የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የለውጥ አቀንቃኝ ከፍተኛ ባለስልጣናትና አስተባባሪዎች ስለሰሞኑ ሹምሽረት ምን አሉ?

በክልሉ የለውጥ አቀንቃኝ ከፍተኛ ባለስልጣናትና አስተባባሪዎች ከቀናት በፊት የተካሄደውን የአመራሮቹ ሹምትና ሽረት እንዲሁም በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ባደረሱት አጭር ማብራሪያ “የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት አመራሮች የገለልተኝነት ጥያቄ ዉስጥ ያስገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአስተባባሪ ኮሚቴ ሹም ሽረት” በሚል አካሄዱን ገልጸዋል።
“በፓርቲው 2ኛ ጉባኤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ብሆንም በጉባኤው ማግስት በተደረገው በክልሉ የአስተባባሪ ኮሚቴ መልሶ ማደራጀቱ የሚያሳየዉ ልክ አለመሆኑን መሆኑን በግላጭ ያሳዬ ተግባር ሆኗል” ብለዋል።
አክለውም በክልሉ የለውጥ አቀንቃኝ አስተባባሪዎች “የፌደራል የፓርቲዉ ማዕከል በክልሉ ለታዩት ብልሽቶች ዋናው ባለቤት በሆኑ አመራሮች በጎ ፍቃድ እንድደራጅ የተደረገዉ የአስተባባሪ ኮሚቴ መልሶ ማደራጀት ሂደት የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት ገለልተኝነት ጥያቄ ዉስጥ ያስገባ ተግባር ሆኖ ታይቷል” በሚል ቅሬታ አሰምተዋል፡፡
“የብልፅግና ፓርቲ መላ ኢትዮጵያዊያንን በእኩል ዓይን የሚያይና የሚዳኝ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ነጻነት የሚረጋገጥበት፣ እውነተኛ ህብረ-ብሔራዊነት የሚረጋገጥበት፣ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት ዋነኛ ትልሙ እንደሆነ የሚታመን ነው” ብለዋል።
“ሆኖም ከዚህ በተቃራኒዉ የደቡብ ኢት/ያ ክልል ህዝቦች ጩሄት ሰሚ ልያገኝ ባለመቻሉ ህዝቡ ወደ አመጽ እንድገባ እያስገደደ ይገኛል፤ የደቡብ ኢት/ያ ክልል በአገራችን ኢትዮጵያ የተለየች የአስተዳደር ክዋኔ ህደቶች የሚፈፀምባት በሚገርምና በምያሳዝን ሁኔታ ፈራጅም ገዳይም አንድ ሰዉ የሆነበት ክልል አድርጓታል” በሚል ሁኔታውን አስረድተዋል።
“የክስተቱ ጠያቂ እና ተጠያቂ የማይለይበት ለያዥ ገናዥም የድርግቱ ክዋኔ አፈፃፀም ግራ የሆነበት፣ ኋላና ፍቱ የታጣበት መሆኑ የክልሉ ህዝብም ይሁን የፖለቲካ ኤሊቶቹን ወደት እየሄድን ነዉ ያስባለ ከእዉነት ከሆነ መንግስት ከወከለዉ ህዝብ ይልቅ በመንግስት የተወከለዉ አንድ ግለሰብ ብቻ የሚደመጥበትና የሚሰማበት መሆኑ አግራሞት ፈጥሯል” ብለዋል።
“ለማሳያነት በፓርቲዉ ም/ፕረዝዳንት በአቶ አደም ፋራ መሪነት ለአራት የግምገማ ቀናት ቆይታ የክልሉ የፊት አመራሮች ብልሽቶች ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ በዋናነት ቡድንትኝነት፤ ምስጥር ማባከን፤ ሴረኝነት፤ ቅመኝነት፤ አግላይነት፤ ሰሴኝነት፤ ሌብነት፤ አድሎኝነት፤ የየአካባቢ ገዥ መሆን የሚሉ የተረጋገጠ ብሆንም የችግሩ ባለቤት የሆኑት ርዕሰ መስተዳድሩ ሌሎቹን እንድያባርርና አዲሱን ለራሳቸው በሚመች መልክ እንድያደራጁ መፈቀዱ ክልሉ በችግር ዉስጥ እንድኖርና ልማት እንዳይሰራ የፌደራል መንግስትም ጭምር እንድንጠረጥር የሚያደርግ ነዉ” ሲሉ አስተባባሪዎቹ ቅሬታ ገልጸዋል።
“ከምንም በላይ እጅግ በጣም የሚያሳዝነዉ ርዕሰ መስተዳድረሩ በክልሉ ላይ የታዩትን ብልሽቶችን ራሳቸዉንም ሆነ ክልሉን ልፈዉስ በሚችል መልኩ ዉስጣዊ አድርጎ ከመቀበልና ለቀጣይ ፈጥኖ ለመዉጣት በሚያስተምር መልኩ ያለመቀበሉ ስሆን ይሄም ርዕሰ መስተዳድሩ ምን ያክል ፓርቲዉንና ህዝቡን ለመነጠል በዕዉቀት ከዉስጥ ሆኖ እየሰሩ እንደቆዩ በግላጭ ያረጋገጠ ነበር” ብለዋል፡፡
