1000034492

በተለይም በዞኑ ሶስቱ ፓርቲዎች በብልፅግና ጨው ሳይታለሉ ለህዝብ ጥቅምና መብት እንዲቆሙ ማድረግ ይቻላል !? ለመሆኑ ፓርቲዎቹ በህዝብ ቁስል የሚነግዱ ሳይሆን የሚያክሙ መሆን የለባቸውም ወይ ?- የዛሬው የዎላይታ ታይምስ የፖለቲካ ወጌሻ ጥንቅር እንደሚከተለው ምላሽ ይዟል 👇

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ዛሬ የዎላይታ ፓርቲዎችን ወቅታዊ ቁመና ከሐሳብ ጥራት፣ ከአመራር ብቃት፣ ከአደረጃጀት ጥንካሬ እና ከሕዝብ ተቀባይነት እንዲሁም በሐገር ደረጃ ከተጽዕኖ አሳዳሪነታቸዉ አንጻር ግምገማ እናደርጋለን።

በዚህም አንጻር ቅርጫፍ ብቻ ቢሆንም የዎላይታ ብልጽግና፣ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግምባር፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ እንዲሁም የዎላይታ ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄን እንዳስሳለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ሐገራዊ ምርጫዉም አንድ አመት ብቻ ስለቀረዉ፣ ትክክለኛ ርዕስ በትክክለኛ ሰአት ብያለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እሺ እናመሰግናለን። በቅድሚያ ከዎላይታዉ የብልጽግና ቅርንጫፍ ቢጀምሩልን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ እኔም አመሰግናለሁ። ያዉ ብልጽግና ወጥ ፓርቲ ስለሆነና በክልልም በዞንም ደረጃ መሰብሰብ የማይፈቀድለት ቅርንጫፍ ብቻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ከትግራይ ክልል ዉጪ ገዥዉ ፓርቲ ብልጽግና ስለሆነ፣ በፓርቲው ዉስጥ ዎላይታ ምን ድርሻ አለዉ የሚለዉን መገምገም ይቻላል።

ብልጽግና ከጥንስሱም ለዎላይታ ሕዝብ ጥሩ አመለካከት አለዉ ማለት አልችልም፣ ፓርቲው በሐገር አቀፍ ደረጃም የሐሳብ ጥራት ብቻ ሳይሆን የወጥነትም ችግር ያለበት ነው። በተለይ ፓርቲውን በሐገር ደረጃ ከሚዘዉሩ ሰዎች ዉስጥ የዎላይታ ተወላጅ የለም።

ፓርቲዉ የሚሰጠዉ የመንግስት የስልጣን ሹመት ብሔሩን ወሳኝ ከሚባሉ ቦታዎች ማግለልን መሠረት ያደረገ ነው። በአቅም ደረጃ በብልጽግና ዉስጥ ብዙ የተሻለ አቅም ያላቸዉ ዎላይታዎች መኖራቸዉን መካድ እንደማይቻለዉ ሁሉ ፓርቲ ብለዉ ያሉበት ብልጽግና በብሄራቸዉ ምክንያት ቦታ እንደማይሰጣቸዉ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

አደረጃጀቱ የመንግስትን መዋቅር ተከትሎ ብዙ ሰዎችን ቢያቅፍም፤ ፓርቲው ከልባቸዉ አምነዉ አባል የሆኑበት ነው ማለት አይቻልም። በተለይ ደኢህዴን የዎላይታን ሕዝብ በማስጠቃቱ ፊርማ አሰባስቦ ከድርጅቱ የወጣዉ ሕዝብ ልብ ዉስጥ ብልጽግና መልሶ ገብቷል ማለት ቀልድ ነው። በሐገር ደረጃም የዎላይታ ብልጽግናዎች ተጽዕኖ እምብዛም ነው።

ብሔሩ በክልልም በፈደራልም ሚዛናዊ የስልጣን ዉክልና መነፈጉም የችግሩ የአንዱ ሳንቲም ሁለተኛዉ ገጽታ ነው። ስለዚህ የዎላይታ ብልጽግናዎች፣ ፓርቲያቸዉ ስለሕዝባቸዉ ያለዉን የተዛባ እይታ መቀየር የቻሉበት አግባብ የለም፣ ስለዚህ በአፈናና በጉልበት ካልሆነ ብልጽግና በአካባቢው ብዙ ተቀባይነት አለዉ ማለት አይቻልም። ይሄንን ሁኔታ በማጤን ማስተካከል ከተቻለ መፍትሔ ሊኖር ይችላል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እሺ በመቀጠል ስለ ዎሕዴግ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ዎሕዴግ አንጋፋ ድርጅት ነው። ለዘመናት ለሕዝቡ ድምጽ በመሆን ያደረጋቸዉን ተጋድሎዎች አደንቃለሁ፣ በፓርቲው መስመር ለዎላይታ ለታገሉ ሁሉ ክብር አለኝ። ነገር ግን በዚህ ሁሉ አመታት ፓርቲው በዞኑ ምርጫ ለምን አላሸነፈም? የክልል ምክር ቤትም ሆነ የፌደራል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ አባሎቹን ለምን ማስመረጥ አልቻለም የሚለዉ በራሳቸዉ መገምገም ና የመፍትሔ አቅጣጫም ሊያስቀምጡለት ይገባል።

