የዎላይታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ስነ ልቦናዊ፤ ስነ ምህዳራዊ መጎሳቆል ከመቼ ይጀምራል? ዎላይታ በምኒልክ ወረራ ወቅት ምን ይመስል ነበር ? – ከፈረንሳዊ አይን ምስክርነት
(ክፍል አንድ)
ይህ ጸኁፍ በ1896 ዓ.ም ምኒልክ ዎላይታን ሲወር አብሮት የተጓዘው ፈረንሳዊ ጸሃፊና የአይን ምስክር የነበረው ጀግ #ቫንደራሂም /J.G Vanderhem የዕለት ማስታወሻ ሲሆን ስማቸው በምህጻረ ቃል የተገለጸ ዶክተር D.M ከተረጎመው የተወሰደ ነው፡፡

ጹሑፉ ጉምቱ የዎላይታ ባህል አዋቂና ምሁር ለነበሩት ለአቶ ዘብድዎስ ጫማ በነጻ የተሰጠ ስጦታ አንደነበር በትርጉሙ ላይ ተብራርቷል፡፡
ጸሃፊው ስለ ዎላይታ እንደጻፈው ከወረራው በፊት ዎላይታ በፖለቲካው መስክ በራሱ ንጉስ ራሱን በራሱ የሚያስተዳደር ግዛት ነበር፡፡ ዎላይታ በኢኮኖሚው በለምነቱና በልምላሜ የሚታወቅ በመሆኑ ዎላይታዎች በምግብ ራሳቸውን ችለው ይተዳደሩ ነበር፡፡
በባህል ደግሞ ዎላይታዎች ድንቅ ባህልና ቅርስ አንዲሁም የራሳቸው የእምነት ተቋማት ነበራቸው፡፡ በስነ ልቦና ዎላይታዎች ደስተኞች፣ በራስ የሚተማመኑ፣ ጀግና ተዋጊዎች፣ ስትራቴጂስቶች፣ ጠቢባን… እንደነበሩ እንመለከታለን፡፡ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የታሪክ ጥንቅር ላይ፦ ትርጉሙ ከዚህ በታች ቀርቧል መልካም ንባብ!
እንደ ጀ.ግ ቫንደራሂም /J.G Vanderhem ምልከታ የዎላይታ ባህልና ስነ ምህዳር በምኒልክ ወረራ ወቅት ምን ይመስል ነበር?
የዎላይታ ሀገር በጣም ለም፣ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ተክሎች ያሉት፡- ስንዴ፣ ገብስ፣ ቡና፣ ትምባሆ፣ ጥጥና ማሽላ በጎጆአቸው ዙሪያ ተተክሎ ጎጆአቸውም እጅግ በጣም አስውበው ይገኛሉ፡፡ በየገጠሩ ትላልቅ እንጨቶች፣ ፍራፍሬ፣ ዘንባባ፣ ወይራ ስፔንድል ዛፎች በብዛት ይገኛሉ፡፡

