“በኡሁኑ ወቅት ጃዋር የራሱን መንጋ ከብልፅግናው መቀማት የሚችልበት አቋም ላይ አይደለም” ደግሞ “ችግሩን የፈጠሩ ሶስቱ ብሄሮች ብቻቸውን መፍትሔ ይሰጣሉ ማለት በኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ቅዠት ነው”- የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ፖለቲካ ወጌሻ እንግዳ

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥንቅር ነው
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ከሰሞኑ ከ BBC አማርኛ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደነበረ ይታወቃል፣ በዝርዝር የተወሰኑ ነጥቦችን ቀጥለን ከማንሳታችን በፊት አጠቃላይ ቃለ ምልልሱን እንዴት አገኙት?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በአጠቃለይ ቃለ ምልልሱ ብዙ ወሳኝ ጉዳዮች የተነሱበት ነው። ጃዋር መሐመድም በሚዲያ ቀርቦ በዚህ ሰዓት ሐሳቡን ማቅረቡ ጥሩ የሚባል ነው። በተለይ በዋናነት በሐገር ወይንም ኢትዮጵያ ላይ አተኩሮ አዉርቷል ያም መበረታታት ያለበት ይመስለኛል። እንደ ቅሬታ ደግሞ አሁንም ቀድሞም የነበረና የቀጠለዉ የጃዋር ችግር ኢትዮጵያን ከሶስቱ ብሔሮች ማለትም ኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ ጋር ብቻ አያይዞ አዉርቷል። በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሱማሌን ጠርቷል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ጃዋር መሐመድ አሁን በጣም የሚያስጨንቀዉ የሐገር መፍረስ (state collapse ) እንደሆነ አንስቷል፣ በተጨማሪም ሐገሪቷ አሁን ከመስመር ለመዉጣቷ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብቸኛ ተጠያቂ በማድረግ ማለትም ከአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ወደ ግለሰባዊ አምባገነንነት እንዳሸጋገሩ ምልከታዉን አጋርቷል፣ ይሄንን የጃዋርን ሐሳብ ይገዛሉ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የተቀላቀለ ነው፤ እዉነትም፣ ዉሸትም የራሱ የግሉ ምልከታም እና ምርጫም ያለበት ነው አቋሙ በእኔ እይታ። ለምሳሌ የሐገር መፍረስ ስጋት በእዉነቱ ተጨባጭ ነው፣ ግን ጃዋር እራሱምኮ ለዚህ ከመስመር ለወጣ አካሄድ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ኢህአዴግ ከፈረሰ በዛዉ ሐገር እንዳይፈርስ ጥንቃቄ አድርጌያለሁ ከ Arab spring በመማር የሚለዉ ጃዋር፣ ፈተና አዉጥቶ መበተን ፣ በሐገር ላይ የሚያስከትለዉን ተጽዕኖ የገመገመ አይመስልም።
ከለዉጡ በኃላ ኢትዮጵያ መጥቶ ፣አሁን በኢትዮጵያ ሁለት መንግስት ነው ያለዉ የዐብይና የቄሮ ሲልና መንግስት እሱን ሲፈራዉ ለሐገር ፈረሳ ጡብ እያቀበለ እንደነበረ የገባዉ አልመሰለኝም። ጃዋር በሚዲያ የዎልቃይትን ጉዳይ ባናነሳ የአማራ ብሔረተኝነት አይነሳም ነበረ እያለ በኩራት ሲያወራ ነበረ። ያ ችግር አሁን ለሐገር ፈረሳ ከሚያሰጉ ነገሮች አንዱ መሆኑን አሁንም አልገመገመም።
ሌላው ነጥብ በርግጥ ጃዋር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከመጀመሪያውም እንዳልወደደዉና ከኦህዴድ ዉስጥ ከማይመቹት ሰዎች አንዱ እንደነበረ ይነገራል። እንደ ፖለቲከኛ ግን ጃዋር የኦሮሞ ሊህቃንንና የኦህዴድ ሰዎችን ማሳመን ያልቻለዉ ሰዉዮ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መገንባት አይፈልግም፥ የግለሰብ አምባገነንነት ነው እያልኩ ነበረ የሚለዉ እዉነት አይመስለኝም።
