
የዎላይታ ሶዶ ዲስትሪክት በከተማዋ ባሉ አዳዲስ መንደሮች 8 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግንባታ በቅርቡ አጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ማድረጉን የወላይታ ዲስትሪክት የደንበኞች አገልግሎት፣ ሽያጭና ግሪቫንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አንዷለም አብርሀም ገለፁ፡፡
በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከተከናወነባቸው መንደሮች መካከል በአምስቱ ከ400 በላይ ደንበኞች ሀይል ማግኘት የጀመሩ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ከተቋሙ ጋር ውል እየፈፀሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዲስትሪክቱ አልፎ አልፎ የሽቦና የፊውዝ ስርቆት ስለሚፈጸም ህብረተሰቡ መሰረተ ልማቱ የራሱ መሆኑን በመገንዘብ ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የዲስትሪክቱ የስርጭት ፣ ኮንስትራክሽንና ኦፕሬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ገረሱ ቴጋ በበኩላቸው በከተማው ስምንት መንደሮች የተከናወነው የማስፋፊያ ግንባታ ወጪ የተሸፈነው የከተማው አስተዳደር በመደበው 6 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በጀት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም አንድ ባለ 100 ኪሎ ቮልት እና ስምንት ባለ 315 ኪሎ ቮልት ትራንስፎርመሮች፣ ከ420 በላይ የዝቅተኛ እንዲሁም አራት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመካከለኛ ሀይል ማከፋፈያ መስመር ምሰሶዎች መተከላቸውን መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አስተዳደሩ በከፈለው ተጨማሪ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር 26 የዝቅተኛና 43 የመካከለኛ ሀይል ማከፋፈያ መስመር ምሰሶዎች መተከላቸውን የገለፁት ሀላፊው የመስመር ዝርጋታና የትራንስፎርመር ተከላ በአካባቢው ባለው የወሰን ማስከበር ችግር ያልተከናወነ ሲሆን ችግሩ ሲፈታ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል፡፡