በመንገዱ ግራና ቀኝ ከጎጆ እስከ ጎጆ ቆንጆና ውብ ዛፎች ተተክለው ይገኛሉ። ወንዞች በሀረጎች፣ በሚጣበቅ አረሞች እና ቀርከሃዎች መካከል ይፈሳሉ፡፡ የንብ ቀፍ ቅርጽ ያለው ቤቶቻቸው በጥሩ ሁኔታ የተሰራና በጣም ንጽህናቸው የተጠበቀ ነው፡፡
በህዝቡ የተሰሩ የተለያዩ ዕቃዎች ቤቱን አጨናንቀው ይታያሉ፡፡ እነዚህም በጣም ቆንጆ እንስራዎች፣ ከሸክላ የተሰሩ ከበሮ፣ከእንጨት የተሰሩ የቤት ቁሳቁሶች፣ በዶቃዎችና በዛጎሎች ያጌጡ እቃዎች፣ እጅግ ተውበው በቀጭን ሲባጎ መልክ ተወጥረው የተሰሩ የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ (ዲታ) በእህል የተሞሉ ጆኒያዎች፣ የተጠቀለሉ ቃንጫዎች፣ በነጭ ሽንኩርትና በበቆሎ የተሞሉ ከቆዳ የተሰሩ ስልቻዎች፣ ከብረት የተሰሩ ረዘም ያሉና ጠፍጣፋ በኮሮቻ ውስጥ የተሞሉ መነገጃ መሳሪያዎች (ማርጯ) ይገኛሉ፡፡ ይህ መሳሪያ (ገንዘብ) ዎላይታዎች ለንግድ ልውውጥ የሚገለገሉበት ነው፡፡ …. እነዚህ ቅርሶች ሁሉ የሚያመለክቱት ይህ ህዝብ ምን ያህል ጥንታዊና ነባር፣ መሰረታዊ ስልጣኔ ያለው መሆኑን ነው፡፡
በቤታቸው ውስጥ ለዕይታ በሚያመች መልክ በደረጃ በየአይነቱ ተደርድረውና ተሰቅለው የሚታዩ የአንበሳ፣ የነብር ወይም ሌሎች ቆዳዎች ለዚህ ህዝብ አደን ዋና ዋና ተግባሮች መሆኑን ነው፡፡
ሰዎቹ ደስተኞችና ብቃት ያላቸው ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩና ህይወታቸውን በመንፈሳዊ ስርአት የሚመሩ ናቸው፡፡ ዎላይታዎች በካቶሊክ በካቶሊክ ሀይማኖት የሚያምኑ መሆናቸው ንጉሱን በጣም አስገርሟቸዋል፡፡ ንጉሱ ያስቡት የነበረው ዎላይታዎች እስላሞች እንደሆኑ ነበር፡፡ ለወረራ ካነሳሳቸው ምክንያቶች አንዱም ይሄው ነበር፡፡
ቅስና ከጥንት ከአባት ወደ ልጅ እየተላለፈ የመጣ ሲሆን ልማዳዊ (ባህላዊ ) ሀይማኖት ያሏቸው መሆኑን ተረዳን፡፡ አንዳንድ የንጉሱ ወታደሮች ለወረራ በተሰማሩበት ጫካ ውስጥ እንዲያውም ቤተክርስትያንና ምስጢራዊ ድንጋዮችን እንዳገኙ ገለጹልን፡፡
የዎላይታዎች የመቃብር ስርአት ዓይነት ከአቢሲኒያዎች ዘንድ ፈጽሞ አይታወቅም፡፡ በርግጥም አንዳንድ ያየኋቸው የመቃብር ቦታዎች ቆንጆዎች ሲሆኑ በዙሪያቸው የጥላ እንጨቶች ተተክለው በዙሪያው ጉድጓድ ተቆፍሮ በእንጨት ጥላ ስር መሆኑ በርግጥም አስከሬኑን ለእርፍት የተጋደመ ያስመስለዋል፡፡
የሞተው ወንድ ከሆነ በህይወት በነበረ ጊዜ ሟቹ የሚጠቀማቸው መሳሪያዎች ከመቃብር አጠገብ እንጨት አቁመው ይሰቀላሉ፡፡ ሴት ከሆነች ግን ጌጣጌጦቿ በተመሳሳይ መልኩ ይሰቀላሉ፡፡ #ዎላይታዎች አዳኞችና ገበሬዎች ናቸው፡፡ እነሱ ለጦርነት የሚነሱት አገራቸው በወራሪዎች ሊወረር ብቻ ነው፡፡ ከኋላ ቀር መሳሪያዎች መካከል አዘውትረው የሚይዟቸው ሁለት ጦሮች ይገኝበታል፡፡ አንዱን ይዘው ሌላውን ይወረውራሉ፡፡ በወገባቸው የጠላቶቻቸውን አንገት መቀነጠስ የሚያስችል ከባድና በጣም ሹል ጎራዴ ይታጠቃሉ፡፡
የአለቆቻቸው መሳሪያዎች በመዳብና በብር ያጌጡ ሲሆን፣ አንዳንዱ ከባድና ከቆዳ የተሰራ ጋሻ ይይዛሉ፡፡ ዎላይታዎች ዝሆን ማደን ይወዳሉ፡፡ ይሄውም የሚከናወነው በጣም በተቀናጀ ወጥመድ ነው፡፡ ዝሆኑ በሚያልፍበት መንገድ ላይ በጣም የተሳለና ሹል ጦር ተወጥሮ በእንጨት ቅርንጫፎች የተሸፈነና ተስፈንጥሮ ሊወጋውና ሲወድቅ ይጠባበቁ የነበሩ አዳኞች ተረባርበው ይገድሉታል፡፡
የዎላይታ ወንዶች አጭር ቁምጣ (ሱሪ) ሲታጠቁ በወገባቸው ሸማ ያገድማሉ፡፡ ሸማቸው በወፍራም ማግና ድር የተሰራ ሲሆን ጥለቱም ጥቁር፣ ቀይ፣ ሰመያዊ ወይም አረንጓዴ መልክ ያለው ነው፡፡ ይህ ልብስ በአጠቃላይ ከአፈሩ መልክ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ የሀገሩ አፈር ነጣ ያለ ቀይ ነው፡፡
ሀብታቸው የእህል ምርት፣ ከብትና በአብዛኛው የባሪያዎች ብዛት ነው፡፡ እነዚህ ምርቶች ለንግድ ልውውጥ የሚጠቀሟቸው ናቸው፡፡ …


ዎላይታዎች እጅግ በጣም በጀግንት የአቢሲኒያ ወታደሮች ስለተቋቋሙ ንጉሳቸውን ጦና በቀላሉ ለመያዝ አልተቻለም፡፡ ጦርነቱ የተጠናቀቀው ንጉስ ጦና ክፉኛ ቆስሉ ከተያዘ በኋላ ነው፡፡ ……….” ይቀጥላል።
ይህ ከላይ በዎላይታ ታይምስ ታሪክ ጥንቅር ላይ የቀረበው ጽሁፍ በ1896 ዓ.ም ምኒልክ ዎላይታን ሲወር አብሮት የተጓዘው ፈረንሳዊ ጸሃፊና የአይን ምስክር የነበረው ጀግ ቫንደራሂም /J.G #Vanderhem የዕለት ማስታወሻ ላይ ዎላይታ በምኒልክ ወረራ ወቅት ምን ይመስል ነበር የሚለውን ሲሆን ስማቸው በምህጻረ ቃል የተገለጸ ዶክተር D.M ከተረጎመው የተወሰደውን ለዛሬ ክፍል አንድ አቀረብን ….. ክፍል ሁለት ይቀጥላል። በቅርቡ ይጠብቁ 🙏
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
#Ethiopia #southethiopia #Wolaita #KingTONA #Minilik