በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ
የቀጠለው ብርሃን ባንክ በዎላይታ ሶዶ ግንባታ ውዝግብ፡ የአከባቢው ደንበኞች ቅሬታ
በትናንትናው ዕለት በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የቀረበውን የብርሃን ባንክ ግንባታ ውዝግብ ተከትሎ ዛሬም ተጨማሪ መረጃዎች ይፋ ሆነዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ሶዶ ከተማ የብርሃን ባንክ ደረጃውን የጠበቀ ህንፃ ለመገንባት 5,000 ካሬ ሜትር መሬት ተረክቦ እንደነበር ይታወሳል።
ይሁን እንጂ፣ ባንኩ “በአዲስ አበባ ግንባታ ስለምንጀምር አሁን አንችልም” በሚል ምክንያት ግንባታውን በማዘግየቱ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ ተመልሷል።
ይህ ውሳኔ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን የፈጠረ ሲሆን፣ “በአዲስ አበባ ምንም ዓይነት የብርሃን ባንክ ሕንፃ ግንባታ እንደማይካሄድ መረጃዎች ያሳያሉ” የሚሉ ወገኖችም አሉ። በዚህም ምክንያት የአካባቢውን ልማት ለማደናቀፍ ከውስጥና ከውጭ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ጥርጣሬዎች እየተስተጋቡ ይገኛል።
ባንኩ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብርሃም አላሮ አነሳሽነት መሬቱን ተረክቦ በዓመት ውስጥ ዲዛይን አዘጋጅቶ በጉታራ በተዘጋጀው አውደ ርዕይ ላይ ለህዝብ ትችት አቅርበው እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ይህ በክልሉ ታይቶ የማይታወቅ ሂደት ነበር። የዲዛይን አሸናፊው ከተለየ በኋላ የግንባታ ጨረታ ወጥቶ የመጀመሪያው ጨረታ ሳይሳካ ቀረ። በሁለተኛው ዙር አሸናፊው ተለይቶ ግንባታው ሊጀመር ሲል የዎላይታ ሶዶ ከተማ ሌዊ-ግብርና ኮሌጅ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሊጀመር እንደሆነ ተገልጿል።
ባንኩ የመንገዱን ቁፋሮ ውጤት ጠብቆ የግንባታውን ደረጃ ለማወቅ ሲጠብቅ የዞኑ አስተዳዳሪ ባንኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን ካልጀመረ መሬቱን እንዲያስረክብ ደብዳቤ ልኮ ነበር።
የመረጃ ምንጫችን “ባንኩ በምላሹ የመንገዱ ቁፋሮ እንደተጀመረ ደረጃውን አውቆ ግንባታውን እንደሚጀምርና እስከ ታህሳስ ወር እንዲጠበቅ ጠይቆ በዚህ መሃል ቀደም ሲል መሬቱን ይዞ ለአምስት ዓመታት ቁጭ በማድረጉ የተነጠቀው አካል መሬቱ በህገወጥ መንገድ ለባንኩ ተሰጥቷል ሲል የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ መጀመሩን ያስታውሳል።
በዚህ የተበሳጨው የባንኩ አመራር የዞኑ አስተዳደር ባንኩን ከማገዝ ይልቅ እንቅፋት እየፈጠረ ነው በማለት 3 ሚሊዮን ብር ከፍሎ የተረከበውን እና ለዲዛይን ስራ 10 ሚሊዮን ብር የወጣበትን 800 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት መሰረዙን ከባንኩ ውስጥ አዋቂዎች ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጠቁመዋል።
የነዋሪዎች ጥያቄዎችና ተጨማሪ ጥርጣሬዎች
የአካባቢው ነዋሪዎች የዞኑ አስተዳደር ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ይልቅ ያለውን ኢንቨስትመንት እንዴት እንደሚያደናቅፍ ሊጣራ ይገባል ይላሉ።
በዎላይታ ሶዶ ከተማ የቴሌ እና የብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ከ15 ዓመት በላይ ቦታ ይዘው የቆዩ አካላት ለምን እንዳልተጠየቁ፣ ከዳሽን ባንክ ውጪ ሌሎች የግል ባንኮች በሶዶ ህንፃ ሳይሰሩ ብርሃን ባንክ እንዲሰራ የግል ሎቢ የተደረገው ለምን መሬት በልዩነት ይቀማል?” የሚል ጥያቄዎች ተነስተዋል።
በተጨማሪም “ብርሃን ባንክን ጨምሮ ሰባት የሚሆኑ ባንኮች በውህደት ስጋት ላይ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ባንኩ ፕሮጀክቱን ለመሰረዝ የወሰነበትን ምክንያት ለባለአክሲዮኖቹ እና በዎላይታ ለሚገኙ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ደንበኞች ግልጽ ማድረግ እንዳለበትም ተጠይቆ በሶዶ የሚገኘውን የዲስትሪክት ቢሮ ወደ ሌላ ቦታ ያዛወረው ለምን እንደሆነ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል” ተብሏል።
ይህ ሁኔታ ለተፈጠረው ውዝግብ ተጨማሪ ጥርጣሬን ያሳደረ ሲሆን የዎላይታ ሶዶ ነዋሪዎች ባንኩ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ግልጽነት እንዲያሳይ እና የዞኑ አስተዳደርም ተገቢውን ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