የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ፖለቲካ ወጌሻ እንግዳ፦ በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ከሰሞኑ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከ47 የመንግስት ዩኒቨርስቲ ፕረዚዳንቶችን ከየቦርድ ሰብሳቢዮቻቸዉ ጋር አዲስ በወጣዉ የዩኒቨርስቲ በጀት እና ቀጣይነት በዉጤት ብቻ የሚመዘንበትና ካልሆነ ወደ ማሰልጠኛነት የሚወርዱበት አሰራር የሚደነግግ ዉል እያፈራረሙ እንደሆነ በመንግሥት ሚዲያዎች ተዘግቧል።
ይህንን ሕግ እንዴት ያዩታል ? የእዉነት የትምህርት ጥራት ለማምጣት ነው ወይስ የድሮ ሥርዓቶች ተንኮል ለማጽናት? ሕጉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክና ሕገመንግሥት ያገናዘበ ነው ? በዚህ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ምልከታዎትን ቢያጋሩን?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በመጀመሪያ በጣም ወሳኝና ታሪካዊ ጉዳይ ላይ አስተያዬት እንድሰጥ እድሉን ስላመቻቻችሁልኝ ሚዲያችሁን ከልብ አመሰግናለሁ። በመቀጠል ይህ አዲስ ወጣ የሚባለዉን ሕግ (ዉል) ከመገምገማችን በፊት ጥሩ ሕግ እራሱ ምን እንደሆነ በይነን ብንጀምር የተሻለ ይመስለኛል። ጥሩ ሕግ የሚባለዉ ጽንሰ ሐሳብ በሕግ ፍልስፍና ( Jurisprudence or philosophy of law ) ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የሚዉል ሐሳብ ነው።
የሕግ ፍልስፍና ማለት ደግሞ በራሱ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን በአጭሩ ሕጉ ምንድነዉ ምንስ መሆን አለበት። ምንንስ እንዲያመጣ ታልሞ ይቀረጻል፣ ምንንስ ከግምት ዉስጥ ማስገባት አለበት፣ የሚለዉንና የመሳሰሉትን ነገሮች የሚያመለክት ነው።
ወጥ ብያኔ ማስቀመጥ ባይቻልም፣ በአብዛኛው የሚያስማማዉ አንድ ሕግ ጥሩ የሚባለዉ የሚከተሉትን ሲያሟላ ነው ማለት ይቻላል፥ ሕጉ ለሕዝብ ጥቅም እንዲቆም ተደርጎ መቀረጽ አለበት፤ ሕጉ ማዳላት የለበትም ማለትም ለሁሉም በእኩልነት መተግበር አለበት፣ ሕጉ ምክንያታዊ መሆን አለበት፣ ለሕዝቡ ግልጽ መደረግ አለበት ቀጥሎ ሊተዳደርበት ስለሆነ ለሕዝቡ ( ለአካዳሚክ ማህበረሰብ ሊሆን ይችላል ) ግልጽ መደረጉ፣ መተግበር የሚችል፣ መቀየርም የሚችልና የመሳሰሉትን ጨምሮ መጥቀስ ይቻላል።
በተለይ ምክንያታዊ እና ፍትሐዊ ሕግ ነው ወይ የሚለዉ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሐገሪቷ ሕገመንግሥት መርሆዎች ጋር መጣረስ የለበተም። ይህ ሕግ ተቋማትን ያወዳድራል፣ እኩል ያልተከፈቱትን እኩል ያወዳድራል። ለምሳሌ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እነ ፖልተር ጋትን የሚያሸንፈዉ ዉድድሩን እኩል ጀምሮ ነው።
በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች እኩል አልተከፈቱም፣ በሐገራችን ደግሞ እነዛ ነገሮች በብሔር ጭቆናና ሸፍጥ በመነዳት የተደረጉ ናቸዉ። የማደግ እድላቸዉም እኩል አልነበረም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ፣ እነዚህ ነገሮች ከግምት ዉስጥ መግባት አለባቸዉ። ያ ካልሆነ የቀደሙ መንግስታት የሰሯቸዉን ስህተቶች ማጽናት ነው የሕጉ አላማ የሚሆነዉ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ለምሳሌነት የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ወይንም አጠቃላይ የዎላይታ አካባቢ ላይ በቀደሙት መንግስታት ተፈጽሟል ብለዉ የሚያስቡት በደል አለ? አሁን የሚወጡ ሕጎች ታሳቢ ማድረግ የሚገባቸዉ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በሚከፈትበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥያቄ ቀረበላቸዉ፣ በፓርላማ “ለምን ዎላይታ ሶዶ ላይ ዩኒቨርስቲ ይከፈታል፣ አዋሳና አርባምንጭ ላይ በቅርበት እያለ ?” የሚል ነበር ጥያቄዉ። መለስ ዜናዊም “ዉሃ የሚቀዳዉ ከምንጩ ነው” በማለት የሐገሪቷን ሶስት መንግስታትን የዘለቀ እንቆቅልሽ የፈታበትን ምላሽ ሰጠ። በርግጥ ከዛ በፊት መለስ ዜናዊ በነ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ተክለወልድ አጥናፉ፣ ተሾመ ቶጋ ጋር ባለዉ ግንኙነት የእዉቀት ሰዎች መሆናቸዉ ተጽዕኖ አሳድሮበት ይሆናል።
በርግጥ በጀነራል ዊንጌት የሚያዉቃቸዉ በአጼ ኃይለስላሴ የተሸለሙት ጓደኞቹ እነ ቢሾፕ ዳዊት ጦሼ ትዝ ብለዉትም ይሆናል። በርግጥ በዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ግምባር ቀደም የነበሩት እነ ሰለሞን ዋዳ እና ሎንዶን ካንኮ ትዝ ብለዉት ይሆናል። በርግጥ በዘመነ ስልጣኑ እጅግ የፈተነዉ፣ ይቅርታ እንዲጠይቅ ያስገደደዉ፣ በእዉቀት
የተመራዉ የዎጋጎዳ ትግል ትዝ ብሎትም ይሆናል ።
….. ነገር ግን የመለስ ዜናዊ መልስ ከዛ ያለፈ ትርጉም ያለዉ ነው የነበረዉ፣ በዉስጡም ለጠያቂዎቹ ብዙ መስቀለኛ ጥያቄ ያዘለ ነው። ቀድሞ ነገር በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ሳይከፈት እስከ 1999 ዓ.ም የዘለቀዉ በፖለቲካ ሸፍጥ መሆኑን አታዉቁም ወይ የሚል ነው ? ጭሰኝነት ለማጥፋት ባበረከተዉ አስተዋጽኦ ቂም ተይዞበትና እና የነገ ተስፋዉ ተጠልቶ ዋዱ መዘጋቱን አታዉቁም ወይ የሚል ?
በዎላይታ የተጀመረዉን የግብርና ልማት ወደ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ዳዉሮና ኮንታ ለማስፋት ጥናቱ አልቆ በደርግ የሰብአዊ መብት ጥሰት ብዛት፣ ለጋሾች ገንዘብ በመከልከላቸዉ አለመተግበሩ በሚያስቆጭበት ደርግ ዎላይታ ብቻ ይለማል እንዴ ብሎ ዋዱን የዘጋዉ በጤናማ አስተሳሰብ ነበረ ወይ ?
በዎላይታ ዙሪያ ዩኒቨርስቲዎች ሲከፈቱ የነበሩት በዎላይታ እንዳይከፈት መሆኑን አታዉቁም ወይ? ዩኒቨርስቲዎቹንስ ሲያንቀሳቅስ የነበረዉ አብዛኛዉ ኃይል ከዎላይታ እየሄደ መሆኑ እየታወቀ በቀየዉ ያልተከፈተዉ በብሄር ጭቆና ምክንያት እንደሆነ አይገባችሁም ወይ ?
የኢትዮጵያ መንግሥታት ማስተማር የማይፈልጓቸዉን ብሄሮችና ብሄረሰቦች በእግራቸዉ እየኳተኑ ሲያስተምሩ የነበሩ ( ቦጋለ ዋለሉና ዋና ዋገሾን ልብ ይሉል ) ዎላይታዎች መንደር ዩኒቨርስቲ እስካሁን ያልተከፈተዉ በአጋጣሚ አለመሆኑን አታዉቁም ወይ ?
