1000030274

ከዚህ በኃላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማስተካከል አልረፈደም ? ምናልባት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ጠልፈዉ የራሳቸዉን አላማ የሚያስፈጽሙ ኃይሎች ይኖሩ ይሁን ? ይሄ መንግስት የኦሮሞ መንግሥት ነው ማለት ይቻላል ? የትግራይ እና የዎላይታ ግንኙነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዴት እንደ ስጋት ታያቸው ? የኦሮ-ማራ ጥምረት በብሄር ብሄረሰቦች ላይ ያመጣው ዳፋ እንዴት ይለካል ? በርካቶች እንደሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ዳንኤል ክብረት ምክር ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ስጋት እየፈጠረ ነውን ? …… የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ያልተመለሱ ሀገራዊ ቀጠናዊ ጥያቄዎች ምላሽና ቁምነገሮችን ይዟል፤ ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ 👇

ብዙ ተለፍቶበት የተዘጋጀ ታሪካዊ ጥንቅር ነውና በትዕግሥት እንድታነቡ እንጋብዝሃለን🙏

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ከለዉጡ በኃላ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር ስር የቀድሞ ደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል ሕዝቦች፣ አመራሮች አሰላለፍ ምን ይመስላል ? እዉን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ዎላይታን ስልጣን ከመያዛቸውም በፊት ይጠላሉ ? አሁን ኢትዮጵያ ለገባችበት ዉድቀት ሆነ ለዎላይታ ሕዝብ መገፋት የደቡብ አመራሮች ሚና ምንድነው ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሚያ ሰው ናቸው፣ እንደሚታወቀው ደግሞ በታሪክ አርሲና ጅማን ብንወስድ እንኳን ከዎላይታ ጋር ነገስታቶቻቸዉ በሰላም ለመኖር ልጆቻቸዉን ይድሩ ነበር። ከዛም መለስ ሲል ከሜጫና ቱለማ ማህበር ጀምሮ አብረዉ የሚታገሉ በመሆኑ አንዱ ለአንዱ ትግል እዉቅና የሚሰጡና አብሮ የመሥራትም ሆነ የመኖር ችግር የሌለበት ነው ማለት ይቻላል።

ለዚህ ማሳያዉ በኦሮሚያ የሚገኙ ዎላይታዎች ብዛት ነው፥ በዎላይታም ብዙ ኦሮሞዎች ይገኛሉ። ሕዝቦቹ በኢኮኖሚ ትስስር የተጋመዱ በብዛት የተጋቡና የተዋለዱ ናቸው። ለዛም ይመስላል አንድ ከኦሮሚያ የሚመጣ ሰው ከመሬት ተነስቶ ዎላይታን ይጠላል ብዬ የማላስበዉ። በነገራችን ላይ በአዋሳ እና አካባቢዉ በዎላይታ ተወላጆች ላይ ጥቃት በደረሰበት ወቅት ተፈናቃዮችን ሲጎበኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልቅሰው ነበረ።

ከዛን ጊዜ ጀምሮ በሐገሪቷ ከፍተኛ ትርምስ ነበር በየቦታው፣ በዚህ መሐል ቦታ ያገኙ የደቡብ አመራሮች የዎላይታ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መዉጋት የሚፈልግ፣ በሕወሓት የሚላክ፣ ጥያቄዎች የሚያነሳው ችግሩን ለመቅረፍ ሳይሆን ለዉጡን ለማደናቀፍ እንደሆነ እየተደረገ መረጃ ይሰጣቿል።

ታሪክ እየተጣመመ፣ መረጃ በተንኮል እየተቀመረ ይሰጣቿል። ለምሳሌ የዎላይታ ሐገር ሽማግሌዎች ሶስቴ ከቤተመንግስት በር የተመለሱት በዚሁ የደቡብ ሊህቃን ሕወሓት ነው የሚልካቸዉ በሚል ተንኮለኛ የሐሰት መረጃ ነው። እነኝህ በራሳቸዉ የማይተማመኑ insecure የደቡብ አመራሮች የዎላይታ ተወላጅ ከመጣ ያገኘነዉን ቦታ እናጣለን፣ አስፈላጊነታችን ያቆማል ብለዉ ያስባሉ።

እናም ሕዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ስጋት እንደሆነ አድርገዉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባሉ፣ ለምሳሌ የዎላይታ ሕዝብ የሕወሓት፣ የሸኔ እና የፋኖ ተላላኪ ተብሎ ሶስት የተለያዬና የተራራቀ አላማ ካላቸዉ ኃይሎች ጋር እንዲፈረጅ አስደርገዋል። የዎላይታ ሕዝብ የሚያደርገውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሙሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመጥላት እንደሚያደርግ አድርገዉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባሉ።

