በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ

የዎላይታ ታይምስ የፖለቲካ ወጌሻ ጥንቅር 👇
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ አዳዲስ የፍጥነት መንገዶች፣ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ነቀምትና ጅማ ለመገንባት ጥናት እያካሄደ መሆኑን አሳዉቋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያሎት አስተያዬት ምንድነው ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በጣም ጥሩ ጅምር ነው። በተለይ ነቀምት ለዘመናት፣ አሁን ያለዉን መንግስት ጨምሮ ስትገፋ የኖረች የወለጋ ከተማ በመሆኗ፣ ለልማቱ በመታጨቷ በተለዬ ሁኔታ አስደስቶኛል። የፍጥነት መንገድ ወይንም express way ማለት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት እንዲደሩሱበት ታቅዶ የሚገነባ መግቢያና መዉጫዉም ዉስን የሆነ መሄጃ እና መመለሻውም በግልጽ ተለይቶ የሚሰራ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለዉ መንገድ ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ቀድሞ የተሰራዉ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እንደነበረም ይታወሳል። መንገዶቹ የጉዞ ሰዓትን በመቀነስ ትልቅ ጥቅም ያስገኛሉ። ለኢኮኖሚ እድገትም ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ። ሰሞኑን የተገለጹ መንገዶችም ከዚህ አኳያ መሠራታቸዉ ጥሩ ሆኖ፤ መንገዶቹ በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ብቻ መሠራት አሁንም ልማት በኦሮ_ማራ ቀመር ነው እንዴ የሚሠራዉ የሚል ተጨማሪ ጥያቄን ይፈጥራል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በተለይም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስመር፦ ከአዲስ አበባ ቡታጅራ – ወራቤ – ሆሳዕና – ዎላይታ ሶዶ -አርባምንጭ – ኮንሶ – ሞያሌ መስመርም ቀጥተኛ 3 ክልሎችንና ኬንያና ትላልቅ ከተሞችን ስለሚያገናኝ ፈጣን መንገድ Express way ያስፈልገዋል በሚል በርካቶች ይሞግታሉ። ምን ሀሳብ አለዎት ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በእዉነቱ ስለ ፍትሐዊ ልማት ከሆነ የምናወራዉ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ሁለት ሁለት አግኝተዉ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ዎላይታ ሶዶ፣ ከሱማሌ ጅግጅጋ፣ ከትግራይ መቐለን ጥናቱ አለማካተቱ ጥያቄ ያስነሳል። ልማት በፍትሐዊነት ካልተዳረሰ ሌላ ችግር እንደሚፈጥርም ይታወቃልና ሌሎች ክልሎችም ላይ ልማት መሠራት አለበት እንደ የአስፈላጊነቱ በተጨማሪም እነኝህ መንገዶች ይሠራሉ የተባሉባቸዉ ክልሎች ጦርነት አለባቸዉ ስለዚህ ሰላም በሌለበት የመንገድ ስራ አስቸጋሪ ነዉና ለሰላም ቅድሚያ መሰጠት አለበት።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በአጠቃላይ ከእንግዲህ በኢትዮጵያ የሚሰሩ የፍጥነት መንገዶች ከግምት ማስገባት አለባቸዉ ብለዉ የሚያነሷቸዉ ነጥቦች ካለ ቢጠቁሙን ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አንደኛው ድሮ መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያመራሉ ይባል ነበረ። በኢትዮጵያም መንገዶች የሚሰሩበትን እሳቤ ስታይ መንገዶች ሁሉ ወደ አዲስ አበባ ያመራሉ በሚል ፍልስፍና የሚመራ ይመስላል። የጎንዮሽ ግንኙነት ብዙ ትኩረት ተሰጥቶት አያዉቅም፣ ብዙ ቦታ የሚኬደዉ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደዉ መንገድ እየሄዱ ዞሮ በመመለስ ነው።
ወደቦችን ከክልል ከተሞች፣ የክልል ከተሞችንም ከክልልና የዞን ከተሞች ጋር ለማስተሳሰር አቅም በፈቀደ መጠን በትኩረት መሠራት አለበት። በርግጥ ከሞጆ ወደ ባቱ እና ወደ አዋሳ እንዲሁም ከድሬዳዋ ደወሌ የተሰራዉም ጥሩ ነዉ፥ የተጀመሩትም ከብልጽግና በፊት ነው፣ ብልጽግና ደግሞ ሁሉንም ከአዲስ አበባ ጋር ብቻ ለማገናኘት ማቀዱ መታረም አለበት። የአዋጭነት ጥናት እንደተጠበቀ ሆኖ።
ሁለተኛዉ የፍጥነት መንገዶችን ከመደበኛው መንገድ ዲዛይን ከሚለያቸዉ ነገሮች አንዱ የግድ ከተሞች እንዲያቋርጡ አለመደረጋቸዉ እና በሚያጥረዉ በኩል (shortest route)ላይ የበለጠ ስለሚተኮር ነው። ስለዚህ ብዙ መገንጠያ እና መግቢያ በማስቀመጥ ከየ ትንንሽ ከተሞች ጋር ማገናኘት ባይቻልም፤ ትልልቅ ከተሞች ግን መገንጠያና መግቢያ እንዲኖራቸዉ ቢደረግ መልካም ነዉ። ከወዲሁ ዲዛይኑ ይህንን ከግምት ማስገባት አለበት። አለበለዚያ ብዙዎችን የበይ ተመልካች አድርጎ ቅሬታ ሊፈጥር ይችላል ብቻ ዲዛይኑ ጥንቃቄ ይፈልጋል ለማለት ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ከዚህ ቀደም በኢትዮጲያ ከተሰሩ የፍጥነት መንገዶች በመነሳት ምን መሻሻል አለበት ይላሉ ? ሌላ ተጨማሪ የሚሰጡት አስተያዬትም ካለ ያክሉበትና የዛሬዉን ቆይታችንን እናጠናቅቅ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እና ወደ ባቱ የሚሄደዉን የፍጥነት መንገድ የወሰድን እንደሆነ በጣም አስደማሚ ሥራ ነው። ምናልባት መንገዱን ተከትሎ የተተከሉ ዉብ ዛፎች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የትራፊክ ምልክቶችን የሸፈኑበት ሁኔታ አለ። ይህ አደገኛ ስለሆነ አሁኑኑ መታረም ያለበት እና ለወደፊትም ዛፎች የትራፊክ ምልክቶች ካሉበት ቀጥለዉ ወይንም ወጣ ተደርገዉ ቢተከሉ የተሻለ ነው። በምንም መልኩ የትራፊክ ምልክት ካለበት ፊትለፊት ዛፍ መተከል የለበትም፣ ሲያድግ ምልክቱን በመጋረድ አደጋም ሊያስከትል ይችላል።
ሁለተኛዉ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እና ባቱ የሚወስደዉ መንገድ ሁለቱም በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ ሆኖ እያለ የትራፊክ ምልክቶች ግን ጽሁፉ በኢንግሊዝኛና በአማርኛ ብቻ መጻፉ ተገቢ አይደለም። በተጨማሪነት በኦሮምኛም መጻፍ ነበረበት፣ ይህ አሁንም መታረም ያለበት ነው። በሶስት ቋንቋ መጻፉ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለዉም፣ ሕዝቡም ልማቱን የእኔ ነው እንዲል ያግዛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
Ethiopia #southethiopia #Amhara #oromo #Tigray
ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥንቅር ነው