸው” በሚል ጅምላዊ የማግለል ፖሊስ የተነሳ በትምህርታቸውና በአመራር ብቃታቸው አንቱ የተሰኙ ጀኔራሎች መታሰር፣ ከስራ መሰናበትና ከደረጃ እድገት መገፋት ነው” ሲሉ ከፍተኛ መኮንኑ ሁኔታውን አስረድተዋል።
“ይህ ፖሊሲ ካልተቀየረ ለወደፊትም ከዎላይታ ጀኔራል መኮንን ይወጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከዚህ ፖሊሲ የተነሳ የዎላይታ ጀኔራሎችና መኮንኖች ከማዕረግ እድገትና ከቀጣይ ሃላፊነት ቦታ ከመታጨት ይገፋሉ” ብለዋል።
ከፍተኛ መኮንኑ ለዚሁ ምክንያት ሲያቀምጡ፦ “ለአገዛዙ ታማኝ የሆኑ ሲሾሙና ቁልፍ ቦታዎች ላይ ሲመደቡና ጥቅማጥቅም ሲያገኙ ከዎላይታ የተገኙ የጦር መኮንኖችና ጀነራሎች ይገፋሉ፡፡ ይህ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ በሰራዊቱ ጣልቃ እየገባ የፖለቲካ ወገንተኛ የሆኑትን መኮንኖች ለሹሜት ማጨት ውጤት ነው” በሚል አክለዋል።
በተጨማሪም “የማዕረግ አሰጣጥ ፈር የለቀቀና በጠ/ሚኒስትሩ የግል ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በርካታ እንከኖች የነበሩበት ነበር፡፡ ለምሳሌ ሲኔሮች እያሉ ጁኔሮችን መሾም፡፡ የህዝቦችን ተሳትፎ ከግምት ባለማስገባቱ የአንዳንድ ብሄሮች ጀኔራሎች ቁጥር ማብለጥና ዎላይታን ጨምሮ ሌሎች አናሳዎች ብቃትና ችሎታ እያላቸውም ለሹመትና ማዕረግ እድገትና ለሃላፊነት ቦታዎች አለመታጨት” መኖሩን ጠቅሰዋል።
“ለብልጽግነና እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጀኔራሎች በአንድ ጊዜ ሁለት ደረጃ ከፍ ወደሚል የማዕረግ ደረጃ ማሸጋገር፡፡ በአዛዦች ካውንሲል ያልቀረቡ ዕጩዎችን ጠቅላዩ ራሱ አዞ መሾም፡፡ ለምሳሌ የሴት ጀኔራሎች ሹሜት፡፡ በጅምላ ሜዳይ መሸለም፡፡ በስታፍ ስራ የተሰማሩ መኮንኖች ግንባር ላለው ሰራዊት ያበረከቱትን አስተዋጾኦ በመካድ ከማዕረግ እድገት ውድድር ውጭ ማድረግ” በዋናነት እንደሚገኝበትም አብራርተዋል።
ከፍተኛ መኮንኑ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ “በውትድርና በአንድ ሲኔሪቲ ደረጃ ላይ ያሉ መኮንኖች እያሉ ጁኔር ለጀኔራልነት መሾም ተቀባይነት የሌለው አካሄድ መሆኑ እየታወቀ ይህንን በሚያፋልስ ሁኔታ ሹመትና የሃላፊነት ቦታ ተሰጥቶ ተቋማዊ ስርአት አልበኝነት አንዲነግስ ሆኗል” ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
“ሲጠቃለል ሰራዊቱ ውስጥ ያሉ የዎላይታ መኮንኖችና ጀኔራሎች ተገፍተዋል፡፡ በመከላከያ ፖሊሲና ጉዳዮች የመሳተፍና የመደመጥ አቅም ተነጥቀዋል፡፡ አንዳንዶች በግፍ ከስራ ተሰናብተዋል፡፡ አንዳንዶች በተዛባ ፖሊሲ ምክንያት በእስር ማቀዋል፡፡ አንዳንዶች ለሀገር በከፈሉት ልክ የሚገባቸውን ቦታና ጥቅማጥቅም አጥተዋል” ብለዋል።