በአመራር ደረጃ ጎልቶ የወጣ ነገር ባይስተዋልም፣ በፓርቲው ዉስጥ የተወሰኑ አቅም ያላቸዉ ግለሰቦች እንዳሉ ይስተዋላል ወደ ፊት አመራርነት መምጣት ያለባቸዉ ይመስለኛል። ፓርቲው በተለያዩ ሕዝቡን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በየጊዜዉ መግለጫ ማዉጣቱ የሚደነቅ ነው። ይሁን እንጂ ሐሳቡን በቋዋሚነት ለሕዝቡ በማህበራዊም ሆነ በmainstream ሚዲያ ለመሸጥ የሚያደርገዉ ጥረት ብዙ አይደለም።

ሕዝባዊ ስብሰባዎችን የምሁራን መድረኮችንም ሲያዘጋጅ አይስተዋልም። በሐገር አቀፍ ደረጃም ያለዉ ተጽዕኖ ከሚጠበቅበት በታች ነው ባይ ነኝ።

ዎሕዴግ በሐገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ይዞ የሚቀርባቸዉን አጀንዳዎች ለሕዝብ ይፋ ካለማድረጉም በተጨማሪ መጀመርያ አልሳተፍም ካለበት ምን ስለተቀየረ ለመሳተፍ እንደወሰነም ግልጽ አላደረገም። ፓርቲው አንጋፋ በመሆኑ በዎላይታም ሆነ በኢትዮጵያ ቢታወቅም ተጽዕኖዉን ለመጨመር ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ስለ ዎብን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ዎብን ከለዉጡ በሁዋላ የተፈጠረ በወቅቱም ብዙ አቅም ያላቸዉ ወጣቶች የነበሩበት እና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ ቆይቶ የተቀዛቀዘ ፓርቲ ነው። በአመራር ደረጃ አሁን ከፊት ያለዉ አማኑኤል ሞጊሶ አቅም ያለዉና በተለያዩ ሚዲያዎችም ሐሳቦቹን በጥሩ ምሁራዊ አቅም ሲያስተዋዉቅ ታዝቢያለሁ። መሰል አቅም ያላቸዉ ምን ያህል ሰዎች ፓርቲዉ ዉስጥ አሉ የሚለዉን ለማየት አልቻልኩም።

ዎብን ከነኦፈኮ፣ ኦነግ እና ኦብነግ ጋር በጋራ ምክንያቱን ገልጾ ከሐገራዊ ምክክሩ እራሱን ማግለሉን አከብርለታለሁ፣ በዚህ ረገድ በሐገር አቀፍ ደረጃም ተጽዕኖዉ የሚናቅ አይደለም። ፓርቲዉ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ና የምሁራንን መድረኮች የማዘጋጀት ድክመት አለበት። ሐሳቡንም ለሕብረተሰቡ ለመሸጥ የበለጠ መትጋት ይጠበቅበታል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ስለ ዎሕነን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ምናልባት ከዛ በፊት ስለ ዎሕዴግና ዎብን አንድ ነጥብ መጨመር እፈልጋለሁ። ከፈቀዳችሁልኝ?

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እሺ ይቀጥሉ።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ምናልባት ባለፈዉ ምርጫ ላይ የቱሳ ጥምረት በሚል ፓርቲዎቹ በጋራ እጩዎችን ለማቅረብም የተወሰነ ጥረት ማድረጋቸዉ ይታወሳል፣ ተግባራዊነቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነዉ። በፓርቲዎቹ መሐል በጋራ የቱሳ ጥምረትን ፈጥረዉ እንዳይሰሩ የሚከለክላቸዉ ልዩነት በግሌ ለእኔ ግልጽ አይደለም።

የሐሳብ ልዩነቶቻቸዉ አብሮ መታገልን የሚከለክሏቸዉ እስካልሆኑ ድረስ በጋራ ቢቀጥሉ የተሻለ ይመስለኛል። የደጋፊ ኃይል እንዳይበታተን በአመራር አቅምም በጋራ ቢሰባሰቡ በጣም የተሻለ ነገር የሚፈጠር ይመስለኛል። ድርጅታዊ አቅማቸዉም በጋራ ሲመጣ ትልቅ ነው። ተጽዕኖ አሳዳሪነታቸዉም ይጨምራል። ለሕዝብ ቸወካዮች ምክርቤትም ሆነ ለክልል ምክር ቤት የተሻሉ እጩዎችን ለመመልመልም ያግዛቿልና የተናጠል ጉዟቸዉ አያስደስተኝም።

በትንሹ ወንበሮችን በሁለቱም ምክር ቤቶች ለማሸነፍ ከፈለጉ ከወዲሁ ተጣምረዉ፣ ለምርጫዉ ይዘጋጁ እላለሁ፣ ምርጫዉ ሲደርስ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ እንዳይሆን። ሁለቱም አቅማቸዉን ለማጎልበት ብዙ ምሁራንን አባል ለማድረግ መጣር አለባቸዉ።

