ሰበር ዜና
“ዎላይታ ሶዶን ከታሪካዊና ህጋዊ ባለቤቱ ነጥሎ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ተጠሪነቱ በብዙህ-ብዝሃነቶች ለተገነባዉ ክልል ይሁን ማለት ከሕገመንግሥት ጋር የሚጣረስና የዎላይታን የሀገር ባለቤትነት መብት የሚገፍ አደገኛ የፖለቲካ ሴራ ነዉ”- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መግለጫ
“መንገዱ አጭር መዳረሻው ገደል” በሚል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የሪጅዮፖሊስ ከተሞች ለማደራጀት ያወጣውን አዋጅ በመቃወም የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ/ዎብን፣ የዎላይታ ሕዝብ ደሞክራሲዊ ግንባር/ዎህዴግ/ እና የዎላይታ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ዎሕነን/ የጋራ የአቋም መግለጫ አወጣ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ካቢኔ ጥር 16/2017 ዓ.ም የከተሞችን ፈርጅ ለውጥ ለማድረግ በተቀመጠበት የክልሉን የ54 ከተሞች ደረጃ ለውጥ እንዲደረግ የወሰነ ሲሆን ከነዚህ 54 ከተሞች መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት በቀድሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት በከተሞች የደረጃ ፍረጃ በፈርጅ አንድ ደረጃ ተመድበው የነበሩ ሶስት ከተሞችን ማለትም የዎላይታ ሶዶ፣ አርባምንጭ እና የዲላ ከተሞችን ወደ ሪጂዮፖሊስ ከተማ አስተዳደርነት የከተማነት የፈርጅ ለውጥ አድረጓል፡፡
አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተዋቀረ ከአንድ ዓመት በኋላ በከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የከተሞችን ፈርጅ ለመወሰን የወጣውን አዋጅ መነሻ በማድረግ አስጠንችያለሁ ባለው ምንም ሳይንሳዊ መስፈርት ያለሟላ ጥናት መሠረት በማድረግ እነዚህን ሶስት ከተሞች (ዎላይታ ሶዶ፣አርባምንጭ እና ዲላ) በሪጂዮፖሊስ ደረጃ እንዲፈረጁ እና በልዩ ሁኔታ እንዲያድጉ ለማድረግ ታስቦ የወጣ በተባለው “የደቡብ ኢትዮጵያ ክሌላዊ መንግሥት የሪጅዮፖሊስ ከተሞች ለማደራጀት የወጣ አዋጅ” በክልሉ መስተዳድር ም/ቤት ለመስወሰንና ውጤቱ አስቀድሞ የታወቀ የፖለቲካ ውሳኔ ቢያንስ በከተሜነት፣ በከተማ ልማት ፖሊሲ እና ህጋዊ ማዕቀፍ/urbanization, urban development policy and legal framework/ በዘርፉ ዕውቀትና ልምድ ያለቸውን ምሁራንን ያገለለ የይስሙላ ውይይት ህዝቡን በማደናገር ላይ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ/ዎብን፣ የዎላይታ ሕዝብ ደሞክራሲዊ ግንባር/ዎህዴግ/ እና የዎላይታ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ዎሕነን/ ፓርቲዎች ከሚመለከታቸው በዘርፉ ሰፊ ዕውቀትና የአለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ምሁራን ጋር ሰፊ ምክክር እና ውይይት ግብዓት መሰረት በማድረግ ፓርቲዎች በጋራ በቀን 29/05/2017 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫ ያወጣውን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አድርሷል፡፡
