1000033034

ተጠያቂነት ወዴት ነው? “ዎላይታ የራሱን ጉዳይ በክልሉ ተወካይ በኩል ሲዳማ ደግሞ ቀጥታ በራሱ ተወካይ የተሳተፈበት የዲላው መድረክ ምን ውጤት ያመጣል ? በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መሐከል የፖለቲካ ነጋዴዎች ጠልቃ እንዳይገቡ መፍትሔው ምንድነው ? ለመሆኑ ህዝቡ የራሱን ጉዳይ በቀጥታ በራሱ ተወካይ መነጋገር የሚጀምረው መቼ ?- የዛሬው የዎላይታ ታይምስ የፖለቲካ ወጌሻ ጥንቅር እንደሚከተለው ምላሽ ይዟል 👇

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በቅርቡ የሲዳማ ክልልንና የዎላይታ ዞንን በሚያዋስን አካባቢ የሲዳማ ክልል የጸጥታ አካላት፣ ባልታጠቁ ወጣቶች ላይ በወሰዱት ሕገወጥ እርምጃ፣ በሰዉ ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል። በቅድሚያ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰማዎትን ነገር ቢገልጹልን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ። በመጀመሪያ ለሟቾች ወዳጅ ዘመድ መጽናናትን፣ ለተጎዱ ደግሞ ፈዉስን እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው እመኛለሁ። በእዉነቱ የሲዳማ የጸጥታ አካላት ድርጊት ሕገወጥና የሁለቱን ሕዝቦች ወንድማማችነት የማይመጥን ተራ ተግባር ነው። ይህንን ጉዳት ያደረሱ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረክ እና ተጎጂዎችን ለመካስ የዎላይታ ዞን፣ የሲዳማ ክልልና የፌደራል መንግስት በጋራ መሥራት አለባቸዉ እላለሁ። በዚህም ረገድ በቅርቡ የሁለቱም ሕዝቦች ወዳጅና ወንድም የሆነዉ የጌዲኦ ሕዝብ መናገሻ በሆነችዉ፣ በዲላ ከተማ፣ የተደረገዉ ዉይይት ጥሩና የሚበረታታ ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በጉዳዩ ዙሪያ በዲላ በተካሄደው ስብሰባ ሲዳማ ቀጥታ በራሱ አመራር ወክለው ተሳትፏል፣ ዎላይታ ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመራር በኩል አንደ ተሳታፊ በመሆን እንጂ በቀጥታ ለመወያየት ዕድል አልነበረውም። ይሄን ሁኔታ እንዴት ተመለከትከው ? ከውይይቱ ለቅሶ መድረስና የህግ ተጠያቂነት ማስፈን አይቀድምም ወይ? ለምን መድረኩ በተጎጂ አከባቢ ልተካሄደም ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ መድረኩ በዲላ መካሄዱ ጥሩ ነው። ጌዴኦ የሁለቱም ወንድም ሕዝብ ነዉና የአስታራቂነት ሚናን ሊወጣ ይችላል። የደቡብ ክልል መሳተፉ ጥሩ ሆኖ፣ ለዎላይታ ዞንና አመራሮች ቦታ መስጠት አለበት፣ የጉዳዩ ባለቤት ናቸዉና። ወንጀል የሰሩ ሰዎች ተጠያቂነት የግድ ነው፣ ያ ካልሆነማ መሰል ወንጀል ባህል ይሆናል፣ ስህተትን በስህተት ለማረም የሚፈልጉ ኃይሎችን ይፈጥራል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ የዎላይታ እና የሲዳማ ፖለቲካ በምን አግባብ መመራት አለበት ? የሕዝቦቹስ ትስስር እንዴት ይገለጻል? በርግጥ በሁለቱ ሕዝቦች መሐከል ወሰን ለግጭት የሚያበቃ ነገር መሆን አለበት?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ምንም ጥያቄ የሌለዉ ነገር የዎላይታና የሲዳማ ሕዝብ ወንድማማችነት ነው። እነኝህ ሁለቱ ሕዝቦች እጅግ በጣም የተጋመደ ጥቅም፣ ተቀራራቢ የፖለቲካ ታሪክ፣ በጋራና በተናጠል እየተደጋገፉ ጭቆናን ለማስወገድ የመታገል ታሪክ፣ በብዛት የተጋባና የተዋለደ ሕዝብ፣ ተቀራራቢ የሕዝብ ብዛት የሚጋሩት ሰፊ ወሰን አላቸዉ። እነዚህ ወንድማማች ሕዝቦች ከዚህ በመነሳት፣ የሚያራምዱት የፖለተካ ሐሳብ የሚደጋገፍና አንዱ ለአንዱ ደጀን የሚሆንበት መሆን አለበት።

