1000037714

ኢህአዴግ የአማረኛ ተናጋሪ ሲጠላ፥ ብልፅግና የብሄረሰቦች አንድነት ለምን ይፈራል ? የከተሞችን ተጠሪነት ለክልል በመስጠት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መንጠቅ ለምን ? ኢትዮጵያ የሚባል ብሔር አለ? የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፖለቲካ ወጌሻ ዝግጅት እንደሚከተለው ዝርዝር ሀሳቡን አቅርቧል።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አከራካሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዷ እንደሆነች ይታወቃል። በሐገራዊ ምክክሩ ከቀረቡ አጀንዳዎች አንዱ አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ በኦሮሚያ ክልል ስር እንድትሆን የሚጠይቅ ነው፣ ፊንፊኔ፣ በረራ የሚሉ መከራከሪያዎች ይታወቃሉ።

ባልደራስ የሚባል ፓርቲ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ክልል ትሁን የሚል አቋም እንዳራመደም ይታወሳል፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ እርሶ ያልዎት አቋም ምንድነዉ ?

በሐገራዊ ምክክሩ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች በተለይ የደቡብ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ምን አይነት አቋም ማራመድ አለባቸዉ ብለዉ ያምናሉ? ብልጽግና የከተማን መሬት የግለሰብ የማድረግ እቅድ እንዳለዉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወቃል፣ ሰሞኑን ደግሞ ዎላይታ ሶዶ ሪጂዮፖሊታን ከተማ ስትደረግ ብልጽግና ሕገመንግስቱ ሳይቀየር ተጠሪነቷን ለክልሉ መንግስት አድርጓል ጠቅለል አድርገዉ በእነኝህ ጉዳዮች ላይ አስተያዬቶትን ቢሰጡን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ አመሰግናለሁ። ወቅታዊዉ የብልጽግና አካሄድ ከተማ ለአማርኛ እና ኦሮምኛ ተናጋሪዎች፣ ገጠር ለብሔሮችና ብሔረሰቦች የሚል ነው። በአብዛኛው የዘዉዳዊዉ እና የወታደራዊው አገዛዝ አስተሳሰቦች አጣምሮ የያዘ አካሄድ ነው። ሐገሪቷን ብልጽግና ወደሁዋላ ወስዷታል ስንል በመሰል ግልጽ ማስረጃዎች አስደግፈን ነው። የብልጽግና ትልቁ ችግር ታማኝነቱ ለሕገመንግስቱ ሳይሆን ለስልጣን ማጽኛነት ኦሮ_ማራ እና ለአጃቢዎቹ መሆኑ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሐገረ መንግስትም የብሔረ መንግስትም ግምባታ መክሸፉ በግልጽ ከሚታይባቸዉ ነገሮች አንዱ ከተማ ነው። አዲስ አበባ የዉዝግብ ማዕከል ነች፣ አዋሳ ዎላይታ ክልል ጠይቆ በተከለከለበት ከዎጋጎዳ ትግል በሁዋላ በ56 ብሔሮችና ብሔረሰቦች ለምታ የዎላይታ ሕዝብ ዘግናኝ ጭፍጨፋ አስተናግዶባት አሁን የሲዳማ ክልል ስር ነች። ከተሞች ከአስተዳደር ከቋንቋ እና culture friendly መሆን አለባቸዉ ከሚለዉ አንስቶ ስያሜያቸዉም በኢትዮጵያ ዉስጥ ከፍተኛ ዉጥረት የሚታይበት ነው።

ደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ)፣ ዝዋይ(ባቱ)፣ አዲ አርቃይ (ሰላምበር (ወረዳ ነው ))፣ አሰበ ተፈሪ (ጭሮ) እና የመሳሰሉትን ብናይ ከተማን ከአማርኛ ተናጋሪነት ጋር የማስተሳሰር የቀድሞ አገዛዞች እና ናፋቂዎቻቸዉ ፍላጎትና የየአካባቢው ሕብረተሰብ ዉጥረት በግልጽ ይታያል። አዋሳ የሚለዉ ዎላይትኛ ነው የሚባለዉ መጠሪያም ሐዋሳ ተብሎ ወደ ኦሮምኛ የተቀየረበትንም አጋጣሚ ማስታወስ ይቻላል።