ባይሆን ጃዋር ለራሱ የነበረዉን የተሳሳተ ግምትም ሳያሳይ አይቀርም፤ በአክቲቨስትነት የኢትዮጵያን መሪ የሚሆን ሰዉ መርጣለሁ ማለቱ የሚገርም ነው (የጃዋር ሚና የሚናቅ ባይሆንም) ሌላዉ እነ ጃዋር በሚዲያ ከዉጭ ቢያስተባብሩትም፣ አመጹን በኦህዴድ ዉስጥ ሆኖ ይመራ የነበረው አንድ ቁጥር እራሱ አብይ አህመድ መሆኑን በልኩ የተገነዘበ አይመስለኝም።
አንድ ጃዋር ያስቀመጠዉ እዉነት የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ተገፎ የመድብለ ፓርቲ ሥርአት አለመምጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ብልጽግና ግን ኦሮ_ማራዊ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ነው እንጂ የአንድ ግለሰብ ብቻ አይመስለኝም።
ለሐገሪቷ ዉድቀት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብዙ ኃይሎች ጋር በጋራ ተጠያቂ ናቸዉ እንጂ ብቻቸዉን አይመስለኝም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ፦ ጃዋር በዚህ ቃለምልልሱ መንግስትን በ priority (ቅድሚያ መስጠት ላለበት ጉዳይ ቅድሚያ ባለመስጠት) ከሷል፣ ይሄንንስ እንዴት አዩት?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሱ ሙሉ በሙሉ የምስማማበት ነው። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ችግሯ የቤተመንግሥት ግምባታ፣ ፓርክና መናፈሻ አይመስለኝም እኔም። በተለይ ጃዋር የስኳር ፋብሪካዎች በመለዋወጫ እቃ እጥረት ሥራ ማቆማቸዉ፣ የባቡርና የተለያዩ ፕሮጀክቶች ቆመዉ መቅረታቸዉን በቁጭት ማንሳቱ ተገቢ ነው። ከዛዉ ጋር አያይዞ ዶላራችን ለድሮን መግዣ መዋለን የተቸበት መንገድም የሚያስመሰግነዉ ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ አሁን ላይ ምርጫ በኢትዮጽያ ቅንጦት ነው ብሏል፣ የሐገራዊ ምክክሩም ላይ የሰላ ትችት ሰንዝሯል፥ ይሄንንስ እንዴት አዩት?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በተለይ የሐገራዊ ምክክሩ ላይ ያቀረባቸዉ ሐሳቦች ዉሐ የሚቋጥሩ እና የእነ ጃዋር ፓርቲ ኦፈኮ እንዲሁም የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄም ጭምር የሚያራምዱት ምክንያታዊ አቋም ነው። ምርጫ ግን አንድ አመት ከምናምን ብቻ ስለሚቀረዉ እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ መቀጠል ስላለበት ጃዋር በዚህ ደረጃ ባያጣጥለዉ ይመረጣል። ብልጽግና ከባህሪዉ እንደምንረዳዉ ምርጫዉ ጋር ከደረሰ በዉድም በግድም ምርጫ ማድረጉ አይቀሬ ነዉ። የሚሻለዉ ጃዋር የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነት ቢተች ጥሩ ነበረ። ነገር ግን በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ያለዉን የጸጥታ ችግር በልኩ አስቀምጧል ለዚህም መመስገን አለበት። የሰላም ስምምነት መኖር እንዳለበትም ተናግሯል። እኔ ግን የበለጠ የሚያሳስበኝ ባለፈዉ ትግራይ ምርጫ እንዳለፋት በቀጣይ አማራ ክልል ምርጫ እንዳያልፍ ያሰጋል።
መንግስት በኦሮሚያ ምርጫ ማድረጉ የሚቀር አይመስለኝም። ግን በተለይ ሐገሪቷ ሰላም እንደሚያስፈልጋት በኢህአዴግ ጊዜ የሕዝቡ ጥያቄ የከተማ፣ የቋንቋና የመሳሰሉት እንደነበረ አሁን ግን የህልዉና መሆኑን መመስከሩ ያስመሰግነዋል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Tigray #Amhara #Oromo
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥንቅር ነው