ለመሆኑ “ጃዋር በትግራይ ሻዕቢያ ያደረሰውን ጥቃት ለማዉገዝ ለምን ተቸገረ”?! “የጃዋር ኢትዮጵያ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ብቻ ናት”?! “በሀገሪቱ ለተከሰተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ናቸው ተጠያቂ” ?- የዛሬው የዎላይታ ታይምስ የፖለቲካ ወጌሻ ጥንቅር እንደሚከተለው ምላሽ ይዟል 👇 ቃለመጠይቁ በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ነው

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ፖለቲከኛ #ጃዋር #መሐመድ እና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ሰሞኑን በርዕዮት ሚዲያ ቃለምልልስ ማድረጋቸዉ ይታወሳል። አንዳንድ ነጥቦችን ከማንሳታችን በፊት አጠቃላይ ቃለምልልሱን እንዴት አገኙት?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ያዉ በሩቅ ሆኖ ከመታኮስ ተቀራርቦ መነጋገር የሚበረታታ ነው። ቃለምልልሱ ከመስመር የወጡ እንካ ሰላሚትያዎች ሊያስተናግድ ይችላል ብዬ ፈርቼ የነበረ ቢሆንም፤ ከሞላ ጎደል ጥሩ በሚባል አኳሐን ተደርጓል። ለዚህ ሁለቱም መመስገን ያለባቸዉ ይመስለኛል። ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ጥሩ ዝግጅት አድርጎ ነው የመጣዉ፣ ጃዋር መሐመድም ያመነባቸዉን ምላሾች ሰጥቷ ከሞላ ጎደል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በቃለ ምልልሱ አንዱ የተነታረኩበት ነጥብ የ state resiliance (የኢትዮጵያ ሐገረ መንግስት ፈረሳን የመቋቋም አቅም) ነው። በዚህ አርዕስት ያደረጉትን ምልልስ እንዴት ታዘቡት?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ቴዲ ጃዋርን ከአመት በፊት ጥንታዊ ስለሆነ በቀላሉ አይፈርስም ያልከዉ ሐገረ መንግስት ምንም የተለዬ ነገር ባልተፈጠረበት የመፍረስ ስጋት ዉስጥ ገባ ያልከዉ እንዴት ነው ላለዉ ጃዋር የሰጠዉ መልስ አጥጋቢ አልነበረም። በተለይ ከ IMF ስምምነት በሁዋላ መንግስት አቋም ቀይሯል የሚለዉን በበኩሌ አጥጋቢ ምክንያት ሆኖ አላገኘሁትም።
በነገራችን ላይ ቴዲ አላነሳዉም እንጂ ጃዋር፣ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ማፍረስ እንችል ነበረ ስላልፈለግን ነው የተዉነዉ ያለበትንም ቢያነሳበት ጥሩ ነበረ። በዚህ ጉዳይ ላይ የጃዋር የ consistency ችግር ግልጽ ነው። በርግጥ ፈጽሞ የማይታረቁና የተራራቁ ነገሮችን በሐገረመንግስቱ ዘላቂነት ናፈረሳን የመቋቋም አቅም ላይ ተናግሯል በተለያዬ ጊዜ።
ከጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ ጋር ባደረገዉ ቃለምልልስ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሐገረመንግስት ነች ብሏል። በርግጥ በአብዛኛው የብሔር ትግል ዘመናዊት ኢትዮጵያ ከሚኒሊክ ወዲህ የተፈጠረች ተደርጎ ይገለጻል፣ ነገሩ የጠራ አይደለም። በእዉነቱ የኢትዮጵያ ሐገረመንግስት ጥንካሬ ከሚመነጭባቸዉ ምክንያቶች አንዱ ጥንታዊነቱ ቢሆንም፤ የታሪክ ስርቆትና ድበቃ ያንን እዉነታ የደበቀብን ይመስለኛል።
