1000045744

በትግራይ የፈነጠቀዉ የዴሞክራሲ ጮራ… ለኢትዮጵያ የመከራ ጊዜ የሚያራዝሙ መቼ በቃኝ ይላሉ ? ሽማግሌዎቹ በሻዕቢያ ተላላኪነትና በፌደራል መንግስት ተላላኪነት የሚካሰሱበት እንዴት ይቆማል ? ትግራይ ከተቀረዉ ኢትዮጵያ ቀድማ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ታካሂድ ይሆን? ተስፋና ስጋቶች፣ ፈተናና እድሎች ዙሪያ የተዘጋጀ የፖለቲካ ወጌሻ መደበኛ ዝግጅት 👇

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተዘጋጀ

ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በሁዋላ፣ አተገባበሩ ከመዘግየቱ ጋር ተያይዞ፣ በትግራይ ክልል ያለዉን የፖለቲካ ኃይሎች የሐሳብ ልዩነት እና የሚታዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እንዴት ይገመግማሉ ? ከተቀረዉ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የክልሉ የፖለቲካ ምህዳር እንዴት ተለያዬ? የክልሉ ሚዲያዎችን እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ? በነዚህ ጉዳዮች ላይ አስተያዬት ቢሰጡን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በእኔ አስተያዬት የልዩነቶቹን መነሻ ለመረዳት ቢያንስ ወደ ጦርነቱ መነሻ መመለስ አለብን። በወቅቱ በትግራይ ቀድሞ አንጃ ተብለው በሕንፍሽፍሽ ጊዜ ከተለዩ ሰዎችም የተወሰኑት ወደ ሕወሓት ተጠግተው ነበር። የሕወሓት ነባሩም ሆነ ወጣት አመራር በጋራ መቐለ የነበሩበት ሁኔታ ነበር።

የሚዲያ ጦርነቱ በትግራይ በኩል በድምጺ ዎያኔ እና በትግራይ ቴሌቪዥን እንዲሁም በአክቲቪስቶች በማህበራዊ ሚዲያ ሲመራ የፈደራል መንግሥት ከብሔራዊ ጣቢያዎች እስከ አማራ ክልል እንዲሁም በዉጪ የሚገኙ መንግስት የሚደጉማቸዉ ሚዲያዎች ና አክቲቢስቶች ይመሩት ነበር ከጦርነቱ በፊት።

ሕወሓት መንግስት ሕገመንግሥት ጥሷል፣ ጦርነት ሊያዉጅብኝ ነው ይላል፣ መንግስት ሕወሓት በየቦታው ግጭት እየጠመቀ ነው ይላል። የብልጽግና ምስረታም ልዩነቶቹን አጦዛቸዉ። በሁለቱም በኩል የጦርነት ዝግጅት ይደረግ ነበር፣ የወታደር ሰልፍም ማየት ተለምዶ ነበር። ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ የሐይማኖት አባቶችና የሐገር ሽማግሌዎች በሄዱ ጊዜ ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልን አንድ እናት ተንበርክካ ስትለምን እሱ “አሁንማ ረፍዷል” ሲል ተደምጧል።

በወቅቱ የሐገር ሽማግሌዎቹም ሕዝቡም በፌደራል መንግስትና አጃቢዎቹ ፕሮፖጋንዳ ተጽዕኖ ስር ስለነበሩ ንግግሩን እንደጥጋበኝነት ብቻ ወሰዱት። ግን ብልጽግናስ በስዉር ምን ቢያደርግ ነው ህወሓት እንዲህ የተማረሩት ብሎ የጠየቀ ሰዉ ብዙ አልነበረም። በኢትዮጵያ Narrative በበላይነት የሚቀምሩ አካላት በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምክንያት ሕዝቡ የፌዴራል መንግስት ሰላም ቢፈልግም፤ ህወሃት እምቢ ያለ እንዲመስለዉ ተደርጓል።

