1000029956

“ትግራይን በመግፋት ከሻዕቢያ ጋር መተቃቀፍ ከባድ ዋጋ አስከፍሎናል”….. ያልተመለሱ ሀገራዊ ቀጠናዊ ጥያቄዎች ምላሽና ቁምነገሮችን ይዘናል፤ ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ 👇

ብዙ ተለፍቶበት የተዘጋጀ ታሪካዊ ጥንቅር ነውና በትዕግሥት እንድታነቡ እንጋብዝሃለን

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በኤርትራ ጉዳይ መንግስት ከሰሞኑ አቋም መቀየሩን በሚያሳብቅ መልኩ በቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ሻዕቢያ እና የኤርትራዉን መሪ ኢሳያስ አፈወርቂን የሚያጥላሉ ዘገባዎችን እያሰራጨ ነው። እነዚህን ለዉጦች እንዴት አዩአቸዉ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በእዉነቱ በጣም አሳዛኝ የዲፕሎማሲ ዉድቀት ነው። ሲጀመርም ጭፈራና ሆያ ሆዬዉ ከጥላቻ የመነጨ ነው እንጂ ተጨባጭ እና ግልጽ ስምምነት እና አቅጣጫ ስለተቀመጠ አልነበረም።

ከመጀመሪያውም ሕገመንግሥቱን ተቋማዊ አሰራሮችንና አለም አቀፍ መርሆችን የተከተለ ስላልነበረ ይህ ቀን ሊመጣ እንደሚችል የሚጠበቅ ነው የነበረዉ። እዉነት ለመናገር ከኤርትራ ጋር ሐገራችን ጤናማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቢኖራት የሚጠላ ጤናማ ኢትዮጵያዊ የለም።

ነገር ግን የኤርትራ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢሱ ኢሱ” እንደሚሉት በቀላሉ የሚፈታ አልነበረም፣ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራውያን ያለቁበት ጉዳይ ነው። በከፍተኛ ብስለት፣ ጥንቃቄና ተቋማዊ በሆነ መንገድ መያዝ የነበረበትን ጠቅላይ ሚኒስተሩ እና መንግስታቸዉ በተከተለዉ የተሳሳተ አካሄድ ሐገሪቷ ዋጋ ከፍላለች።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ ነው የሚባለዉ ጃል መሮ (ኩምሳ ዲሪባ)፣ በአንድ ቃለምልልስ ላይ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የገባነዉ ተደራድረን ሳይሆን እንደ ምርኮኛ ነው ብሏል። ከፋኖ መሪዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ዘመነ ካሴም ኤርትራ የነበረ እንደሆነ ይታወቃል።

በእነኝህ ግለሰቦች የሚመሩ እንቅስቃሴዎች ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የሚገባቸዉ ትኩረት ተሰጥቶ በቂ ድርድር ተካሂዶ ወደ ሰላማዊ መሥመር የሚመጡበት መንገድ ተዘርግቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ምናልባት የትጥቅ ትግልን አማራጭ አያደርጉም ነበረ።

ከዛ ባለፈ ሻዕቢያ የተዋጋዉ ከኢትዮጵያ ጋር ሆኖ እያለ ከትግራይ ጋር ብቻ ይመስል፣ በተለይ የፈደራሉን መንግስት የሚመሩ አካላት፣ ሕወሓት እና ትግራይን ለማብሸቅ ተንቀሳቅሰዋል። ትግራይን ገፍተዉ፣ ኢሳያስ አፎርቂን ጎንደር፣ አርባ ምንጭ፣ ጂንካ፣ ጅማ እና አየር ሐይሉን ሳይቀር አስጎብኝተዉታል፣ በወቅቱ ትግራይ ተገፍታ ነበር።

ይህ ሕገመንግሥታዊ ያልሆነዉ አካሄድ፣ የትግራይን ጦርነት ከወለዱ ምክንያቶች አንዱ ነው። ግንኙነቱ ተቋማዊ ካለመሆኑም በላይ የትግራይ መገፋት፣ ኢትዮጵያን አክስሯል፤ ምክንያቱም ሻዕቢያን ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ የትግራይ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በመንግሥት በመገፋታቸዉ እዉቀታቸዉን መጠቀም አልተቻለም።