“በአጠቃላይ የፓርቲዉ ዋና ጽ/ቤት አመራሮች በገለልተኝነትና ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ ክልሉንና ፓርቲዉን የሚያሻግር፤ ህዝቡን እርስበርስ በማባላት ለመኖር የሚፈልጉ የየአካባቢዉ ገዥዎች፤ ከፋፋይ ተግባራቸዉን በሚዲያ በመቀባት የስልጣን ጊዜያቸዉን በማራዘም ህዝቡንና ፓርቲዉን ለመነጠል የሚሰሩ ስዉር እጆችን፤ በመድረክ በፓርቲዉ ስም የሚተዉኑና የሚገዝቱ ከመድረክ ጀርባ ሆኖ ደግሞ የሴራ ንጉሰ ነገስቶችን በአግባቡ ለይቶ እርምጃ ይወስዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪዎቹ በአድሱ ሹመት የታዩት ችግሮች ሲጠቅሱ፡- “በክልሉ በታዩ በርካታ ብልሽቶች የርዕሰ መስተዳድሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑ እየታወቀ ተጠያቂ ያለመሆኑ፣ ችግሩ የበለጠ እንድባባስ ያደረገዉ የፓርቲዉ ቅ/ጽ/ቤት ሃላፊ አፌ-ጉባኤ መደረጉ ለህዝብ ም/ቤት ያለዉን ክብር የሚያሳንስ መሆኑ፣ በሥነ-ምግባር ጭምር የተገመገመ የፓርቲዉ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ የነበሩት የፓብልክ ሰርቭስ ሃላፊ ተደርጎ መሾሙ በክልሉ ብዙ ሪፎርም ሥራዎች የሚጠበቅበት ተቋም የተሰጠዉ ትኩረት አናሳ መሆኑን” አብራርተዋል።
በተጨማሪም “ሰራተኛዉ ደመወዝ እንኳን በአግባቡ ሳያገኙ በክልሉ ህግ ተጠሶ እንዳሻቸዉ ሀብት እንድያባክኑ ዋና አመቻች የነበሩትን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩትን ወደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ በማሳደግ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባል መደረጉ በክልሉ ብልሹ አሰራሮች ተጠናክረዉ እንድቀጥል የሚፈቅድ መሆኑ በተጨባጭ መረጃ የተደገፉ የድንጋይ ከሰል ምዝበራ ያካሄዱ የዉሃ ቢሮ ሃላፊ በቦታዉ እንድቀጥል መደረጉን” ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባሻገር “ጠንካራ የነበሩ የክልሉ አፌ-ጉባኤ ያለምንም ጥፋትና ሥነ-ልቦና ዝግጅት ሳያደርጉ እንድነሱ መደረጉ፣ በጂንካ ክላስተር አስተባባሪ እንዳይኖር የተደረገበትና በተጨማርም በጂንካ ማዕከል የነበሩ ብሮዎችን ለመቀነስ እየተደረገ ያለዉ ሴራ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንድደረግ” ብለዋል።
በመጨረሻም እነዚህ የለውጥ አቀንቃኝ ከፍተኛ ባለስልጣናትና አስተባባሪዎች ለውጥ ተከትሎ የተካሄደውን የአመራሮቹ ሹምትና ሽረት እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ባደረሱት በዚሁ አጭር ማብራሪያ “የፓርቲዉ ዋና ጽ/ቤት ከህዝብ በላይ ግለሰብን በመርህ አልባ ግንኙነት ከመወገን ገለልተኛ ሆኖ በክልሉ ሁሉንም ሕዝቦች እንደ ልጁ የሚመለከትና በአፍ የሚያወራዉን የሚፈጽም አስመሳይ፤ እልሄኛ፤ ቅመኛ፤ ቡድንተኛ ያልሆነ አባት መሪ የሚያስፈልግ መሆኑን በማመን ክልሉን ለዳግም ቀዉስ ዉስጥ በማያስገባ ሁኔታ የአመራር መልሶ የማደራጀት ሥራና በአድስ ለሚደራጁትም ግልፅ ኦሪዬንተሸን የሚሰጥበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት ለመጠቆም እንወዳለን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በቅርቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የገዥው