በነገራችን ላይ OLA ከብልጽግና ጋር በታንዛንያ ሲደራደር referendum በኦሮሚያ ይደረግ የሚል ጥያቄ አንስቷል ተብሎ ነበር፣ ስለዚህ ጃዋር ኦሮሚያ ሐገር የምትሆንበት እድል አሁን የለም ብሎ ካመነ ስልጣን በእጁ ቢሆን ምን አድርጎ ግጭቱን እንደሚያስቆም ቴዲ ቢጠይቀዉ ጥሩ ነበረ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መንግስታትን ከዚህ በቀደም የአማራ እና የትግሬ እያልክ ፈርጀሐል፣ የአሁኑን የኦሮሞ ብላቹ አትፈርጁ ብለህ ምክንያት ደርድረሐል የሚል አንድምታ ያለዉ ጥያቄም ተነስቶ ነበር፣ ለዚህ ጃዋር የሰጠዉ መልስ አጥጋቢ ነው ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አይመስለኝም። በተለይ ከ1987 ሕገመንግሥት በሁዋላ ኢትዮጵያ የፈደራል ሥርዓት ስለምትከተል መንግሥት የአንድ ብሔር የተለጠጠ ዉግንና እንዳይኖረዉ አድርጓል ሥርአቱ። ስለዚህ ከዛ በሁዋላ መንግስትን ጠቅልሎ ወያኔ እያሉ መፈረጅ ስህተት ነው። ኢህአዴግ ህወሃት መራሽ ቢሆንም ለብአዴን ከመጀመሪያዉም የጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ የአማራ ተወላጅ ጀነራሎችን በመከላከያ አመራርነት፣ አየር ኃይል አዛዥ እስከማድረግ አሳትፏል።
#ከዎላይታዉ #ዎጋጎዳ #ትግል በሁዋላ በዎላይታ አንስቶ ሌሎችንም የደቡብ ብሔሮች በከፍተኛ ስልጣን አሳትፏል። እዉነት ለመናገር ኦሮሞ በሚገባዉ ልክ ተገቢ ቦታ አልተሰጠዉም፤ ቢሆንም ጠቅልሎ መንግስትን ወያኔ ብሎ መፈረጅ ልክ አይደለም። ሌላዉ ወያኔ ማለት በትግራይ አልምበረከክም ባይነት እኩል ነኝ።
በሐገሬ ጉዳይ ባይተዋር ልታደርጉኝ አትችሉም ባይነትን የሚገልጽ ሕዝባዊ የትግልና የጀግንነት ስያሜ እንጂ የፓርቲ ስም አይደለም። ስለዚህ ወያኔ ይዉረድ ማለት የትግራይ ሕዝብ ታግሎ የተጎናጸፈው ራስን በራስ የማስተዳደርና በፈደራል ደረጃም ሚዛናዊ ዉክልናዉን አስጠብቆ የመዝለቅ ሕገመንግሥታዊ መብቱን የሚጋፋ ነው።
ትክክለኛዉ መንገድ ሕገመንግሥታዊዉ የኦሮሞ ሕዝብ ሚዛናዊ ዉክልና የማግኘት መብቱ ይከበር ማለት ነው የነበረዉ። አዉርዶ የመዉጣት ነባሩ የኢትዮጵያ የተቃዉሞ ፖለቲካ ቅኝት፣ ከፈደራል ሥርዓቱ እሴቶች ጋር የሚጣረስ ነው። ዛሬ ሐገሪቷን ወደዚህ ዉጥንቅጥ የከተታት በተለይ ኦሮ_ማራ የሚል የሌሎችን ሕዝቦች causes ችላ ያለ አካሄድ ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በአቶ ኃይለማርያም ጊዜ ስልጣን ለመቀማት ጃዋር ባደረገው ቅስቀሳ አብዛኛው ቦታ በህወሓት ላይ ቢሆንም እነሱን ለመቃወም በተደረገው አንድም የትግራይ ተወላጅ በኦሮሚያ ክልል አልተገደለም አለ። ጋዜጠኛውም ያልተገደሉት በእናንተ ሳይሆን በኦሮሞ ህዝብ ቸርነት ነው በሚል ዘጋ። ነገር ግን በእሱ ምክንያት በመቂ፣ ዝዋይና መሠል በእዛ አከባቢ ምንም ፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ንፁሃን ዎላይታዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደል ያደረገው ማነው ? ቃለመጠይቁ ላይ ይሄንን ጉዳይ ጠያቂውም መላሹም አላነሳምና ምን ምላሽ አሎት ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ያዉ የዎላይታ ሕዝብ ላይ የደረሰዉ ጠቃት በቂ ትኩረት አላገኘም። ከለዉጡ በፊትም ሆነ ከለዉጡ በሁዋላ ሐገሪቷ የእልቂት ሜዳ እንድትሆን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ይህ የዎላይታ ሕዝብ ላይ የደረሰዉ ጥቃት በቸልታ መታለፉ ነው። ያኔ ሁሉም ለምን ቢል ኖሮ ሐገሪቷ ለዚህ ሁሉ ፍጅት አትዳረግም ነበር። ግልጹም ነገር ቴዲ እንዳለዉ ጃዋር በዚህ ፍረጃ ላይ ከሚጠቀሱ ሰዎች ግምባር ቀደሙ ነው።