ይህ ከጥጥ ልብስን ቀድሞ የሸመነ መገበያያ ሳንቲም የፈበረከ ስልክ በአፍሪካ ቀድሞ ያስገባ ሕዝብ ወደ ሁዋላ የቀረዉ በብሄር ጭቆና ምክንያት መሆኑ ግልጽ አይደለም ወይ? እናንተ እራሱ በፓርላማ ከፈታዉን ለማጨናገፍ የምት ጠይቁት የአያትና አባቶቻችሁን ተንኮል ለማስቀጠል መሆኑን ሰው ይታዘባል አትሉም ወይ? የሚሉ ብዙ ጥያቄዎችን ያዘለ መልስ ነበር ብዬ አምናለሁ።
የዎላይታ ብቻ ሳይሆን የወለጋንም ጉዳይ ብናነሳ አካባቢው ብዙ ምሁራንን ያፈራና በኢትዮጵያ በትምህርት ፈር ቀዳጅ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲ የተከፈተዉ እጅግ ዘግይቶ ነው የነበረዉ። ስለዚህ እነኝህ ነገሮች ከግምት ዉስጥ መግባት አለባቸዉ። ሆን ተብሎ ወደሁዋላ የቀሩ አካባቢዮችን ሆን ብሎ የማሳደግ እርምጃ መወሰድ አለበት ብዬ አምናለሁ።
የቀድሞ የፖለተካ በደሎች መቀልበስ አለባቸዉ። ለምሳሌ መቐለ ዩኒቨርሲቲ ጥሩ ደረጃ ላይ ነበረ፤ አሁን ግን የጦርነቱ ተጽዕኖ ወደሁዋላ ሊያስቀረዉ ይችላል የትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ በመቀስቀሱ። ተመራጭነቱን ቀንሶ ሊሆን ይችላል፣ ያም የተጠና አይመስለኝም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት በሕጉ (ዉል) ላይ የአካዳሚክ ማህበረሰቡ በቂ ዉይይት አድርጓል? ፖለቲከኞች እና የሚዲያ አካላትስ በቂ ትኩረት ሰጥተዉታል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አይመስለኝም። በቂ ትኩረት ያላገኘ ጉዳይ ነው። የሐገሪቷን እጣፋንታ የሚወስን ጉዳይ እና የሐገረ መንግስት ግምባታ አቅጣጫ ላይ የራሱ ተጽዕኖ የሚያሳድርም ጉዳይ ነው፤ ግን ትኩረት ተነፍጓል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ዩኒቨርሲቲ እንደስሙ universal ወይንም አለም አቀፍነቱ፣ አሁን ከምናነሳዉ አካባቢያዊ ቅሬታ ጋር እንዴት ይጣጣማል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይህ ሰፊ ጉዳይ ነው። በአጭሩ በአንድ አካባቢ ዩኒቨርስቲ መኖሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት፣ በትንሹ የማህበረሰብ አገልግሎትን ብቻ እንኳን ብናይ ነገሩ ግልጽ ነው ጥቅሙ።
🎙💻 ዎላይላታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየሰራሁ ነው ይላሉና፣ የእዉነት ሕጉ (ዉሉ) አላማዉ ይሄ ብቻ ነው ማለት ይቻላል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔ አሁንም የትምህርት ጥራት ደጋፊ ነኝ፤ ግን የኢትዮጵያን ዉስብስነት ከግምት እናስገባ ነው የምለዉ። በቂ ዉይይቶች ይደረጉ ሕግና አሰራሮች ከመዘርጋታቸዉ በፊት። ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ የእዉነት የዴሞክራሲ ሰዉ ከሆኑ በዚህ አዲሱ ዉል ላይ ዴሞክራሲያዊ ዉይይት በመክፈት ማረጋገጥ አለባቸዉ። ይህ ዉል ነባሮቹን ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፣ የተሻለ የተደራጁት፣ በጎበዝ ተማሪዎች ተመራጭ የሚሆኑት ነባሮቹ ናቸዉ፣ በጣም ጠንካራ ሥራ የሠራ ታዳጊ ዩኒቨርሲቲ እንኳን ከነባሮቹ ጋር ተወዳድሮ መዝለቁ ያጠራጥራል። ጉዳዩ በቂ ትኩረት አልተሰጠዉም፣ በቂ ጥናትም የተካሄደበት አይመስለኝም፣ በቂ ዉይይትም የተደረገበት አይመስለኝም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት ሕጎች (ዉሎች) ፍትሐዊና ሐቀኛ እኩልነትን የሚያሰፍኑ መሆናቸዉ የሚኖረዉ ፋይዳ ምንድነው ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ፋይዳዉ ትልቅና ለሐገር አንድነትና ልማት የሚተርፍ ነው። አንድነት (cohesion ) የሚመጣዉ፣ ፍትሐዊ ሕግ ሲወጣና ወጥቶም ለሁሉም በወጥነት ሲተገበር ነው፣ ዳኛዉ ሕግ ነው፣ ሕጉም የቀደሙ ተንኮለኛ የፖለቲካ ዉሳኔዎችን ከግንዛቤ በማስገባት ሲረቀቅ ሕዝብ ሁላችንን የሚዳኘዉ ሕግ ነው ብሎ ሲያምን አንድ ይሆናል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
#Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Tigray #Amhara #Oromo
ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተጠናቀረ ዘገባ ነው
ዩኒቨርስቲዎችን ወደ ማሰልጠኛነት ማውረድ?
“በመለስ