ፓርቲ ም/ፕረዝዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አደም ፋራህ በተገኙበት በዎላይታ ሶዶ በተካሄደው መድረክ ላይ በአብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች በዋናነት ስር በሰደደው ሙስና፣ ስነምግባር ጉድለት፣ አድሏዊነት፣ ብልሹ አሰራር፣ በመፍትሔ አቅጣጫ ዙሪያ እንዲሁም የመንግስት አሰራር ሆነ የገዥው ፓርቲ ተግባርና ስልጣን በግለሰቦች እጅ በመውደቁ ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይጥል እንቅፋት ሆኗል” በሚል ተገምግሞ የተነሱ ተጨባጭ መረጃዎችን በመውሰድ አስቸኳይ እርምት እርምጃ የሚያስፈልገው በመሆኑ በቦታው ምንም ውሳኔ ሳይሰጡ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመለሳቸውና የእርምት እርምጃ እየተጠበቀ ስለመሆኑ መዘገባችንም ይታወሳል።
በዚሁ መነሻ ከቀናት በፊት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ “የመንግስት አሰራር ሆነ የገዥው ፓርቲ ተግባርና ህግ በመጣስ በየአካባቢው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ እንዳይሰጥና ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይጥል እንቅፋት ፈጥሯል” በሚል የተገመገሙ አመራሮች ሹም ሽረት ማካሄዱ ይታወሳል።
በተለይም ክልሉን በተመለከተ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እውነትንና ተጨባጭ መረጃዎችን መነሻ አድረጎ በተደጋጋሚ በሰራው ዘገባ መሠረት በክልሉ ሁለት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮች ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነስተው ሌሎች በቦታው የተተኩ ቢሆንም ተጨባጭ ህገወጥ ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ አመራሮች ሾልኮ መቅረታቸውን ለመታዘብ ችለናል።
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የደቡብ ኢትዮጵያ የአመራር ብልሽት በተመለከተ በከበሩ ማዕድናት፤ በኮንትሮባንድ፤ በከተማና በገጠር በኢንቨስትሜንት መሬቶች እንደሆኑ በመረጃ አስደግፈን ለሕዝብ ይፋ ማድረጋችን የሚታወቅ ሲሆን የተወሰኑ በዚሁ ብልሹ አሰራር የተዘፈቁ አመራሮች ከኃላፊነታቸው የተነሱ ቢሆንም አብዛኞቹ ለጊዜው ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ በስልጣን እንዲቀጥሉ መደረጉን በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል።
በመሆኑም “ክልሉ የገዥው ፓርቲው በይፋ ባረጋገጠው መሠረት “የመንግስት አሰራር ሆነ የገዥው ፓርቲ ተግባርና ህግ በመጣስ በየአካባቢው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ እንዳይሰጥና ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይጥል እንቅፋት ፈጥሯል” በሚል የተገመገሙ አመራሮች ሹም ሽረት አካሄድ ለህብረተሰቡ ዘላቂ ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ ሲባል ዳግም ሊያጤናውና ሊፈትሸው የሚገባ እንደሆነ ያስረዳል” በሚል የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት መዘገባችን ይታወሳል።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
Ethiopia #southethiopia
ደቡብ ኢትዮ