በትግራይ ጦርነትም ሻዕቢያ እንዲገባ መደረጉ ከባድ ስህተትና ጦርነቱ ከቁጥጥር ዉጪ እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ነው። ከፕሪቶሪያ ስምምነት በሁዋላም በአማራ ክልል ጦርነት ሲጀመር የሻዕቢያ እጅ የማይናቅ ሚና እንደነበረዉ የአደባባይ ምስጢር ነው።
ስለዚህ በኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከባድ ኪሳራ ኢትዮጵያ አስተናግዳለች።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት ከለዉጡ በሁዋላ በተጀመረው የኢትዮ_ኤርትራ ግንኙነት ስኬት የሚሉት ነገር የለም?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በመጀመሪያ አካባቢ የተለያዩ ቤተሰቦች ሲገናኙ ማየት አስደሳች ነበር፤ ከዛ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የተሸለሙት የኖቤል የሰላም ሽልማትም ተስፋ ሰጪ ነበረ፣ ግን ሽልማቱ ግቡን የሳተ ይመስለኛል አሁን ላይ እርሳቸዉም በተሳሳተ ፖሊሲያቸዉና ሲንከባለሉ በመጡ የኢትዮጵያ ችግሮች ምክንያት ጦርነት ዉስጥ ተዘፍቀዋል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦በአጠቃላይ ጠቅለል አድርገን ሰናየዉ ከለዉጡ በኃላ ከኤርትራ ጋር የተጀመረዉ ግንኙነት ትርፍ ሳይሆን ኪሳራዉ አመዝኖ ተቋጭቷል እያሉ ነውና በተጨባጭ ለዚህ ዉድቀት የዳረጉ የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃዎች ምን ምን እንደሆኑ ቢጠቅሱልን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የለዉጥ ኃይል ነን ባዮች ሕወሐትን እና የትግራይን ሕዝብ ማብሸቅ መፈለግ ነው፣ ይህ የብሽሽቅና የእልህ ፖለቲካ ከባድ ዋጋ አስከፍሎናል። የኢትዮጵያ አካል የሆነችዉን ትግራይን በመግፋት ከሻዕቢያ ጋር መተቃቀፍ ዋጋ አስከፍሏል። ተቋማዊና ሕገመንግሥታዊ የዲፕሎማሲ ሥራ አለመሠራቱ ዋጋ አስከፍሏል።

የትግራይን ጦርነት ከጠነሰሱ ኃይሎች አንዱ ሻዕቢያ ነው፣ አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ቀዉስ በኢትዮጲያ መንግስት ሻዕቢያ በኢትዮጵያ የዉስጥ ጉዳይ ላይ እንዲገባ መደረጉ የአንበሳዉን ድርሻ ይወስዳል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት ያኔ በኢትዮ_ኤርትራ ጦርነት ጊዜ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ጦር አስመራን ለመያዝ ሲሄድ ባይመልሱ ኖሮ ዛሬ ሻዕቢያ ለዚህ አይበቃም ነበር የሚሉ ወገኖች አሉና የእርሱዎ ምልከታ ምንድነው ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አሁን ላይ ሻዕቢያ በሐገራችን ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የፈተፈተበት ዋነኛዉ ምክንያት የብልጽግና መርህና ሞራል እንዲሁም ሕገመንግሥት አልባ ፖለቲካ ነው። ወደ መለስ ዜናዊ ጉዳይ ስንመለስ በርግጥ የኢትዮጵያ ጦር በወቅቱ አስሠራን መያዝ አያቅተዉም ነበር። የአሰብን ወደብም እንዲሁ፤ ግን አንድ ሉአላዊ ሐገር ገብተህ ለመዉረር፣ እንደኛ አይነት ደሐ ሐገር በኢኮኖሚም፣ በአለምአቀፍ ጫናም አንጻር ከአቅም በላይ ነው።

ሌላዉ ሻዕቢያ ወደ ጎሬላነት እራሱን ቀይሮ በመፋለም አላስፈላጊ ዋጋ ማስከፈሉም አይቀርም፣ ከዛ ዉጪ ሽብርተኛዉንና የአልቃይዳ ክንፍ የሆነዉን አልሸባብን ለመዉጋት ሱማሊያ እንደመግባት፣ ኤርትራ መግባቱ ቀላል አይደለም።

ነገር ግን የመለስ ሁዋላም የኃይለማርያም No war No peace ፖሊሲ ሻዕቢያ ልኳን እንድታዉቅና በኢትዮጵያ ላይ ሽንቷን ለመሽናት የምትመኘዉን ከንቱ ያደረገባት ነበረ። አሁን ሰሞኑን መንግስት ወደዛ ለመመለስ ያሰበ ይመስላል። የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒሰትር ግን በኤርትራ ላይ ተከርችመዉ የነበሩ በሮችን የኤረትራ አምባሳደር ነኝ እያሉ አስከፍተዋል፣ ምናልባት መልሶ ማስከርቸም ሊኖርባቸዉ ይሆናል ከቻሉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ የኢትዮጲያ መንግስት አሁን ላይ ቢከተል የሚሉት አቅጣጫ ቢጠቁሙንና ብናበቃ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የመጀመሪያው ሕገመንግሥቱን፣ በማክበርና በማስከበር የሻዕቢያ ጣልቃ ገብነት መግታት። ሁለተኛው የፕሪቶሪያን ስምምነት በሙላት መተግበር። ሶስተኛዉ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ሕገመንግሥቱን ያከበረ የሰላም ስምምነት መፈራረም።

አራተኛው ከኤርትራ ጋር የቃላት ጦርነት ዉስጥ አለመግባትና ችላ ማለት፤ ከእንግዲህ ግንኙነቱ ከቀጠለ በተቋማዊ መንገድ ማድረግ። አምስተኛ፦ በተለይ ሻዕቢያን በደምብ የሚያዉቁ የትግራይ መከላከያ፣ የደኅንነት እና ፖለቲካ ሰዎችን ቦታ ሰጥቶ እዉቀታቸዉን መጠቀም ያስፈልጋል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Ethiopiadefenceforce

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን። 👇