- ዎላይታ ሶዶ የዎላይታ ብሄር፤ ታሪክ፤ ባሕል፤ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ማዕከል/እምበርት ናት፡፡ የብሄሩ ማንነት መገለጫ ብሄራዊ ቅርሱና ርስቱ ናት። የዎላይታን ሕዝብ ከዎላይታ ሶዶ እና ዎላይታ ሶዶን ከዎላይታ ሕዝብ ነጥሎ ለመግለጽ-ማሰብ ዘሬም ነገም አይቻልም፡፡ በርካታ የተለያዩ ማንነቶች፤አይዲጆሎጂዎች እና የተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች አካቶ የያዘ የክልሉ መንግስት እና መስተዳድር ምክር ቤት ስለ ዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ይዞታ የመወሰን ስልጣንና ሞራላዊ ብቃት የለዉም፡፡ ዎላይታ ሶዶን ከታሪካዊና ህጋዊ ባለቤቱ ነጥሎ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ተጠሪነቱ በብዙህ-ብዝሃነቶች ለተገነባዉ ክልል ይሁን ማለት ከኢፌዲሪ ሕገመንግሥት ጋር የሚጣረስና የዎላይታን የአገር ባለቤትነት መብት የሚገፍ አደገኛ የፖለቲካ ሴራ ነዉ።
አካሄዱ የአዳማን ከተማ ተጠሪነት ለኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፤ የጎንደር ከተማ ተጠሪነት ለአማራ ብ/ክ/መ፤ የሃዋሳ ከተማ ተጠሪነት ለሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንደማድረግ አለመሆኑ ሊሰመር ይገባል፡፡
- በረቂቂ አዋጁ የዎላይታ ሶዶ ከተማ ም/ቤት እና ከተማዉን ወክለዉ የህዝብ ተወካዮች እና የክልል ም/ቤት አባላት ከከተማዉ ነዋሪዎች መካከል የሚመረጡ ይሆናል የሚባለዉ /ዎላይታን እና ዎላይታ ሶዶን የዎላይታን ሕዝብ እና የዎላይታ ሶዶ ከተማን ህዝብ የመለያየት ብሎም የዎላይታን ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን /self-rule/ መብት የሚገፍ አደገኛ የፖለቲካ ጠቅላይ እና አግላይ የኢምፔሪያል ፕሮጄክት ነዉ፡፡
በጣም አብዛኛዉ የብሄሩ ልህቃን (የፖለቲካ፤ የባህል፤ የኢኮኖሚ፤ የአካዳሚ፤ የሃይማኖት) እና ፐብሊክ ምሁራን መኖሪያቸዉ ዎላይታ ሶዶ ከተማ እንደመሆኑ እነኚህ ልህቃን እንደወትሮአቸዉ ሁሉ ህዝባቸዉን እንዳያገለግሉና እንዳይወክሉ እንደዚሁም ከከተማዉ ዉጭ ያለዉ የብሄሩ ልህቅ የአያቶቹን አጽመ ርስት (ቅርስ) የሆነችዉን ዎላይታ ሶዶ የማገልገልና የማልማት ታሪካዊ፤ ሰብአዊና ህገመንግስታዊ መብትና ነጻነቱን የሚገፍና የልዩነት ግድግዳ የሚፈጥር በጣም አደገኛ የፖለቲካ ፕሮጄክት መሆኑን በመገንዘብ የክልሉ መንግስት አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡
- እነዚህ ሶስቱም ከተሞች በጋራ ዕኩል ደረጃ (ፈርጅ አንድ) ደረጃ የሚገኙ የነበሩትን ብቻ አንድ ደረጃ በማሳደግ ሁሉንም ወደ ሪጂዮፖሊ የከተማ አስተዳደርነት ማሳደግ በከተሞቹ መካከል ለፈርጅ ለውጥ የተደረገውን ውድድር የይስሙላ መሆኑን እንረዳለን፣
- ከዚህም በተጨማሪ የሪጂዮፖሊ ከተማ ላለበት አከባቢ ማዕከል ሆኖ በዙሪያው ያሉ ከተሞችን አስተሳስሮ የሚያሳድግ ከተማ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ መስፈርት ስናይ ከዎላይታ ሶዶ ከተማ ውጪ ሌሎች ከተሞች በ20 ኪሎሜትር ራዲየስ እንኳ ሌላ የከተማ አስተዳደርም ሆነ የወረዳ ማዕከል እንደሌላቸው ይታወቃል፡፡