ሰዉ ከተሜ መሆን ይፈልጋል፣ ከተማ የስልጣኔ፣ የኢኮኖሚ፣ የተሻለ የመሠረተልማት አቅርቦት፣ የሥራ እድል፣ የተሻለ ኑሮ ማዕከል ነው። በኢትዮጵያ የድሮ አገዛዞች እና ናፋቂዎቻቸዉ ከተሜነትን በአማርኛ ለዉሰዉ ያቀርባሉ። ስለዚህ በተዘዋዋሪ ከተሞች የስልቀጣ ማዕከላት (assimilation centers) ሆነዉ ኖረዋል። ከተሜ ለመሆን የግድ ወደ አማርኛ ተናጋሪነት ሰዉ መለወጥ አለበት ወይ የሚለዉ ወሳኝ ጥያቄ ነው።

በዚሁ ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ መጽናናትን እየተመኘን በቅርቡ ያረፉት አንጋፋው ፖለቲከኛ እና የቅንጅት አመራር የነበሩት ዶክተር በፌቃዱ ደግፌ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለዉ ነበረ፦ 👇

«አማራነት መንፈስ ነው። አማራ ለመሆን የማይፈልግ የለም። አንድ የደቡብ ክልል ህጻን ለምንድነው የምትማረው ሲባል አማራ ለመሆን ይላል።» “ከዛላ አንበሳ ጀምሮ እስከ ደቡብ መጨረሻ ድረስ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ድረሰ አማራ ነኝ የማይል አማራ ለመሆን የማይፈልግ የለም ዛሬ የወያኔ ጠላትነቱ አማራን በአማራነቱ ሳይሆን አማራ መንፈስ በመሆኑ ነው ወያኔ ዛሬ የተሸነፈውም አማራ መንፈስ በመሆኑ መንፈስን ማሸነፍ ስላቃተው ነው” ይህ አባባላቸዉ የዘነጋዉ አንድ ሐቅ ቢኖር ሰዎች የሚፈልጉት አማራ ወይንም አማርኛ ተናጋሪ መሆን ሳይሆን ከተሜ መሆንን ነው።

በአማርኛ ተለዉሶ የሚቀርብ የከተሜነት እድል
urbanization backed by cultural assimilation ለዘመናት በሐገራችን በመንሰራፋቱ የተፈጠረ ችግር ነው። ይህ ሰዎች አማራ መሆን የሚፈልጉበት ምክንያት ብዙ ታሪካዊ መነሻዎች ያሉት ቢሆንም ይህ ጽሑፍ ከከተማ አንጻር ብቻ ለመዳሰስ እንደሚሞክርም ይሰመርበት።

ወደ አዲስ አበባም ስንመጣ ችግሩ በሰፊዉ ይስተዋላል፣ አዲስ አበቤ ለመሆን አማርኛ መናገር አለብህ፣ አገልግሎትም ሆነ ትምህርት በመንግሥት የሚሰጥህ በአማርኛ ሆኖ ነው የኖረዉ። ከተማዋ ለዘመናት በመንግሥታት ጫና የኦሮሞን ጨምሮ የብሔሮችንና ብሔረሰቦችን ቋንቋ ገፍታ ኖራለች። ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በቀኃሥ ጊዜ ስለነበረዉ ሁኔታ እንደሚከተለዉ ያብራራሉ “ጀነራል ታደሠ ብሩ (በጥቅምት 23፡ 1958 ዓ.ም ይመስለኛል ) ንጉሡን ለመግደል አሲረዋል የሚል ወሬ ስለ ተሰማ፣ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ሸፍተዋል” ተብሎ በስፋት ተሰራጨ።

በአዲስ አበባ ለነበሩ ኦሮሞዎች ልዩ ስሜት ፈጠረ። ከዚህ በፊት በአፋን ኦሮሞ ለመነጋገር የሚፈሩ ወይም የሚያፍሩ ሁሉ በቋንቋዉ መናገር ጀመሩ። ቋንቋውን የማይችሉትም ለራሳቸው ና ለቤተሰቦቻቸው አባላት የቋንቋዉ መምህር መቅጠር ጀመሩ።” ሰዎች በቋንቋቸው ለመናገር የሚያፍሩትና የሚፈሩት የሐገሪቷ ሥሪት ስለሚያሸማቅቃቸዉ ነው፣ ብዙ ተጽዕኖ እና መገፋትም ስለሚደርስባቸው ነው።

