በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን ለጥቂት ጊዜ ጋብ ብሎ የነበረው በማህበራዊ ሚዲያ ሀሳባቸውን የሚገልጹ ወጣቶችና የመብት ተሟጋቾችን ማሰርና መደብደብ ሁኔታ ማገርሸቱ ተገልጿል።
ከትናንት ጀምሮ በዞኑ በሶዶ ከተማ እና ሌሎች መዋቅሮች የታሰሩት በዞኑ እና በአከባቢያቸው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ሌሎች ችግሮችን ባመኑበት ሀሳብ በማህበራዊ ሚዲያ ይገልፃሉ የተባሉትን እንደሆነ ተነግሯል።
ቤተሰቦቻቸው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደገለፁት፦ እነዚህ የታሰሩ ወጣቶች “እስከአሁን ድረስ የተጠረጠሩበት የወንጀል መረጃ ማስረጃ እና ከሳሽ በለሌበት በፖለቲካ አመራር ትዕዛዝ ብቻ ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ተነፍገው ህገመንግስት ያጎናጸፈው መብት በሚፃረር መልኩ ፖሊስ ማሳሰሩን ገልጸዋል።
አሁን ያለው አዝማሚያና መረጃዎች እንደሚጠቀሙ በዎላይታ ዞን በአከባቢው የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መናገር፣ መንግስታዊ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ማጋለጥ እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የተለያዩ የህዝብ ችግሮቹን ይፋ ለማድረግ የሚሞክሩ ወጣቶች ያለምንም ህጋዊ መጥሪያና አሰራር እየታሰሩ ይገኛሉ።
በተለይም አንድ በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የተግባቦትና ጋዜጠኝነት መምህር በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው “ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሌለበት አስገድደው የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውን እንዲከተሉ በማድረግ የግለሰቦችን ድምፅ ለማፈን የሚደረግ አዝማሚያ የመብት ጥሰት ከመሆኑ ባሻገር በአከባቢው መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍንና ብልሹ አሰራር እንዲሰፍን ያደርጋል” ብለዋል።
የዎላይታ ዞን ከየትኛውም አከባቢ በላይ ሚዲያዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እንዲሁም ወጣቶች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብት ተጠቅመው በአከባቢው የሚስተዋሉ መንግስታዊ አሰራርና ብልሽት ላይ በሰላማዊ መንገድ ትችት በሚያደርጉበት ወቅት በህገወጥ መንገድ በማፈን፣ በማሰር፣ ያለጥፋታቸው ፍርድቤት እንዲመላለሱ በማድረግ እንዲሁም በስደት ከአከባቢው እንዲሸሹ የሚያስገድድ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለፃችን ይታወሳል።
አንድ ለመረጃው ቅርበት ያለው ግለሰብ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደጠቆመው የእስር ዘመቻው የተጀመረው የዎላይታ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጴጥሮስ ወልደማርያም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማዕድን ምዝበራና የአሰራር ጥሰት በተመለከተ የሀገሪቱ የመንግስት ሚዲያ የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “የማዕድን ስር ቁማርተኞች” በሚል ርዕስ በሰራው ዘገባ ላይ “እኛ እንዴት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን በደብዳቤ እንጠይቃለን ?” “እኛ አሁን በአፍ Communicate እየተደራረግን ነው” በማለት የሰጡት ሀሳብ የሕዝብ ጥቅም የሚጎዳ አስተያየት የተቹትን ሲሆን ሌሎችንም ለመያዝ ክትትል ላይ ነው” ብለዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዎላይታ ዞን በየመዋቅሩ በማህበራዊ ሚዲያ በአከባቢው የሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ሀሳባቸውን በልዩነት የሚገልጹ ወጣቶችንና የመብት ተሟጋቾችን ለእስርና ድብደባ መዳረግ ለጥቂት ጊዜ ጋብ ያለ ቢመስልም አሁን ላይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መልሶ አገርሽቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