የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር ከምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር ለጋዜጠኞች ስለምርጫ አዘጋገብ ላይ ስልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር አዘጋጅነት ለ2 ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ ስልጠና ጋዜጠኞች በምርጫ ወቅት መረጃ ለህዝብ በሚያደርሱበት ጊዜ ስለ ምርጫ ስለሚኖራቸው የተሻለ ግንዛቤ ያተኮረ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ አሁን አሁን እየተባባሰ የመጣውን የጥላቻ ንግግር በማስወግድና ሀቅን በማንጠር ጋዜጠኞች ለዜጎች ትክክለኛ መረጃ ማድረስ እንደሚገባቸው በመድረኩ ተነስቷል።
የማህበሩ ፕሬዜዳንት ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት በምርጫ ወቅት ብዙ አጀንዳዎች ወደ ህዝቡ ይቀርባሉ ፤ የሚቀርቡት አጀንዳዎች በመንግስት አካላትም ሆበ በተቃዋሚ ጎራ ሊሆን ይችላል መረጃውን የሚያቀርቡት ጋዜጠኞች እራሳቸውን ከዜናው ውስጥ በማውጣት ሁሉንም ባማከለ መልኩ መረጃዎችን በማመዛዘን ማቅረብ አለባቸው ብለዋል።
ጋዜጠኛ ኤልያስ ፥ “ለአንድ ጋዜጠኛ ትልቁ አለቃው ኤዲተሩ ወይም የሚሰራበት ሚዲያ ባለቤት አይደለም፤ እውነት ነው መሆን ያለበት በተለይ እንደምርጫ ባለ ጉዳይ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭቱ ፣ የጥላቻ ንግግሩ የተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎች የሚንፀባረቁበት ነው አሁንም እያየን ነው ያለነው ፥ ስለዚህ ከፍተኛ የፕሮፌሽናሊስም ስታንዳርድ ጋዜጠኞች መከተል አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለው ፥ ጋዜጠኞች የራሳቸውን አስተያየት፣ የሚደግፉት የሚከተሉት አቋም ሊኖር ቢችልም ነገር ግን ከዛ ውስጥ እራሳቸውን አውጥተው በማሰብ ሁሉንም ባማከለ መንገድ ፣ በገለልተኝነት ዜናዎችን መስራት አለባቸው ብሏል ስል ዳጉ ዘግቧል።