በመሰል ጫና ስር የሚያድጉ ሰዎች ከተሜነትን ከአማርኛ ቋንቋ ጋር በጫና ምክንያት አዋህደዉ ተሰልቅጠዉ ስለሚያድጉ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በስነልቦና ከቤተሰቦቻቸው ብሔርናብሔረሰብ ጋር detached ይሆናሉ። ለምሳሌ መንግስቱ ኃይለማርያም የተወለደበት እና ያደገበት ቦታ እንዲሁም የቤተሰቦቹ ማንነት አወዛጋቢ ቢሆንም፤ በርግጠኝነት የሚታወቀዉ ግን ብሔሩ ከአማራም ብቻ ሆነ ከትግራይ እንዲሁም ከኤርትራ ወገን አለመሆኑ ነው፤ ይሁን እንጂ መንግስቱ ከአማርኛ ቋንቋ ዉጪ የትኛውንም የኢትዮጵያ ቋንቋ አይችልም።

በወቅቱ መልኩ የጠቆረ ሰዉ ባሪያ መባሉ እንደሚያስቆጨዉ በምሬት መናገሩ ይነገራል፣ አለፍርድ 60ባለስልጣናት ወደ ሚረሸኑበት በሚወሰዱበት ጊዜ ከመሐላቸዉ አንዱ “ይሄ ባሪያ አለፍርድ ሊያስፈጀን ነው።” ይል እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። መንግስቱ በስመ ከተሜነት የአማርኛ ተናጋሪ ሆነዉ ይደጉ እንጂ አጠቃላይ የሐገሪቷ ሥሪት ከማንነታቸዉ ተነስቶ እንደሚገፋቸዉ ይታወቃል።

“የነዋርዲት ወንድም” ይባልም ነበረ፤ ይሁን እንጂ መንግስቱ መሰል የብሔር ጭቆናዎች የወለዷቸዉን የብሔር ድርጅቶች እንደጠላት ያይ ነበር። ስለቤተሰቦቻቸዉ ብሔር ወንድሙ፣ በአባትም፣ በእናትም ኦሮሞ ነን ብሏል፣ አንዳንድ በቅርበት እናዉቃለን የሚሉ ሰዎች ደግሞ በአባት ኦሮሞ በእናት ዎላይታ ናቸዉ ይላሉ። እርሳቸዉ ደግሞ ከአማራ እና ከኦሮሞ እንደተወለዱ ይናገራሉ። በተለይም ከወደ አማራዉ አለኝ በሚሉት ዝምድና እራሳቸዉን መግለጽ ይፈልጋሉ።

መንግስቱ ኃይለማርያም አያና ቢሆንም ሙሉ ስማቸዉ በዘመነ ስልጣናቸዉ አያና ተጠርቶ አያዉቅም። በመላዉ ኢትዮጵያም ሰዎች ለልጆቻቸው የአማርኛ ስም የሚያወጡት፣ በዋናነት በከተሞች የሚታዬዉ ስልጣኔና የተሻለ ኑሮ በአማርኛ ተለዉሶ በመቅረቡና ለልጆቻቸዉም የተሻለ ነገር መመኘታቸዉ እንደሆነ አያጠራጥርም ድሮ ደግሞ ቀጥተኛ ጫናም ነበረ።

የጋሞ አካባቢ ሊህቃንም በአንድ ወቅት ልጆቻችንን በቋንቋችን አናስተምርም፣ ቋንቋችን ወንዝ አያሻግርም ያሉት የዚህ ተጽዕኖ ሰለባ ስለነበሩ ነው። የልጆቼን ሰብአዊ መብት ካላስጣስኩ የሚለዉ ጥያቄ በርግጥ ፖለቲካ ቋንቋን ከወንዝ አሻግሮ የፌደራል ሥራ ቋንቋ ማድረግ እንደሚችልም አለመገንዘብ ቢሆንም ጥያቄ ባለማወቅ የተነሳ እንጂ ክፋት የለዉም።