በዋናነት ከዚህ የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ስለ ዎላይታ ሕዝብ ትክክለኛ ግምገማም ሆነ አመለካከት ያላቸዉ አይመስለኝም። ለሐገሪቷ ዉድቀት ደግሞ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ አካላት እነዚህ የደቡብ አመራሮች ይጠቀሳሉ፣ ምክንያቱም ከዎላይታ Phobiaቸዉ ተነስተዉ ከሚያቀርቡት በተንኮል የታጨቀ መረጃ ባለፈ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ግምባሩን ከማንበብና መስማት የሚፈልገዉን ከመናገር የዘለለ ሚና የላቸዉም፤ የሚጠቅመዉ ግን ጠቅላይ ሚኒሰትሩን ሞግተው ሐሳብ እስከማስቀየር የሚደርስ ሰው ቢኖር ነበረ።

የደቡብ አመራሮች በዚህ ሁሉ ዉጥቅጥ ዉስጥ ፈሪ፣ አስመሳይ፣ በራሳቸዉ የማይተማመኑ፣ ተንኮለኞች፣ ግምባር አምባቢዎች፣ አቅመቢሶች በመሆናቸዉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ላይ ከሚሆኑ ባይኖሩ የተሻለ ነው። ሌላዉ ከደቡብ አሁን ብልጽግና ዉስጥ ያሉ አቅም ያላቸዉ ግን ተገቢ ቦታ የተነፈጉ የሲዳማ፣ የስልጤ፣ የጉራጌ፣ የሐዲያ፣ የከምባታና የሌሎችም አመራሮች እንዳሉም መዘንጋት የለብንም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ይሄ መንግስት የኦሮሞ መንግሥት ነው ማለት ይቻላል ? ያልተመለሰ የኦሮሞ ጥያቄ የለም እነ ዳንኤል ክብረት የሚሉትን እንዴት ታዬዋለህ ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አየህ ይህ መንግስት የኦሮሞ አይደለም። ከጥንስሱም ኦሮ_ማራ በማለት የተዋቀረ ነው፣ ሐገሪቷን ለዚህ ሁሉ ቀዉስ የዳረጋትም በግምባር ቀደምትነት ይሄዉ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ መብት የሚከበረው ከብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር አንድ ላይ መሆኑን ከእነ ጀግናዉ ባሮ ቱምሳ ጀምሮ የተናገሩት ሐቅ ነው። አሁን ኦሮሞዎችን ከፊት በማድረግና የተወሰኑ ጥያቄዎቹን በመመለስ፣ የተቀሩ ጭቁን ብሔሮችን ለዘዉድ ናፋቂዎች ቅዥት አሳልፎ የመስጠት አካሔድ ነው ያለዉ፣ ጫና ለማሳደርም የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የጥላቻ ቅስቀሳ እንዲደርስበት እየተደረገ ይገኛል።

ዳንኤል ክብረት የዘዉድ ናፋቂነት መሰሪ አላማዉን ከጀርባ ሆኖ እያስፈጸመ ስለሆነ፣ ለዛ ነው በኦሮሞ መደበቅ የሚፈልገዉ። ሲጀመር ይህ ግለሰብ የትግራይን ሕዝብ እንደ ታዝሜኒያ (ከደቡብ አዉስትረሊያ ጥቂት ሰዎች ሲቀሩ የጠፋ ሕዝብ)፣ ለማጥፋት የሚመኝ ከንቱ ሰው ነው።

አንድ ድሮ የሮም ነጉስ ነበረ ካሊጉላ የሚባል ሰው ተናዶ፣ “ምን አለ የሮም ሕዝብ አንገት አንድ በሆነና በቀነጠስኩት” ብሏል ይባላል። ዳንኤል ክብረት ኢትዮጵያዊዉ ካሊጉላ ነው። ይህ ሰው ስለትግራይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤናማ ነገር ያማክራል ማለት እብደት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለትግራይ በትግራይ ሰዉ ጋር ነዉ መመካከር ያለበት። ሌላዉ ይህ ግለሰብ አሁን ኦነግ፣ በኦነግነቱ አያስፈልግም የሚል ለሕዝቡ እኔ አዉቅልሐለዉ የሚል መሰሪ ጸረ ዲሞክራሲያዊ አቋም ያለዉ ሰዉ ነው።