የዎላይታ ሶዶ ከተማ ግን በ20 ኪሎሜትር ራዲየስ ብቻ እንኳን 3 የከተማ አስተዳደርና 7 የማዘጋጃ ቤት ከተሞችን አቅፋለች፡፡ ይህ እውነታ በከተማ ገቢ፣ በህዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋት፣ በዕድገት ፍጥነት፣ በንግድና አገልግሎት ማዕከልነት፣ በቀጣይ የማደግ ዕድል ወዘተ ጉዳዮችም ጭምር በልዩነት የሚታይ ሆኖ ሳለ የዎላይታ ሶዶ ከተማን በዚህ ማዕቀፍ በልዩነት አለማየት እና ከላይ በተጠቀሱ መስፈርቶች በተመሳሳይ መዳኘት የፈርጅ አወጣጥ ስርዓቱን ወደ ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመውሰድ የታለመ በመሆኑ አጥምቀን እንቃዎማለን።
- በክልሉ በኩል ከዚህ ቀደም ለዎላይታ ሶዶ ከተማ የተሰጠው የከተማ ደረጃ ፍረጃ ምንም ያስገኘው ውጤት አልነበረውም፡፡ ክልሉም የፈርጅ አንድ ከተሞችን በልዩነት ለመደገፍና በሚያስመዘግቡት ውጤት ላይ ተንተርሶ የደረጃ ፍረጃ ለማከናወን የተጓዘበት ርቀት ባለመኖሩ ከተሞቹ ባሉበት ያለምንም ልዩነት የፈርጅ ለውጥ እንዲያደርጉ መደረጉ ከስድስቱ የክልሉ ማእከላት ከተሞች የዕኩልነት ውሳኔ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
- በክልሉ ውስጥ ከዎላይታ ሶዶ የሚበልጥ ከተማ ባለመኖሩ የፈርጅ ለውጥ ይኑር ቢባል እንኳን ከዎላይታ ሶዶ የሚጀምር በመሆኑ በተለየ ሁኔታ ጠቃሚ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም፣ የክልሉ መስተዳደር ሆነ የክልሉ ምክር ቤት የራሳቸውን ዕጣ ፈንታም ሆነ አስተዳደር በራሳቸው የመወሰን ሉዓላዊና ህገ-መንግስታዊ ስልጣን በተጎናጸፉ የዎላይታ ብሔር እና ሌሎች የብሔረሰብ ዞኖች የውስጥ ጉዳይ በመግባት መዋቅር ቆርሶ ለሌላ መዋቅር ተጠሪ እንዲሆኑ የመወሰን ስልጣን የላቸውም፣ ኢ-ህገመንግስታዊም ነው፡፡
- ለዎላይታ ሶዶ ከተማ በርካታ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል ከሚል አዎንታዊ ዕይታና ተስፋ የተነሳ የዎላይታ ሶዶ ከተማ በሪጅዮፖሊስ ፈርጅ መካተቱን ማንም የዎላይታ አይቃወምም፡፡ ሲቃወም አይታይም፡፡ ይሁን እንጂ ዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ተጠርነቱ ለክልሉ መንግስት መሆኑና የከተማዉ ም/ቤት አባላት እና በሕዝብ ተወካዮች እና ክልል ም/ቤቶች ከተማዉን የሚወክሉ ሰዎች ከከተማዉ ነዋሪዎች መካከል የሚመረጡ ይሆናሉ ተብሎ መደንገጉ በምንም ዓይነት መስፈርት ተቀባይነት የሌለዉ ነዉ ብለን እናምናለን፡፡ ዎላይታ ሶዶ ከተማ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ጎን እየሰፋ የነበረዉ ከተማ በሪጅዮፖሊስ ከመፈረጁ ጥቂት ወራት በፊት በዞኑ እርሻ ሰብል ምርት እና እንስሳት እርባታና ምግብ ዋስትና ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የነበሩትን በርካታ የገጠር ቀበሌዎችን ከዳሞታ ጋሌ፤ ዳሞታ ዎይዴ፤ ሶዶ ዙሪያ፤ ቦሎሶ ሶሬ፤ ሁምቦ እና ዳሞታ ሶሬ ወረዳዎች ያቀፈዉ ዎላይታ ሶዶ በመንግስታት ትኩረት ያልተሰጠዉ ነገር ግን አራት የዎላይታ ትዉልዶች በቁጭት ተነሳስተዉ ሀብታቸዉን ገንዘባቸዉን፤ ዕዉቀታቸዉንና ክህሎታቸዉን አፍስሰዉ ያለሙትና በሚያስደንቅ ፍጥነት እየለማ የሚገኝ ከተማ ነዉ፡፡