በቤተመንግስትም በቤተክነትም በትልቅ ደረጃ የሚታየዉ የአማርኛ ስም ነዉ፣ በኪነትም በድርሰትም፣ በሚዲያውም በኩል ብዙ ተጽዕኖ ይደረጋል። ብሔረሰብ ቋንቋ ስሞች መሳቅና መሳለቅም በኢትዮጵያ ለዘመናት የተለመደ ነገር ነው ስለዚህ ተጽዕኖዉ ቀላል አይደለም።

አዲስ አበባ በኢትዮጵያ አንደኛ ከተማ ነች፣ ለመወዳደር አጠገቧ የሚጠጋ ከተማ እንኳን የለም። ፍጹም ጤና በጎደለዉ ሁኔታ የሐገሪቷ ሐብት የተከማቸባት ከተማ ነች። የሁሉም ኢትዮጽያዉያን ከተማ ከመሆንም አልፋ የአፍሪካ መዲናነቷም መረሳት የለበትም። ወደ ኦሮሚያ ክልል ትጠቃለል የሚለዉ ልክ እንዳልሆነዉ ሁሉ ክልል ትሁን የሚለዉም ተገቢ አይደለም አንድ ክልል የሐገሪቷን ግማሽ ሐብት ሊይዝ ካለመገባቱም በላይ የከተማዋ ሕዝብ ስብጥርና ነባራዊም ታሪካዊዉም እዉነታ ክልልነትን አያጎናጽፋትም እንደሌሎቹ።

chartered city ሆና መቀጠሉ የተሻለ ይመስለኛል። አሁን ኦሮሞ ልጆቹን በቋንቋው የማስተማር መብቱን በሙላት ያስከበረ ይመስላል እንጂ፤ ለዘመናት አዲስ አበቤ ማለት አማርኛ የሚናገርና ልጆቹንም በአማርኛ የሚያስተምር ሆኖ ኖሯል። የብሔሮች እና ብሔረሰቦች መናሐሪያ ነች፣ የአፍሪካም መዲና ነች በምትባለዉና ያለተቀናቃኝ የኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ ከተማ የሆነችዉ አዲስ አበባ ቋንቋዋ አማርኛ ብቻ እንዲሆን ተደርጎ ኖሯል።

በአለምም ሶስተኛ የዲፕሎማቲክ መናሐሪያ በመሆኗ expats እንደሚበዙና በተለይ ኢንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ቻይንኛ በከተማዋ አስተዳደር በመንግስትም ሆነ በትልልቅ የግል ተቋማት እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ትኩረት ይፈልጋል።

አሁን ደግሞ የከተማ መሬትን የግለሰብ የማድረግ ጸረሕገመንግስታዊዉ የብልጽግና እቅድ ከዚህ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ይፋ መደረጉ ይታወቃል። የኢፌዲሪ ሕገመንግሥት “አንቀጽ40፡3. የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስት ናየሕዝብ ብቻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” ይላል።

ይህ እንግዲህ ከብሔሮች እና ብሔረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን፣ ቋንቋን የመጠቀም፣ ሕልዉናን አስጠብቆ የመቆዬት ዋስትና፣ የሐገሪቷን ፈዴሬሽንነት ከጀርባዉ ያዘለና ሐገሪቷ በታሪኳ በዘመነ ኢህአዴግ ላየችዉ አንጻራዊ ሰላም የድርሻዉን ያበረከተ አንቀጽ ነበር። እንግዲህ ብልጽግና እንደቀላል ነገር ሕገመንግሥት ጥሶ፣ ሐገሪቷን ያልበላትን እያከከ ነው።

የዎላይታ ሶዶ ተጠሪነት ለክልሉ መደረግም ለዚህ የብልጽግና ግብ ቅድመ ሁኔታ ይመስላል። ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት …

አንቀጽ 49 – ርዕሰ ከተማ

  1. የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡
  2. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
  3. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት ይሆናል፡፡
  4. የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሰረት በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወከላሉ፡፡
  5. የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡” ይላል። በተጨማሪነት የኦሮሚያ ክልል ሕገመንግሥት ፊንፊኔ ዋና ከተማ ነች ይላል የክልሉ (አዲስ አበባ ማለት ነው )። በግሌ ከላይ የተጠቀሱ ነገሮች ላይ ተቃዉሞ የለኝም፣ መብቱ በሙላት አለመከበሩ አንዱ ለዉጡን ካመጡ ጉዳዮች አንዱ ነዉና። ነገር ግን የአዲስ አበባ አስተዳደር የሥራ ቋንቋ ብዙ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፣ ለምሳሌ ዎላይትኛ፣ ትግርኛ፣ ጉራጊኛ፣ ሱማሌኛ እና የመሳሰሉት መታቀፍ አለባቸዉ። የኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ ከተማ የሆነችዉ አዲስ አበባ ከክልል ሕዝቦች ጋር በዘላቂነት እንድትተሳሰርና የእዉነትም የሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች መሆን አለባት። የኦሮሚያ ክልልም ቢሮዎቹን፣ ጨፈዉን ጨምሮ በአዲስ አበባ ቢያደርግ ተገቢ ነው እላለሁ። በጸጥታ ረገድ የአዲስ አበባ ፖሊስና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ተቀናጅተዉ የሚሰሩበት ደምብና መመሪያ ምናልባት ያስፈልግ ይሆናል። በተረፈ ግን የአዲስ አበባ ፖሊስ ስልጣኑ መሸራረፍ የለበትም።

ወደ ዎላይታ ሕዝብ ጉዳይ ስንመለስ የዎላይታ ሕዝብ የሁለተኛ ደረጃ ከተማዉ አዋሳ ነበረች ከለዉጡ በፊት እንግዲህ ከጭፍጨፋዉ በሁዋላ ብዙ ሰዉ ያሰበዉ ዎላይታ ሶዶ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከተማነት እንድትመጣ በማድረግ መንግስት ሕዝቡን ይክሳል የሚል ነበር። አሁንም በጉልበት በተፈጠረዉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕዝብ ቁጥሩ የሚበልጠዉ የዎላይታ ሕዝብ፣ ትልቁ ታሪካዊዉ እና ጥንታዊዉ ከተማ ዎላይታ ሶዶ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሁለተኛ ደረጃነት ዎላይታ ሶዶ እንደማትመጣ እና የዎላይታ ሕዝብም መንከራተቱ እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ አሳዉቋል፣ ይህ እንግዲህ ግልጽ የብሄር ጭቆና ነው።

ሕዝቡ ኢንዱስትሪ ዞን ይከፈት ሲል አልከፍትም ብለዋል ቃል በቃል። በመሰረቱ ብልጽግናን ጨምሮ ሁሉም የኢትዮጵያ መንግስታት ሁሉም በጋሞ ስር ያሉ ዴሬዎች፣ ዳዉሮ፣ ጎፋ እና ኮንታ የዎላይታ አካል እንደነበሩ፣ በየትኛውም መመዘኛ መሰባሰብ ያለባቸዉ በቁጥር አብላጫ በሆነዉ ሕዝብ ዙሪያ መሆኑን ልቦናቸዉ ያዉቀዋል፣ ጥንታዊ ማዕከላቸዉም ዎላይታ እንደነበረ ልቦናቸዉ ያዉቀዋል።

ሕዝቦቹ ተመሳሳይ ቋንቋ እና ባህል ስላላቸዉ በጋራ ከተማ መሥራት እንደሚችሉም ግልጽ ነው በተለይ የባህልና ቋንቋ መመሳሰል ጠቃሚ እንደሆነ ይታወቃ፣ culture friendly ከተማ ለመሥራት ያግዛል። ብልጽግናን ጨምሮ የኢትዮጵያ አገዛዞች ያ ሕዝብ በዎላይታ ሶዶ ከተሰባሰበ የዝሪፍያና የቅሚያ አጀንዳቸዉ ዉሃ እንደሚበላዉ እና የሕዝቦቹ እንኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መብት መረጋገጡ ግዴታ እንደሚሆን ያዉቃሉ።