ባለፈዉ በሐዋሳ ከተማ እና አካባቢዉ በዎላይታ ተወላጆች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከደረሰ በሁዋላ፣ የዎላይታ ሕዝብ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስበትም፤ ነገሩ በቀላሉ በሐገር ሽማግሌዎች እርቅ መብረድ የቻለዉ ሕዝቦቹ ለዘመናት ባዳበሩት የወንድማማችነት እሴት የተነሳ ነው። በርግጥ ግለሰቦች በወንጀላቸዉ መጠየቃቸዉ ግዴታ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝቦች ወንድማማችነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሠራት አለበት።

ሲዳማ በመላዉ ዎላይታ ይኖራል፣ ዎላይታም እንደዛዉ፣ ይህ የሕዝቦቹ ወንድማማችነት የፈጠረዉ ነው፣ ማንም ሊያለያዬዉ አይችልም፣ የሁለቱም አካባቢ ሊህቃን ደግሞ ይህንን ወንድማማችነት ለማጎልበት መሥራት አለባቸዉ። የሐዋሳ እና ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲዎች በጋራ የሁለቱን ሕዝቦች ወንድማማችነት ለማጠናከር ተቀናጅተዉ ቢሰሩ መልካም ነው።

ለምሳሌ የዎላይታና የሲዳማ ወንድማማችነት መድረክ፣ ሲምፖዚየም፣ ፈስቲባል፣ ንግድና ባዛር ወይንም አንዳች ትርጉም ያለዉ የወንድማማችነት ማጎልመቻ ዝግጅት በየአመቱ ቢካሄድ ጥሩ ነው። ሁለቱ ሕዝቦች መሐል ጸብ የለም፣ እያደገ የሚሄድ ወንድማማችነት እንዲኖር በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። የጊፋታ እና የጫምባላላን በአል የልኡካን ቡድን እየላኩ በጋራ ማክበር ያስፈልጋል፣ በዉጪ የሚኖሩ የየብሄሩ ተወላጆችም በየአዲስ ዓመታቸዉ መገባበዝና በጋራ ማክበር አለባቸዉ።

ይህን ካደረግን ወሰን ዎላይታና ሲዳማን አያጣላም፣ በሌሎችም የፖለቲካ ጉዳዮችም እየተደጋገፉ በጋራ መሥራት ይቻላል። የዎላይታና የሲዳማ ተደጋግፎ መሥራት በኢትዮጵያ ፖለቲካም ላይ ተጨባጭ ለዉጥ ያመጣል። የወሰን ጉዳዮች በዉይይት እና በሰላማዊ መንገድ የሕዝቦቹን ወንድማማችነት በሚመጥን ጨዋነት መፈታት አለበት፣ በሲዳማ የሚኖር ዎላይታም፣ ሆነ በዎላይታ የሚኖር ሲዳማ፣ በወገኖቹ መሐል እንደሚኖር እንዲሰማዉ በሚያደርግ አግባብ እና ለሌሎችም አካባቢዎች ምሳሌ በሚሆን አግባብ መፈታት አለበት። የሲዳማ ክልል አመራሮችም፣ ከዎላይታ ዞን አመራሮች ጋር ሆነዉ፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን ማጽናናትና መደገፍ አለባቸዉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

#Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Sidama

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።

“ዎላይታ የራሱን ጉዳይ በክልሉ ተወካይ በኩል ሲዳ