ገዥዉ ፓርቲ በግልጽ የዎላይታን ሕዝብ የሚገፋ በመሆኑ ብዙ ነጥብ ሊያስቆጥሩበትና የሕዝቡን ድምጽ ሊያገኙ ይችላሉ። ለምሳሌ የዎላይታ ዞን የሚያገኘዉ በጀት ከተገቢዉ በታች ነው። ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሕዝቡ ጠይቆት የኢንዱስትሪ ዞን አንገነባም ብሏል መሰል ነጥቦችን መጠቀም ይችላሉ። ስለዚህ ጠንክረዉ ከሰሩ ዉጤት የማያመጡበት ምክንያት የለም።

በዚሁ ስለ ሐገር አቀፉ ዎሕነን ስሔድ ፓርቲዉ አዲስ ከመሆኑ በተጨማሪም ሐሳቡም አዲስ ሆኖ አግንቼዋለሁ። ፓርቲዉ ዎላይታ ድንበሯ ና ሕዝቧ አሁን በዞን ደረጃ ያለዉ ብቻ አይደለም በድርድር ሰፊ አንድነት መፈጠር አለበት የሚል አቋም ያለዉ ነው። የፓርቲው አዲስነት እንዳለ ሆኖ ፓርቲው ከሌሎች የዎላይታ ፓርቲዎች ጋር መሥራት የሚችልበት አግባብ ካለም ከወዲሁ ቢጀምር ከዞኑ ዉጪም እንደቃሉ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግ ባይ ነኝ።

ምናልባት መሪዉ ወልደማርያም ልሳኑ አቅም ያለዉ ሰዉ ይመስላል፤ ግን ለዎላይታ ክልል በመታገሉ እና ፈደራል ሰርዓቱን በመከላከሉ አድንቀን ሳንጨርስ፣ በምርጫዉ እናት ፓርቲን ወክሎ የፈደራል ስርአቱ ከፋፍሎ ለመግዛት የተፈጠረ ነው ብሎ አስደንግጦኝ ነበረ። አቋም በዚህ ደረጃ መዋዥቅ ያለበት አይመስለኝም።

ሳጠቃልለዉ በሁሉም ፓርቲና ግለሰቦች ላይ የምናደርገዉ አስተያዬትና ትችት ከጥላቻ ሳይሆን የተሻሉ እንዲሆኑና ለሕዝባችንም ጥቅም በማለት ነው። በተረፈ በገዥዉም ሆነ በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፎ ፖለቲካ መሥራት ቀላል እንዳልሆነና ብዙ ዋጋ እንደሚያስፈልግ ስለምንገነዘብ ለእነሱ ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ አጠቃላይ በዎላይታም ሆነ በሐገር ደረጃ በፓርቲዎች አደረጃጀት ላይ ክፍተት የሚሉትን ነገር ቢጠቁሙንና ብንዘጋ?ማየት የሚፈልጉት ጥምረት ወይንም ፓርቲ ካለም ቢጠቁሙን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ በጋራ ያለመሥራት ችግር አንዱ ነው ። እነ ዎብንና ኦፈኮ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ ለምሳሌ ግምባር ቢፈጥሩ፣ አሁንም ያላቸዉን ኮከስ እንደቀላል ባይወስዱት እላለሁ። ሌላዉ በአደረጃጀት ደረጃ ኢፈፓ (የኢትዮጵያ ፈደራሊስት ፓርቲ) ቢደራጅ ትልቅ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል ብዬ እገምታለሁ።

የፌደራል ሥርዓቱን የሚቀበል የትግራይን ግዛታዊ አንድነት ማስመለስ፣ በአዲስ አበባ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ማስከበር፣ የዎላይታን የክልል ጥያቄ መመለስ፣በአማራና ኦሮሚያ የሚደረጉ ጦርነቶችን የሚያስቆም ሐሳብ ማቅረብ፣ የመሰሉ አጀንዳዎችን ይዞ ቢወዳደር ቀላል ተቀባይነት የሚኖረዉ አይመስለኝም በመላዉ ኢትዮጵያ።

ሌላዉ ጥቆማዬ የቀድሞ የደቡብ ሕብረት አይነት ፓርቲም ተቋቁሞ ብናይ ባይ ነኝ። ሕገመንግሥታዊ ሥርአቱ ይቀጥል ሕገመንግሥት ይከበር የሚል ሁሉ ስለ ምርጫዉ ከወዲሁ ቢያስብበት መልካም ነው እላለሁ። ምርጫ ማሸነፍ ቢከብድም በምክር ቤቶች መቀመጫ ማግኘት በቀላሉ ሊታይ አይገባም።

ከተሞችን፣ ዞንና ክልሎችንም ማሸነፍ ከተቻለ ቀላል ነገር አይደለምና ቢታሰብበት እላለዉ። ሁለተኛው ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነዉና ሁሉም ተቃዋሚዎች ትኩረት ቢሰጡበት እላለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Politicalparty

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠይቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥንቅር ነው