ዎላይታ ሶዶን የሚሸሹት ሕዝቡን የመርገጥ ሕልማቸዉ ማርከሻ የቡዳ መድኃኒት መሆኗን ስለሚያዉቁ ነው። ብልጽግና አይደለም ያ ሁሉ ወንድማማች ሕዝብ ተሰብስቦባት እንዲሁ የዎላይታ ዞን ብቻ መቀመጫ የሆነችዉን ዎላይታ ሶዶ ሕገመንግስታዊዉን ፖለቲካዋን ፈርቶ አሰቃቂዉን የዘር ማጥፋት ጦርነት በትግራይ ሕዝብ ላይ ከማወጁ በፊት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ጎራ ብሎባታል።

ብልጽግና ዳዉሮንና ኮንታን ከተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪ ጎፋ፣ ጋሞ እና ዎላይታ ጋር ሲለያይ ለተንኮል መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሓፊ ነን ባዬች የሕዝቦቹን ታሪክ እያዛቡ እንደሚያቀርቡ የብልጽግና ተንኮል አመንጭዎች ግምባር ቀደሙ ዳንኤል ክብረት በተመረዘ አስተሳሰቡ የጻፈው የትርክት እዳ መጽሐፍ ምስክር ነው። የዳዉሮና ኮንታ መቆረጥ ሳያንስ በክልሉ አብዛኛው ሕዝብ የሚናገረዉ ዎላይትኛ ቋንቋ የፌደራል የሥራ ቋንቋ አለመደረጉ ሳያንስ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አለመሆኑም ሌላ እንቆቅልሽ ነው።

ይርጋለም፣ አዋሳ፣ አርባምንጭ ከዛም ድጋሚ አዋሳ በመንከራተት ሲያለማ የኖረዉ የዎላይታ ሕዝብ ከእንግዲህ ይታለላል ብሎ ማሰብ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም ፍንትዉ አድርጎ ያሳያል። የዎላይታ ሕዝብ የሁለተኛ ደረጃ ከተማ ባለቤትነት ጥያቄዉን በዎላይታ ሶዶ በኩል፣ የአንደኛ ደረጃዉን በአዲስ አበባ ቋንቋዉን የሥራ ቋንቋ በማድረግ ማስመለሱ አይቀሬ ነው።

በመሠረቱ የከተማ ጉዳይ እርሳቸዉ ስልጣን የያዙበት ለዉጥ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ እንዴት ይጠፋቿል ( ማስተርፕላኑን ልብ ይሏል) ? የእርሳቸዉ ክልል የሆነዉ ኦሮሚያ ሸገር ብሎ አዲስ አበባን የከበበ ከተማ መመሥረቱ ሳያንስ (ቢሮዎች በከተማዉ መሆን ሲገባቸዉ በአዲስ አበባ መደረጉ አወዛጋቢ ነው )፣ የ500ሺ አባወራ ቤት በጭካኔ በሕገወጥ ግምባታ ስም ያፈረሰዉ እራስን የሚመስል ከተማ ለመሥራት አይደለምን ? ከአዋሳስ ዎላይታዎች የተጨፈጨፋት ለምን ነበር ?

የጭፍጨፋዉስ ተሳታፊዎች አላማቸዉ ምን ነበር ? እና በዚህ አይነት ሐገር የአንድን ሕዝብ መብት የከተማ መብት በፓርቲ ስብሰባ መልዕክ በማስተላለፍ አስቀይራሎ ማሰብ የጌታቸዉ ረዳን አባባል ልዋስና “የፖለቲካ ድንክዬነት ነው።”

INTERNATIONAL COVENANT ON CIVIL AND POLITICAL RIGHTS በአንቀጽ 1 “ሁሉም ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አላቸዉ። በዚሁ መብታቸው መሠረትም የፖለቲካ ሕልዉናቸዉን ይወስናሉ፤ ኢኮኖሚያ፥ ማኀበራዊ እና ባሕላዊ ዕድገታቸዉን በነጻነት ያራምዳሉ።”

