
|| በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና (የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ)
በግሌ የታሪክ ምሁር ባልሆንም፣ በተቻለኝ መጠን የዎላይታን ታሪክ ለማንበብ እተጋለሁ። በዚህ ንባቤ አንድ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር በሚኒሊክ ወረራ እና የዎላይታ መንግስት መፍረስ በኃላ ዎላይታ ለከፍተኛ ማህበራዊ ቀዉስ ተጋልጣለች። ይህ ማህበራዊ ቀዉስ በጉልህ ከሚታይባቸው ነገሮች ግምባር ቀደሙ ቤተሰብ ነው።
በነገራችን ላይ የዎላይታ oral history ዉስጥ አንድ በጉልህ የሚነገር ፣እሱም በሕዝባዊ የታሪክ አረዳድ ደረጃ ሊገለጽ የሚችል ነገር አለ።
ሰባት ጊዜ የሚኒሊክን ጦር በቀጥታ ተዋግቶ ያሸነፈዉ፣ የዎላይታ ጦር በሰባተኛውን ጦርነት ተዋግቶ ተሸንፏል ተብሎ አይታመንም በሕዝቡ ዘንድ። ዎዚቶ ዎቢሎ እና ሎሚና አዳሬ ሕዝባዊ ሚስጢራችንን፣ ለጠላት ሰጥተዉ አስጠቁን፣ ለዉድቀት ዳረጉን ነዉ ተብሎ የሚታመነዉ። ሚስጢሩም፣ ጥቃቱም ቤተሰብ ላይ ያነጣጠረ ነበረ። ለሚኒሊክ የተነገረዉ ሚስጥርም “ዎላይታን በቀጥተኛ ጦርነት መቼም ማሸነፍ አትችልም !
ነገር ግን ቤተሰባቸዉን ማለትም ሚስትና ልጆቻቸዉን በጣም ስለሚወዱ፣ አንተን ለመግጠም ግምባር ሲመጡ ሌላ ኃይል ከጀርባ ላክና ቤቶቻቸዉ በእሳት እንዲነድ አድርግ። ያኔ ሚስቶቻችን እና ልጆቻችን አለቁ ብለዉ ይመለሳሉ፣ ያኔ ከሁዋላ ተከታትለህ አጥቃ።” ብለዉታል።
ዎላይታዎች አንድ አባባል አላቸዉ ፓስ ( መጥረቢያ ) ብረቱን ለሥራ አያያዝ እንዲያመች የሚያደርግ ቁልምም እንጨት ወይንም በዎላይትኛ ቱቲያ የሚባል አለ። እና ዛፎች” wonikka nuna wursiyage nuso geella “ማለትም “ድሮም እኛን የሚያስጨርሰን፣ የኛዉ ቤት ጠማማ ነው” አሉ ይባላል። እናም ዎላይታ በራሱ ሰዎች በባከነ ሚስጢር ለዉድቀት ተዳረገ።
ወደ ጉዳያችን ስንመለስ በወቅቱ የነበሩ ዎላይታዎች ቤተሰባቸዉን የሚወዱ፣ ለቤተሰቦቻቸዉ የሚሳሱ እንደነበሩም ያሳያል ታሪኩ። እንደዘመኑ የስልጣኔ ሁኔታ በዛን ወቅት ከነበሩ ባህሎች ዉስጥ ለአሁኑ የሰለጠነ ዘመን የማይሆኑ ነገሮችም እንደሚኖሩም መካድ የሚቻል አይመስለኝም።
እንግዲህ ይህ ሕዝብ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በቀጠለዉ ማህበራዊ ቀዉስ፣ ዛሬ ላይ የዎላይታ ሕጻናት የኢትዮጵያን ከተሞች ጎዳናዎችን ሞልተዋል። የማህበረሰቡ ቤተሰብን የመዉደድ እሴት ዛሬም ያለ ቢሆንም፣ በዋናነት በግልጽና ስዉር ብሔራዊ ጭቆናዎች ምክንያት የተጫነዉ ድህነት በዎላይታ ቤተሰብ የተባለን ተቋም በእጅጉ እየተፈታተነዉ ነው።
ለማመን በሚቸግር መልኩ ከዎላይታ በድህነት ምክንያት፣ ትምህርት በመማሪያ እድሚያቸዉ ወደ ኢትዮጵያ ከተሞች በገፍ ይፈልሳሉ ሕጻናት።