- የከተሞች የፈርጅ ለውጥ የከተሞች የዕድገት መለኪያ እንጂ ከከተማው ፖለቲካዊ ተጠሪነት ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ የከተማው ተጠሪነት ለክልሉ መሆኑ የዎላይታን ህዝብ ከዎላይታ ሶዶ ከተማ የበላይ ባለቤትነት በማውጣት የከተማውን ተቋማት ከዞኑ አስተዳደር ይልቅ ለክልሉ የላይኛው ተቋማት በማድረግ በከተማው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የዎላይታ ህዝብ በላቡ ባለማው ከተማ ሚና ሙሉ በሙሉ እንዳይኖረውና የከተማው ተጠሪነት ለክልሉ በመሆኑ መነሻ ከከተማው የሚነሱ ይግባኞች እና ቅሬታዎች በዞኑ በኩል ስለማይታዩ ወደተበታተኑት የክልሉ የማዕከል ከተሞች ነዋሪዎችን እንዲጉላሉ የሚያደርግ፣ ለዎላይታ ዞን አጠቃላይ አመራር በዎላይታ ሶዶ ከተማ ላይ ምንም ዕጣ ፈንታ እንዳይኖረው የሚያደርግ፣ የብሄሩ ተወላጆች እና መዋቅሮች በዎላይታ ሶዶ ላይ ያላቸውን ባለቤትነትና ተሳትፎ የሚገድብ የዎላይታ ህዝብን ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን በገሃድ ቀልብሶ ማዕከላዊ ጠቅላይ አሃዳዊ ስርዓት ስር እንድትሆን የሚያደርግ የየስልጣን ጥማት እና በአገሪተሀ ላለፉት 6 ዓመታት የዘለቀው አውዳሚ የእርስበርስ በጦርነት፣ ሙስና እና አላስፈላጊ ውጪ ምክንያት ክልሉ የገጠመውን የአገሪቱን እና የክልሉን በጀት እጥረት የከተሞችን መሬት ለመቸብቸብ እንዲያመች ስልጣንን ከዞኖች ነጥቆ በመውሰድ ነገ ጠያቂ የሌላችው ከተሞች የሙስና እና የጥገኛ ዋሻ የሚድረግ ነው፡፡
ስለሆነም በየትኛውም መልኩ የሚቀርብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ማህበራዊ መደራደሪያ ከዎላይታ ሶዶ ከተማ ለክልል ተጠሪነት መፈቀድ የለበትም፡፡ የደቡብ ክልል መንግስት ከተሞችን ስልጣን እና የሪሶርስ ቀምቶ ስልጣንና ሀብት ባለቤትነት ጠቅልሎ ለክልል መንግስት በማድረግ በተለይ የዞኑ ህዝብ በከተሞች ምንም ሚና እንዳይኖር በማድረግ ከተሞችን እድገት ለማቀጨጭ እና የከተሞችን ሀብት ለመመዝበር እናም እድገታቸውን ለመቀልበስ የሚሰራው ማንኛም Power centralization and economic exploitation የእጅ አዙር ግዞትና ቅኝ አገዛዝ ስርዓት ላለፉት ሁለት /2/ ዓመታታ ተጠሪነታቸው ለክልል የሆኑትን /አስራ ሁለት/12 ዞኖችን እንኳን መምራት ያልቻለው እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከተሞችን በክልሉ ስር ለማድረግ ማሰብ ለእድገትና ለልማት ሳይሆን ለጠቅላይነት እና ለብዝበዛ ህጋዊ ማዕቀፍ ለማበጀት ነው።
ከሁሉም በላይ ከተሞችን ያለሙት የዞኖቹ ህዝቦች አርሶአደሮች፣ ተማሪዎች መንግስት ሰራተኞች እና የንግዱ ማህበረሰብ ጡረተኞች በመላው አለም የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች ከመቀነታቸው እና ከእለት ጉርሳቸው ቀንሰው የገነቡትን ህዝብ ባለቤትነት ቀምቶ ወደ ቤት ግባ ማለት የፌደራሊዝም ትሩፋት የሆነውን በብሔር ብሔረሰቦች ደምና አጥንት ዋጋ ተከፍሎበት የመጣውን የዞን የከተሞች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከዞን ቀምቶ ያልተማከለ ፌደራላዊ ስርዓት በመናድ በክልሉ የተማከለ ጠቅላይ አሃዳዊ አስተዳደር ስርዓት የመዘርጋት እንቅስቃሴ አስቸኳይ እንዲቆም አጥበቀን እናሳስባለን።”
የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ/#ዎብን፣ የዎላይታ ሕዝብ ደሞክራሲያዊ ግንባር/#ዎህዴግ/ እና የዎላይታ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/#ዎሕነን/ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የሪጅዮፖሊስ ከተሞች ለማደራጀት ያወጣውን አዋጅ በመቃወም የጋራ የአቋም መግለጫ
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