ይህ የከተማን ሕዝብ ወደ አማርኛ ተናጋሪነት ስልታዊ በሆነ መንገድ ለመቀየር መጣር በምንም ተአምር የሚሳካ አይደለም። በቅርቡ ብሥራት FM የሚከተለዉን ዘገባ አቅርቦ ነበር… “ጉራግኛ ቋንቋ ተናጋሪ እያጣ በመምጣቱ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ተባለ የጉራጌ ማህበረሰብ ቋንቋ የሆነዉ ጉራግኛ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተናጋሪ እያጣ መምጣቱን እና ይህንኑ ተከትሎም የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ተነግሯል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዉቲንግ እና ኢኖፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን መምህር ኮራብዛ ሸዋረጋ ለብስራት ሬዲዮ ሲናገሩ 3 ሚልየን ገደማ ይደርሳሉ ተብለዉ ከሚገመቱት የጉራጌ ማህበረሰብ ተወላጆች ዉስጥ ከ25 በመቶ የማይበልጡት ብቻ ናቸዉ ቋንቋዉን አቀላጥፈዉ የሚናገሩት ብለዋል::

ከዚህ በተጨማሪም የጉራግኛ ቋንቋ በብዛት በዕድሜ በገፉ ሰዎች ዘንድ ብቻ ተዘዉትሮ የሚነገር ሆኖ መቅረቱ በአንፃሩ በጉልምስና እና በወጣትነት የዕድሜ ዘመናቸዉ ላይ የሚገኙ የብሄሩ ተወላጆች ከጉራግኛ ይልቅ አማርኛ አብዝቶ የመናገር ዝንባሌ ዉስጥ መግባታቸዉ ቋንቋዉ ተናጋሪ እያጣ እንዲሄድ ማድረጉን ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህር ከአቶ ኮራብዛ ሸዋረጋ ሰምተናል።

ለመፍትሄዉ ‘የጉራግኛ ቋንቋን ከተናጋሪ ዕጦት እታደገዋለሁ’ የሚለዉ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዉን በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሌሎች አጫጭር ስልጠናዎች ለማስተማርስርዓተ- ትምህርት የመቅረፅ እና የትምህርት ክፍል የማደራጀት ስራ በማከናወን ላይ ነዉ።”

ይህ ችግር በአዲስ አበባ ያለዉን ጉራጌ ብቻ ብንወስድ እንኳን ልጆቹን በቋንቋዋዉ ወይንም ቋንቋዉን የሚያስተምርበት እድል ቢመቻች ቋንቋዉ የመጥፋት አደጋ አይጋረጥበትም ነበር።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጎርጎሮሳዉያን የዘመን ቀመር 2050 ላይ 68% የአለም ሕዝብ በከተሞች ይኖራል ብሎ ተንብዩአል። በዝህ ስሌት ከሄድን በኢትዮጽያ የጉራጌ እጣ ሌሎቹም ላይ እየመጣ ነው ከ25ዓመት በሁዋላ በብልጽግና መንገድ ከሄድን አብዛኞቹ ብሄሮች ወደ አማርኛ ተናጋሪነት ይሰለቀጡና ይጠፋሉ ጥቂት ቋንቋዎች በየገጠሩ ጥጋጥግ ይቀራሉ።

አማርኛና ኦሮምኛ በብቸኛነት ትርጉም ባለዉ ደረጃ ይተርፋሉ ማለት ነው። ለኢትዮጵያ የሚበጀዉ መንገድ አሁን ባለዉ የፌደራል ሥርዓት መሠረት ሕዝቦች በየአካባቢያቸው ቀንቋና ባህላቸዉን የመጠቀም መብታቸዉን ባከበረ መንገድ የሁለተኛ ደረጃ እና የሶስተኛ ደረጃ ከተማ እንዲያገኙ በማድረግ በተጨማሪም፣ አዲስ አበባ ላይ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ቋንቋ ሥራ ላይ በማዋል፣ ቋንቋ ሳይገድባቸዉ የመጀመሪያ ደረጃ ከተማ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደሆነችዉ ሁሉ የቤልጅየሟ ብራሰልስ፣ የአዉሮፓ መዲና ነች። የአዉሮፓ መዲናነቷ ግን ለሐገሯ ቋንቋዎች እድል እንዳትሰጥ አላደረጋትም። የተወሰነ ቅሬታ አሁንም ቢኖርም የደች ቋንቋ (ፍሌሚሽ)፣ ከፍሬንች ጎን ለጎን እኩል ቦታ ተሰጥቶታል፣ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ካየን ደግሞ ቋንቋዎቻችን እንደብዛታቸዉ መታቀፍ አለባቸው።
አማርኛ lingua franca ሆኖ መቀጠሉ ባይቀርም።