በአዋሳም የምታስታዉስ ከሆነ ከዎላይታዎች መጠቃት ቀናትን ቀድሞ ሲዳማን በጉልበትም ቢሆን ክልል እናደርጋለን ያለበት ይታወሳል። ጃዋር እንደሚለዉ በሁሉም መሥመር በጥላቻ ቅስቀሳዎች አልተሳተፈም ማለት ይከብዳል። ቴዲ የኦሮሞ ሕዝብ ቸርነት ያለዉ ባይሆን የወደድኩለት አገላለጽ ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሌላዉ ነጥብ ጃዋር በትግራይ ጦርነት ሻዕቢያ መግባቱን ማዉገዝ ሲተናነቀዉ ተስተዉሏል። ይህንንስ እንዴት አዩት? የአማራ ክልልንም መግባት አድበስብሶ አልፏል? ይሄስ ከመርህና ከሕገመንግስት አንጻር እንዴት ይታያል? በርግጥ ጃዋር ለሕገመንግስቱ ታማኝ ከልሆነ እንዴት ሊታመን ይችላል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይህ እንግዲህ መርህ አልባነት ነው። ጃዋር ታዲያ በጦርነቱ ጉዳይ ከብልጽግና አቋሙ በምን ይለያል የሚል ጥያቄም እንድናነሳ የሚያስገድድ ነው። የሻዕቢያም ሆነ፣ የአማራ ክልል ወደ ትግራይ ዘልቀዉ ገብተዉ መዉጋትና መሬት መቆጣጠራቸዉ፣ መንግስት “ሕግ ማስከበር “ያለዉን፣ ያከሸፈና ለጦርነቱ escalation (ወደ ሕዝባዊ የእርስበርስ ጦርነትነት) ደረጃ እንዲያድ ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኞቹ እንደሆኑ ግልጽ ነው።
በእዉነቱ ይህ ጃዋር በምን ይገዛል፣ ሕገመንግሥት ካልገዛዉ የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው። ኢትዮጵያ አትፍረስ የሚል፣ ሰው ኢትዮጵያዉያን በባዕድ እና ሕገወጥ ሐገር በቀል ኃይሎች ሲበደሉ ካላወገዘ አስቸጋሪ ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሌላዉ ነጥብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ የተለያዩ ሕገመንግሥታዊ መብቶቹ በተሻለ ሁኔታ እንዲከበሩ ከሚጠይቅበት ደረጃ ወደ ሕልዉና ጥያቄ በመዉረዱ ለምን አትጸጸትም ተብሎ ለተጠየቀዉ የሰጠዉስ መልስ ሚዛናዊ ነው ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አይመስለኝም። እኔ ወደዚህ ዉድቀት ያመራዉ መጀመሪያ ትግሉ የተመራበት ጃዋርም የተሳተፈበት ሥርዓት አፍራሽና የሌሎችን ሕዝቦች መብት የገፋ አካሄድ ይመስለኛል። ጃዋር አልጸጸትም ብሎ በቁጣ ወያኔ ምናምን ወደማለት ሄዶ በfalse equivalence እነ ሐየሎም ደርግን በመጣላቸዉና እነ ጌታቸዉ አሰፋ በሰሩት ወንጀል ምክንያት መጸጸት የለባቸዉም ብሏል፤ ብዙ ዉሃ የሚቋጥር ምክንያት አይመስለኝም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሌላዉ ሁለቱም የተስማሙበት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምንም ተስፋ ባለማድረግ ነው፤ ይህንንስ እንዴት ያዩታል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔ እዛ ላይ ሁለቱም የተሳሳተ አቋም የያዙ ይመስለኛል። ጃዋር ግን አደገኛ ሐረግም አምልጦታል። በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጋር ያሉ ሰዎች አዉቃቿለዉ፣ እርምጃ መዉሰዳቸዉ አይቀርም ያለዉ በጣም አደገኛ አባባል ይመስለኛል።
ሁለቱም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የፈረመዉን የፕሪቶሪያ ስምምነት ይተግብር፣ ከአማራና ኦሮም አማጽያን ጋር ሕገመንግሥቱን ያከበረ የሰላም ስምምነት ይፈራረም ቢሉ የተሻለ ነበረ። አጠቃላይ ተስፋ የሚያስቆርጥ መልዕክት ማስተላለፋቸዉ ጥሩ አልመሰለኝም። እኔ ሲጀመርም ችግሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ነው በሚለዉ የጃዋር ሐሳብም ሆነ በቴዲ የኦሮሞ መንግስት ነው ዳርዳርታ አልስማማም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
#Ethiopia #southethiopia #JawarMohammed #oromo #Tigray
ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።
ቃለመጠይቁ በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ነው