በቅርቡ እንኳን ለአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ተብሎ በየጎዳናው የነበሩ16ሺ ሕጻናት ከአዲስ አበባ ታፍሰዉ ማጎሪያ ዉስጥ እንዲቆዩ ሲደረግ ከነዛም ወደ 5ሺ ገደማ የሚሆኑት የዎላይታ ልጆች ወሆናቸዉን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል። በዎላይታ የሚዋደደዉን ቤተሰብ ድህነት እየበተነ ነው ለሚለዉ አንድ ማሳያ ነው።
ሌላዉ አሁን አሁን በዎላይታ እየተስፋፋ መጥቶ፣ የተንሰራፋዉ፣ የቤተሰብ በታኝ ቀዉስ “madamii so” ወይንም “የማዳም ቤት” ይባላል። ይህም በዋናነት ወጣት ሴቶችን ለቤት ሰራተኝነት እና ሌሎች መሰል ሥራዎች ወደ አረብ ሐገራት መላክ ነው። ይህ በዎላይታ በአሁኑ ሰዓት እጅግ ብዙ ማህበራዊ ቀዉስ እየፈጠረ ነው። ያገቡ ሴቶች ኑሮን ለማሸነፍ ትዳራቸዉን ጥለዉ በሰዉ ሐገር እየኖሩ ነው፣ ያላገቡ ሴቶች ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ እና በመሳሰሉት መንገዶች በሚያፈራቸዉ የርቀት “ወዳጆች” እየተጭበረበሩ ነው።
በአካባቢው ምቹ የሥራ እድል ቢፈጠርላቸዉ ግን እህቶቻችን በዚህ ደረጃ ለችግር ባልተጋለጡ ነበረ። ታዲያ ስደት በደፈናዉ መጥፎ ገጽታ ብቻ አለዉ እያልኩ አለመሆኔም ይሰመርበት።
በዎላይታ ካለዉ የሰዉ ኃይል ብዛት እና ከተማረ ሰዉ ብዛት አንጻር የኢትዮጲያ መንግስት ለአካባቢው መስጠት የሚገባውን ትኩረት ካለመስጠቱ ፤በተጨማሪም ግልጽና ስዉር የብሔራዊ ጭቆና ስልቶችን ነድፎ ለዘመናት በመንቀሳቀሱ ችግሩ እየተባባሰ ነው።
በቅርቡ ሕዝቡ የእንዱስትሪ ዞኖች ይከፈቱልን ብሎ ሲጠይቅ፣ በቀጥታ “አልከፍትም” በሚል የአስፈጻሚዉ አካል ቁንጮ መልስ መስጠቱ ይታወሳል። ሚዛናዊ ዉክልና መንፈግ፣ መሰረተልማት መከልከል ተቋማትን ማሸሽ ወቅታዊ ፈተና ናቸዉ። የዎላይታ የፖለቲካ ኃይሎች መሰል የብሔር ጭቆናዎችን ለመቀልበስ በጥናት ላይ ተመስርተዉ አቅደዉ ከሌሎች strategic አጋር ኃይሎች ጋር ተቀናጅተዉ መሥራት ይጠበቅባቿል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሳይረፍድ መፍትሔ ቢፈልጉ ጥሩ ነው። ትናንት ጦር ተልኮ የዎላይታን ቤተሰብ አጠቃ የሕዝቡን ሕይወት አመሰቃቀለ፣ ዛሬስ ምን እየተላከብን ነው ከጀርባ የሚለዉ ሁሉም በየፈርጁ ሊያጠናዉና ሊያስብበት የሚገባ ነገር ነው። በተለይ በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙ የብሔር ጭቆናዎች በቂ ትኩረት ተሰጥቷቸዉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠባሳ ዛሬ ላይ እንዳያሳድሩ ካልተደረገ መልሱ ሙሉ አይሆንም።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