ቋንቋ ጠፋ ማለት ስልጣኔ፣ ባህል፣ እዉቀት፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ የፈጠራ ምዕናብ፣ ጠፋ ማለት ነው። ቋንቋ ሰዎች የሚያስቡበትን አካባቢያቸዉን የሚረዱበትን ነገሮችን የሚጋፈጡበትንና የመሳሰሉትን ነገሮች እንደሚወስን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ አማርኛ ብቸኛ ቋንቋ አድርጎ ጥቅም ላይ ማዋል በጣም ሐገሩን የማይቀበልና የማይረዳ ሕብረተሰብ ይፈጥራል።

በደርግ ጊዜ መቻል የሚባለዉ የመከላከላከያ እግርኳስ ክለብ ከሌሎች ጋር ሲጫወት የአዲስአበባ ሕዝብ ጦሩን ወደኦሮሞ ያጋደለ አድርጎ ስለሚያስብ ተቃራኒ ሆነዉ የሚጫወቱ ክለቦችን ይደግፍ ነበር፣ ይሄ ጤናማ ነገር አይደለም። አርከበ እቁባይ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ለዉጥ ቢያመጣም ኢህአዴግ የብሔር ብሔረሰቦች ወገን የሆነ ለአማርኛ ተናጋሪዉ ነዋሪም ባዕድ ተደርጎ ስለሚቆጠር አንድም ድምጽ ማግኘት አልቻለም።

በነገራችን ላይ አሁን በትግራይ ጦርነት ምክንያት በአዲስ አበባ አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ የትግራይ ቤተሰቦች የወለዷቸዉ ሰዎች ከፍተኛ ቀዉስ ዉስጥ ገብተዋል። ትግርኛ የማይችሉ የትግራይ ደም አለባችሁ ተብለዉ በየማጎሪያዉ የታሰሩ፣ ቋንቋቸዉን ባለማወቃቸዉ ከፍተኛ ቁጭት ዉስጥ የገቡ አሉ። በስነልቦና ከሕዝባቸዉ በመነጠላቸዉ ዘመዶቻቸዉን ሲያሳድዱ የነበሩም አሉ። አሁን ሕዝብን በስመ ከተሜነት ቋንቋዉን እንዳይማር የሚያደርግ አደገኛ ሥርዓት መቀጠል እንደሌለበት ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ሐገር ነች፣ ቋንቋዎቿም ብዙ ናቸዉ።

ተጨማሪ የጋራ መግባቢያ መኖሩን በስምምነት ከሆነ ባልቃወምም፣ የራስን ቋንቋ ልጆችን ማስተማር በጣም ወሳኝ ነው። የተለያዬ ብሔር የሆኑ ወላጆችም ልጆቹ ሁለቱንም ዘመዶቻቸዉን እንዲወዱ፣ ከተቻለ ሁለቱንም ካልሆነ የአንዱን ቋንቋ እንዲለምዱ ማድረግ ያለባቸዉ ይመስለኛል። መንግስት በትምህርት ቤቶቹ ይህንን አቅጣጫ እንዲከተል ከማድረግ አልፎ በየግል ትምህርት ቤቶችም በመላዉ ኢትዮጵያ አስገዳጅ አሰራር መዘርጋት አለበት። ኢትዮጵያ የሚባል ብሔር የለም።

ይሄን ስል ሰዎችን ለመለያዬት ሳይሆን በሐገሪቷ ያለዉን ብዝሐነት በተሻለ ሁኔታ ለማስተናገድ ነው። በቤልጅየሟ ብራሰልስ የሐይማኖት ተቋማት እንኳን ብዙ ቋንቋዎችን ይጠቀማሉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

Ethiopia #southethiopia #Amhara #oromo #Tigray

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ

R