የፌደራል መንግስት ከተቋማት የትግራይ ተወላጆችን አለ አግባብ ሲቀንስ ነበር፣ ለሕገመንግስታዊ መርህ ይቆማሉ በሚል ስጋት ብዙ የዎላይታ ተወላጆችንም ቀንሷል፣ አስቀንሷልም። ሻዕቢያን አቅፎ ትግራይን መግፋት ተለመደ። እነዚህና የመሳሰሉ እርምጃዎች ብዙ አለመግባባቶችን ወለዱ፣ በተቀረዉ ኢትዮጲያ ምርጫ ተዘለለ፣ ትግራይ ምርጫ ተደረገ፣ በጀት ክልከላ መጣ፣ ልዩነቶች ተካረሩ።

በዚህ መሐል ህወሃት የሰሜን እዝን ከጀርባ ወጋ የሚል ተከትሎ መግለጫ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰጠ፣ የወቅቱ የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ማይክ ፖምፒዮ፣ ህወሃት በሰሜን እዝ ላይ እርምጃ መዉሰዱ እንዳሳሰባቸዉ ተናገሩ፣ ህወሃትም መብረቃዊ ጥቃት ፈጽሚያለሁ ብሎ በግልጽ አመነ።

እርምጃዉ Anticipatory self-defense ነው የሚል ነጥብ አከለበት። ይህም ማለት በማያጠራጥር ሁኔታ በተጨባጭ ጦርነት ሊታወጅብኝ እንደነበረ እርግጠኛ ስለሆንኩ ሳይቀድሙን ቀደምኩ እንደማለት ነው።

እኔ በግሌ ይህ የተሳሳተ የፖለቲካ ዉሳኔ ነበር ብዬ አምናለሁ የፌደራል መንግስት ቀድሞ ቢተኩስ አንደኛ ደጋፊዎቹ ትርጉም ባለዉ ሁኔታ ይቀንሳሉ ሁለተኛ የመንግስት ኃይሎችም ዉስጥ ክፍፍል ይፈጠራል፣ ሶስተኛዉ መንግስት ጸረ_ትግራይ ቅስቀሳዉን ያቀጣጠለለትን ነዳጅ አያገኝም ነበር፣ አራተኛ ሌሎች የዉስጥና የዉጭ ኃይሎች ለትግራይ ጆሮ የመንፈጋቸዉ ነገር ይቀንስ ነበር።

ሌላው የፌዴራሉ መንግስት “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ይበል እንጂ የከፈተዉ ጦርነት በዚህ ማዕከፍ ሊታቀፍ የሚችል አልነበረም። ሻዕቢያ አይደለም የኛን ሐገር ሕግ ሊያስከብር እዛ በሐገሩስ መች ሕግ አለዉ? ሲጀመር በኛ ሐገር ጣልቃ እንዲገባ የተደረገዉ በየትኛው የሐገራችን ሕግ መሠረት ነው ? የአማራስ ክልል ሕግ ጥሶ ወደ ትግራይ ዘልቆ የገባው የትኛውን ሕግ ሊያስከብር ነው ? እዚህ ጋር መረዳት ያለብን ዘመቻ አሉላ ከሚባለዉ ጦርነት ጀምር የትግራይ ሕዝብ እራሱን ለመከላከል ወደ ጦርነት በሕዝባዊ መልኩ መግባቱን ነው።

እኔ ጦሩ TDF የተባለዉ በአጠቃላይ ሕዝብ ሕልዉናዉን ለማስጠበቅ በራሱ ተነሳሽነት፣ እንዲሁም በህወሓት ግልጽ መልዕክት ጭምር በመሰባሰቡ ይመስለኛል። ህወሓት የሁኔታዉን ክብደት አይታ “የትግራይ ሕዝብ ሆይ ህወሓት ያድነኛል ብለህ አትጠብቅ እራስህን ተከላከል፣ ጦርነቱ ሕዝባዊ ሆኗል!” የሚል መልዕክቶች አስተላልፉል የሚል ነው።

መንግስት ጦርነቱ ከሕግ ማዕቀፍ ዉጪ እንዲካሄድ በመፍቀዱ፣ የትግራይ መሬት የሚቀራመቱና ሕዝቡን የሚበቀሉ ኃይሎች በመፈጠራቸዉ ሕዝባዊዉ TDF ተፈጥሯል ባይ ነኝ። ሌላዉ መረሳት የሌለበት በሚዲያዎች አኳያ ቅስቀሳዉ የሰሜን እዝ ተጠቃ ከሚለዉ አልፎ 27 ዓመት አመራርነት፣ የ17ዓመት ታጋይነት፣ የቀድሞ የትግራይ ታሪኮችም እንደወንጀል እየተደረጉ ተቀስቅሶባቿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በፓርላማ ስለ ወልቃይት ያደረገዉ ንግግር ይታወሳል ሌላዉ ደግሞ በ siege ወይንም ከበባ ወቅት የደርግ ሽንፈት ከሱዳን ኮሪደር መከፈት ጋር አያይዘዉ መተንተናቸዉ በቴሌቪዥንም ደርግ ወያኔ የወሎና ጎንደርን መሬት ሊወስድ አቅዷል ብሎ የሰራዉ ፕሮግራም ሁላ ተላልፏል። እነዚህ ሁሉ ጦርነቱ ተጀመረ ከተባለዉ አላማ ዉጪ ናቸዉ። ይሄ ሁሉ ጦርነቱ በቀጥታ አለዉ ከተባለዉ አላማ ዉጪ መሆኑ ደግሞ ለጦርነቱ escalation ድርሻ አበርክቷል። እንግዲህ ከብዙ እብደት በሁዋላ የፕሪቶሪያ ስምምነት መጣ።

አቦይ ሰብሐት አንዴ ጦርነቱን አንጃዎቹ ናቸዉ ያስጀመሩን ብለዉ ነበር፤ በቅርቡ ደግሞ በጀነራል ጻድቃን ላይ ያነጣጠሩ ክሶችን ሰንዝረዋል ጀነራል ጻድቃን ደግሞ የአማራ ክልል ግጭት ሲጀመር የፌደራል መንግስቱ ወልቃይትን አስመልሱ ሲል ህወሓት እምቢ ብሏል ሲሉ ነበር። እንግዲህ ያ የድሮዉ ክፍፍል አረና ትግራይንም የወለደ ነው እና የትግራይ የተቃዉሞ ፖለቲከኞች ወደነጌታቸዉ ረዳ ማጋደላቸዉ እንዳለ ሆኖ ይህ የአንጃዉ ዘመን ክፍፍል አሁን ላይ ተጽዕኖዉ ምን ያህል ነው የሚለዉ ሰፊ ጥናት የሚፈልግ ነው።

በዋናነት ግን አሁን የሚታዩት ጎራዎች በጌታቸዉ ረዳ እና በዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩ ናቸዉና በግልጽ የሚታዩ ቡድኖች ላይ አተኩሮ ማዉራቱ አይከፋም። በፕሪቶሪያ ስምምነት ህወሓት እንደፓርቲ፣ TDF እንደ ሰራዊት፣ የግዚያዊ አስተዳደሩ ህወሓት በ 50+1 ባለድርሻነት የሚሳተፍበት ሆኖ ተቋቁመዋል። እንግዲህ የፌደራል መንግስት ስምምነቱን ሳይተገብር መቆዬቱና የምርጫ ቦርድ ተብዬዉ አወዛጋቢ አካሄዶች በትግራይ ኃይሎች መሐከል ያለዉን ልዩነት እየገለጡት መጥተዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትግራይን ለአንጻራዊ ሰላም ባበቃዉ ትግል የተሳተፉት ሁሉም የፖለቲካም ሆነ የሌሎች አደረጃጀቶች እና ሕዝቡ ሁሉ ናቸዉ በሚል አሳታፊ አግባብ በመሄዱ ብዙ የተቃዋሚዎችና ገለልተኛ ምሁራንን እንዲሁም የፖለቲካ ተንታኞችን ቀልብ ስቧል። በተለይ ህወሓት ከእንግዲህ ብቸኛ ወሳኝ ሆኖ መቀጠል የለበትም የሚለዉ በግልጽ ይታያል።

የነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን ደግሞ ትግራይ አንዣቦባት የቀጠለዉን ስጋት ለመመከት፣ በጠንካራ አደረጃጀቱ ህወሓት ነባሩን መዋቅሩን ተጠቅሞ መምራት አለበት ይላል፣ በተለይ የፈደራል መንግስት አጃቢዎች የነ ጌታቸዉ ረዳን ቡድን መደገፋቸዉ፣ የነ ደብረጽዮንን ቡድን በተወሰነ ደረጃ የጠቀመዉ ይመስላል ባላንጣዎቻቸዉን በጥርጣሬ እንዲታዩ ለማድረግ።

በዚህ መሐል ገለልተኛ ሆኖ የቆዬዉ TDF በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ወደ እነ ዶክተር ደብረጽዮን ያጋደለ መግለጫ ማዉጣቱ ዉዝግቡን አንሮ በሁለቱም በኩል የሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ሆኗል። በግሌ ሁለቱም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸዉን ወድጄላቿለሁ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካም አዲስ ምዕራፍ ሊባል ይችላል።

አሁን ላይ ያለዉ ዉዝግብ እንዳለ ሆኖ ከዚህ ዉጥረት ትግራይ እንዴት ትዉጣ የሚለዉ ሁሉም የትግራይ ኃይሎች ሊያስቡበት የሚገባ ነው። አንድ መዘንጋት የሌለብን ሐቅ የፈደራል መንግስት የትግራይን ግዛታዊ አንድነት አለማረጋገጡ እና ወደ ቀጣይ እርምጃዎች እንዳይኬድ እንቅፋት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። በአሁኑ ሰዓት እርግጠኛ መሆን የሚቻለዉ ህወሓት በምርጫ አሸንፎ አልያም ስልጣን ተጋርቶ በትግራይ ፖለቲካ መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑ ባይካድም እንደድሮዉ ግን የትግራይ ፖለቲካ በብቸኝነት ሊቆጣጠረዉ በፍጹም አይችልም።

ያ ሕዝብ ዴሞክራሲ ይገባዋል፣ ዛሬ ያያትን አንጻራዊ ሰላምና ነጻነት ከሞት ጋር ተናንቆ አምጥቷልና። ዳያስፖራውን፣ ምሁሩን፣ ወጣቱን ሚዲያዉን ሁሉ ህወሓት በራሱ ቅርጫት ዉስጥ ከእንግዲህ ጠቅልሎ መክተት አይችልም። ገለልተኛ ሰዎች እንዳሉ ሆነዉ፣ ዛሬ ላይ በትግራይ የሁለቱም ቡድን ደጋፊ ቁጥሩ ቀላል የሚባል አይደለም። በጣም ደግሞ ደስ የሚለዉ ሁሉም በጋራ የፕሪቶሪያ ስምምነት ይተግበር የሚል አቋም አላቸዉ።

በቅንነት በጥበብ እና በአርቆ አሳቢነት እንዲሁም በትግራዋይ ወንድማማችነት መነጽር ነገሮችን ካዩ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሁለቱም የሚስተናገዱበትን መንገድ ማበጀት ይቻላል። በአሁኑ ሰዓት ኤርትራ ዉስጥ ማለት የሚፈቀደዉ ወዲ አፎም ወዲ አፎም፣ ወዲ አፎም በዚህ ገቡ፣ ወዲ አፎም በዚህ ወጡ ነው። ከትግራይ ዉጪ ባለዉ ኢትዮጵያ የሚፈቀደዉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጭነት፣ እሳቸዉ ሐሳብ ባያመነጬ ኖሮ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንሼቲቭ እያሉ መቀባጠር ብቻ ነው። በትግራይ በአሁኑ ሰዓት ጉጅለ ደብረጽዮን፣ ጉጅለ ጌታቸዉ ረዳ እየተባባሉ መሟገት ተለምዷል።

ሰላማዊ ሰልፍ ሁለቱንም ወገን የደገፉ ኃይሎች ወጥተዋል። ከሁሉም አስደሳቹ ደግሞ ልዩነቶቹ ወደ ግጭት አለማምራታቸዉ ነዉ። በትግራይ ሚዲያዎችም በሚዛናዊነት ለመዘገብ እየጣሩ ነዉ። ይህ በተቀረዉ ኢትዮጵያ አይታሰብም። ይህንን በትግራይ ሕዝብ ትግል የፈነጠቀዉን የዲሞክራሲ ጮራ መንከባከብ ይገባል።

ይህ ነጻነት በአሁኑ ሰዓት የተቀረዉ ኢትዮጵያዊም ሆነ ኤርትራዊ ቢመኘዉም የማያገኘዉ ነው። እናም ይህ የታየዉ የዴሞክራሲ ጮራ መልሶ እንዳይጠፋ ሁለቱም ቡድኖች ከነደጋፊዎቻቸዉ ብዙ የጋራ አቋም እንዳላቸዉ አዉቀዉ ልዩነታቸዉን በጨዋ ደምብ ማራመድ አለባቸዉ። በተለይ TDF ከወገንተኝነት መዉጣት አለበት። ከዛ ዉጪ በሁለቱ ጎራ ያሉ ኃይሎች በጋራ የሚስማሙባቸዉን ነጥቦች አንጥረዉ ማዉጣት አለባቸዉ።

በእነ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመራዉ ህወሓት አሁን ህወሓት ነጻ አዉጪ ሳይሆን ከጨቋኝነትና ከጠርናፊነት ነጻ ወጪ መሆኑን ነጻ ያወጣዉም የትግራይ ሕዝብ መሆኑን ማመን አለበት። በተለይ ሁለቱ ቡድኖች በጋራ የሚስማሙባቸዉን ነጥቦች ከለዩ በሻዕቢያ ተላላኪነትና በፌደራል መንግስት ተላላኪነት የሚካሰሱበትን ነገር ማቆም ይችላሉ።

የሁለቱ ልዩነት ረግቦ በጋራ የትግራይን ግዛታዊ አንድነት አረጋግጦ፣ ወደ ምርጫ ከሄደ አለጥርጥር ትግራይ በኢትዮጵያ እጅግ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በመፍጠር፣ የተሻለ ሚዛናዊ ሚዲያ በመገንባት ቀዳሚ የማትሆንበት ምክንያት የለም።

እዚህ ጋር አንድ ማንሳት የምፈልገዉ ነገር ዶክተር ደብረጽዮን ከፕሪቶሪያ ስምምነት በሁዋላ ወደ መቐለ የሄዱ ባለስልጣናት ፊት ሻዕቢያ ተጋብዞ ገብቶ ያደረሰዉን ጥፋት ጠቅሶ አዉርቷል። እኔ ደብረጽዮን ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ፤ በአንጻሩ ደግሞ የፈደራል መንግስቱ ጥፋተኛ ነው።

ዛሬ የፌደራል መንግስት የነ ዶክተር ደብረጽዮንን ቡድን ከሻዕቢያ ጋር እየተነጋገረ ነው ብሎ በአክቲቢስቶች በኩል የሚከሰዉ፣ የራሱ መርህ አልባነት ያሰራዉ ወንጀል ስላለ የሞራል ground ስላጣ ነው። በቀጥታ ሻዕቢያ ጋርም የቃላት ጦርነት ዉስጥ የገባዉ አንዱ ምክንያት ህወሓት ከሻዕቢያ ጋር እያሴራችሁ ነዉ ብሎ ለመክሰስ የሚያስችል የሞራል ብቃት ስለሌለዉ ነው።

ከላይ ለትግራይ ኃይሎች አቅጣጫ ያልኩትን ጠቁሚያለሁ ፌደራሉ መንግስት ደግሞ በአሁኑ ሰዓት የሚበጀዉ በቀጥታ የፕሪቶሪያን ስምምነት ማጓተቱን ትቶ የአፍረካ ሕብረት ታዛቢዎች አየገመገሙት መተግበር ነው።

የፌደራሉ መንግስት በተለይ የትግራይን ግዛታዊ አንድነት አረጋግጦ ወደ ቀጣይ እንቅስቃሴ እንዳይኬድ እንቅፋት ማድረጉ፣ የሐገሪቷን ችግሮች እያወሳሰበ ይገኛል። የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲተገበር ሁሉም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጫና ማሳደር አለበት።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

#Ethiopia #southethiopia #Tigray #Eritrea