ግለሰቡ ስለዎላይታም አጠቃላይ ስለብሔሮች መብትም ጥሩ አመለካከት የለዉም። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐገሪቷን ወደ ሰላም መመለስ ከፈለገ፣ እነኝህንና የመሳሰሉ ሰዎችን ከዙሪያዉ በማራቅ፣ ቀናነት፣ እዉቀትና ሕገመንግሥታዊ አመለካከት ባላቸዉ ሰዎች መተካት አለበት።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት ታዋቂዉ ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን መንግስት ጠልፈዉ የራሳቸዉን አላማ የሚያስፈጽሙ ኃይሎች አሉ ብለዉ እርሶም ያምናሉ ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በትክክል የእርሳቸዉን ሐሳብ እጋራለሁ። በነገራችን ላይ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከአገዛዙ ጋር ከሰላማዊ መድረክ ልዩነት እስከ ጫካ የዘለቀዉ ልዩነታቸዉም ላይ የኦሮ_ማራ የተቃወሰ የፖለቲካ አካሄድ አንዱ ምክንያት ነው። ይህ መንገድ ልክ ካለመሆኑም በተጨማሪ የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅምና መብት በዘላቂነት አያስጠብቅም ነው የሚሉት። በትንሹ የትግራይን ጦርነት ኦነግና ኦፌኮ አልደገፉም ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ጦርነቱ አይጠቅመዉም ብሎ ከማመን የሚነሳ ነው።

ጦርነቱን የፈጠሩ ኃይሎችን ክፉ አላማ ከመገንዘብ የሚነሳ ነው፤ ኢዜማና አብን ግን ከድጋፍ አልፈዉ ዘምተዋል። ይሄ ማለት ግን የኦሮሚያ ብልጽግና ከደሙ ንጹ ነው ማለት አይደለም፣ አምነዉበት እንጂ ምንም ተገደዉ የሚወስኑት ዉሳኔ የለም፣ አንዳንዴ የጠለፈዉ ማነዉ የሚያስብሉ ጉዳዮችም አሉ።

በዚህ መሐል ግን አሁንም የደቡብ አመራሮችን፣ ቦታ ይዘዉ ከዎላይታ ጥላቻ አንጻር ብቻ እየቀመሩ እና ኦሮ_ማራ ምን ብንል ይደሰታል እያሉ የሚያደርጉት ተንኮለኛ ተሳትፎ ሚናዉ ቀላል አይደለም። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ሁሉ ዉድቀት የዳረጉ አማካሪ ተብዬና አመራር ተብዬዎችን በጥልቀት በመገምገም የአቅጣጫና አካሄድ ለዉጥ ማድረግ አለበት። እስካሁን የተመጣበት መንገድ አያዋጣም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ከዚህ በኃላ አልረፈደም? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንግዲህም እድል አላቸዉ ብለህ ታምናለህ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በሚገባ እድል አላቸዉ። ወደ ሕገመንግሥታዊዉ መንገድ መመለስ ነው፣ የተገፉ ሕዝቦችን ጉዳይ በአንክሮ ማጤን ነው። አጨብጫቢ ብቻ ሳይሆን ሞጋች ሰዎችን ቦታ እንዲይዙ ማድረግ ነው። መንግስት በግልጽ ወደ ሕገመንግሥታዊዉ አቅጣጫ ከተመለሰ ሐገሪቷም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ተስፋም እድልም አላቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈረሙትን የፕሪቶሪያ ስምምነት ይተግብሩት፣ ከሌሎች የታጠቁ ኃይሎች ጋር ሕገመንግሥቱን ያከበረ የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ቁርጠኛ ይሁን። ምርጫን አይፍሩ በየትኛውም ክልል ሕዝቡ የፈለገዉን እንዲመርጥ ይፈቀድለት፣ በተለይ ብልጽግና ቅሬታ ያላቸዉን ሕዝቦች ጉዳይ በድጋሚ ይመርምር።

በነገራችን ላይ አሁን ሁሉም ነገር ያበቃለት የሚያስመስሉ ኃይሎች አንደኛው፣ ሕገመንግሥቱን መናድ የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ ሁለተኞቹ ደግሞ ሐሳባቸዉ ተሞክሮ የከሸፈባቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ከቀየረ ተረሳን፣ አስታዉሱን ባዮች ናቸው። ኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ያላት ሐገር ነች፣ ሕገመንግሥቱ በተከበረበት ምንም መነጋገር ይቻላል፤ ከዛ ዉጪ የትም አያደርስም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Tigray #Amhara #Oromo

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።