ሀገርን በመከላከልና በውትድርና ዘርፍ ዎላይታ ጉልህ አስተዋጾ አበርክቷል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የዎላይታ ልጆች በየአገዛዙ በውዴታና በግዴታ የውትድርና አገልግሎት በመስጠት ለሀገር ግንባታ መስዋአትነት መክፈላቸውንና እየከፈሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከፍተኛ መኮንኑ “አሁን የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዎላይታ ልጆች ተቋሙን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ለከፍተኛ የማዕረግ እርከን የሚወጡ አባላትና ጀኔራል መኮንኖች መመናመን አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ መገፋቱ መቆም አለበት፡፡ የተገፉ የዎላይታ መኮንኖችና ጀኔራሎች የሚካሱበት ሁኔታ መፈጠር አለበት” በሚል በአፅንኦት ጥሪ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በመከላከያ የነበረዉ የአመራር ብሄር ተዋጽኦ አለመመጣጠኑ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ ከርሞ ለዉጡን ካፈነዱ ጥያቄዎች አንዱ ነው። እንግዲህ በኢህአዴግ ዘመን ዎላይታ የዉትድርና ባህል ስላለዉ፣ ሐገር ለመከላከል ካለዉ ቁርጠኝነት እንዲሁም እንደ ሥራ እድልም በመቁጠር በብዛት ተሳትፎ ሐገሩን ይጠብቅ ነበር። በኢህአዴግ ዘመን ሐቀኛ ሪፎርም ከተካሄደ ጥሩ ቦታ ያገኛሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ብሄሮች አንዱ ነበር።
ምክንያቱም በነዚህ አመታት ብዙ የዎላይታ ልጆች በብቃታቸዉ እስከ ጀነራልነት መድረስ ችለዉ የነበረ ሲሆን ከኢህአዴግ የተነሳዉ የአሁኑ ብልጽግና ስልጣኑን የተረከበዉ በሰላማዊ መንገድ ቢሆንም፤ ዘመነ ስልጣኑን ገና ከመጀመሩ፤ በጣም አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ከሁሉም የሰራዊቱ ክፍሎች በብሄር እየለዬ 40ሺ ዎላይታዎችን ብቻ መርጦ ተቀንሶ እንደነበር ይታወሳል።
ይህ ማለት ዎላይታ ከአብዮቱ ጀምሮም ሆነ፣ ከ1983 ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊት ያደረገዉ ተሳትፎ በዜሮ ተባዝቷል ማለት ነው። ይህ ክፉ እጣ ከትግራይ ጦርነት ጋር ተያይዞ በትግራይ ልጆችም ላይ ደርሷል። አሁን ሐገሪቷ ለገባችበት ዉድቀት የዎላይታ እና የትግራይ ልጆች ከመከላከያ በገፍ እና በግፍ መቀነሳቸዉ የአንበሳዉን ድርሻ ከተወጡ ነገሮች አንዱ እንደሆነ ይነገራል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት ብዙ የዎላይታ ልጆች ጁንታ እየተባሉ በጦሩ ፊት ተረሽነዋል፣ የታሰሩና የተባረሩት ደግሞ ከመሠረታዊ ወታደር እስከ ጀነራሎች ይደርሳሉ። እንግዲህ ያ 40 ሺ ጦር መቀነሱ አንዱ ምክንያት የዎላይታ ልጆች ጦሩ ዉስጥ የአመራር ቦታዎችን እንዳይዙ ነበረ፣ የሐገሪቷም ጦርም ለታቀደዉ ጦርነት አመቺና ታዛዥ እንዲሆን ታማኝነቱም ለሕገመንግስቱ ሳይሆን ለአገዛዙ እኩይ አላማ እንዲሆን ሆኖ እንደነበር ባለፈው ሳምንት ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በፓለቲካ ወጌሻ ጥንቅር ዝግጅት ላይ ማቅረቡ ይታወሳል።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Ethiopianarmy
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው