ባለፈው በተከሰተው አደጋ የተቃጠለው የዎላይታ ሶዶ መርካቶ ገባያ በዘመናዊ መንገድ መልሶ እንዲተካ የሚያስችል ዲዛይን ለምክርቤት መቅረቡ ተገለፀ
የዎላይታ ሶዶ ከተማ ምክር ቤት 2ተኛ ዙር 8ተኛ ዓመት 2ተኛ መደበኛ ጉባኤ አካሄደ።
ምክር ቤቱ በጉባኤው የባለፈው ጉባኤ ቃለ ጉባኤን ማጽደቅ፣ የከተማ አስተዳደሩን የግማሽ በጀት ዓመት አፈፃፀም መገምገም፣ የመርካቶ ገበያ መልሶ የማልማት ግንባታ ዲዛይን ማጽደቅ፣ ተጨማሪ ሁለት የከተማ ቀበሌያት በማዋቀር ፕሮፖዛል ላይ መወያየት፣ ሹመትና የመሳሰሉትን እንደ አጀንዳ አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ የሆኑት ወ/ሮ ታልጎሬ ታደሰ ጉባኤውን ባስጀመሩበት ንግግራቸው እንደገለፁት ምክር ቤቱ ከከተማ አስተዳደርና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት የሰፊውን ህብረተሰብ ፍላጎትን ባገናዘበና ለህዝቡ ጥቅም ይሆናሉ በተባሉ በማህበራዊ፣ ኢኮኖመያዊና አስተዳደራዊ ዘርፎች በበጀት ዓመቱ ብዙ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በዚህም የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ ትጋትና ታማኝነት ፍፁም የህዝብ ወገንተኝነት አስፈላጊ በመሆኑ የአስፈፃሚ አካላትን ቀርቦ በማወያየት እየተከታተለን በመደገፍ፣ የህዝብ የሆኑ ጥያቄዎችን ከሚመለከታው ጋር በመናበብና በጋራ በመሆን የተከናወኑ ተግባራት ፍሬያማ እንደነበሩና ለዛሬው አፈፃፀምም ግብዓት እንደ ነበሩም ወ/ሮ ታልጎሬ አውስተዋል፡፡
በመሆኑም ባለፉት ጊዜያት የተሰሩ ሥራዎች ለህዝብ ጥቅማ ብቻ ያተኮሩ ናቸው ያሉት አፈ ጉባኤዋ ዛሬም እንደ ትላንቱ ጠንካራውን በማስቀጠል ውስንነት የታየባቸውን መስኮችን በማረም ለህዝብ የሚናሳየው ወገንተኝነትና ታማኝነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
አቶ ዘካሪያስ ታደሰ የዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ለምክር ቤቱ የአስተዳደሩን ግምሽ በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በከተማ ዐቀፍ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች የተሰሩ የተለያዩ ዘርፍ ተግባራትን በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡
በከተማ መሰረተ ልማት ማስፋፍያ ስትራቴጂ ዕቅድና አፈፃፀም፣ እየጨመረና እያነረ የመጣውን የገበያ ሁኔታን በተመለከተ እንደ ሶዶ ከተማ የተሠሩ የገበያና ንግድ ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን፣ ከሁሉም በላይ ትኩረት ስለሚሰጥ ጉዳይ ማለትም ሰላምን የማስጠበቅና ፀጥታን በተመለከተ በከተማው በህብረተሰቡና ፀጥታ አካላት የተሠሩ አኩሪ ተግበራትንም ከንቲባው በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡
ከንቲባው አያይዘውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበና እየጨመረ የመጣው የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ እንደ መፍትሔ የተሠሩ በርካታ ተግባራትን፣ እንደ ሀገር አሳሳቢና መልካም አስተዳደር ችግር ይሆናል ተብሎ የሚነሳውን የስራ አጥ ወጣት ሥምሪትን በተመለከተ የተሠሩ ሥራዎች፣ በአለም ደረጃ ስጋትን ስለፈጠረው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና እስካሁን እየተደረገ ስለሚገኘው ጥንቃቄ፣ ሳይታሰብ በመከሰቱ ተደራራቢ ተግባርና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስለከተታው ስለ መርካቶ ገበያ ድንገተኛ እሳት ቃጠሎ ፣ በዚም በከተማው ስለተከሰተው የገቢ ምንጭ እጥረት፣ የመሳሰሉትና ሌሎች የየሴክተሩ ተግባራትን በማንሳት ከንቲባው አቶ ዘካሪያስ ለምክር ቤቱ ሰፋ ያለ ማብራርያና ገለፃ አድርገዋል፡፡
በተለይ የከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ ተግባራትን በተመለከተ ህብረተሰቡ ከተቋሙ የሚያገኘው አገልግሎት ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በመሆን የህዝቡን ጥያቄም የሚመለስ ሊሆን እንደሚገባ በማመን ሴክተሩ ለተሳለጠ አገልገሎት አሰጣጥ ዝግጁ እንዲሆን በማድረግ የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ መምጣቱንም ያነሱት ከንቲባው በቀጣይነትም በሂደቱ በሚገጥሙ ችግሮች ዙሪያም በቅርበት እየተናበቡና አቅጣጫ እያስቀመጡ እንደሚሄዱ ገልፀዋል፡፡
በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያም የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ብዙ ሲሠራ መቆየቱን ያነሱት ከንቲባው አሁንም መልኩን እየቀያየረና እያደገ ከመጣው ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር ተያይዞ በየሴክተሮች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችም እንደሚኖሩ በማመን በቀጣይነት ችግሮችን በየፈርጁ በመለየት ለመመለስም ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል ከንቲባው አቶ ዘካሪያስ፡፡
የምክሩ ቤቱ ሶስቱ ቋሚ ኮሚቴዎችን ለምክር ቤቱ አባላት የየተቋማት ግምገማ ግብረ መልስ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ጠንካራ ደካማና ወደ ፊት ሊሻሳሉ በሚገቡ ጉዳዮች ትኩረታቸውን አድርገዋል፡፡
በተለይ በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ህብረተሰቡ ፍትሐዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል፣ በዚህም የዋጋ ንረት፣ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ተደራሽነትና ፍትሐዊነት፣ የገቢ አሰባሰቢና አጠቃቀም፣ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት፣ ህጋዊ የንግድ ሥርዓት መዘርጋትና በተያያዙ ጉዳዮች ግብረ መልስ ሰጥተዋል ሲል የከተማው ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ዘግቧል።