“መባከን የሌለበት እምቅ የፖለቲካ አቅም… ወዲ ረዳ! የወዲ ረዳ፣ አነጋጋሪው ጌታቸው ረዳ ቀጣይ መዳረሻ እስከየት ነው?”

በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ
ላለፉት ሁለት አመታት የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ፕረዚዳንት የነበሩት አቶ ጌታቸዉ ረዳ ከሰሞኑ ስልጣናቸዉን ምትክላቸዉ ለነበሩት ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ አስረክበዋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የጫካ ባህልናባህሪ የተላበሱ ሰዎች የሚበዙበት መሆኑ ስለሚታወቅ አልያም ሕወሓት የ paramilitary ባህሪዉን ማስጠበቁ ለትግራይ ይጠቅማል ተብሎ ከታመነም፣ በአጭሩ የትኞቹ ኃይሎች ምን አስበዉ ጌታቸዉን አነሱት የሚለዉን በቢሆን ከመተንተን ተቆጥበን ዛሬ ግን ስለ ወዲ ረዳ አንዳንድ ነጥቦችን እናነሳለን።
ጌታቸዉ ዉልደቱ አላማጣ ነው፣ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪዉን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የሁለተኛ ዲግሪዉን ደግሞ ከአላባማ ዩኒቨርስቲ አግኝቷል። በመቐለ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት አገልግሏል። በጋዜጣ አምደኛነት፣ በዉጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ በኮሚዉኒኬሽን ሚኒስቴር አቅሙን አስመስክራል።
ስለ ወዲ ረዳ ብቃት እና አንባቢነት ብዙ የሚያዉቁ ሰዎች ከሚሰጧቸዉ ምስክርነቶች ባለፈ በተለያዬ አጋጣሚ የሚያደርጋቸዉን ንግግሮች እና ቃለምልልሶች ማየቱ ሊያረጋግጥልን ይችላል። በጦርነት እሳት መሐል ሆኖ በስሜታዊነት የሚያደርጋቸዉ የቃለምልልስ ንግግር እና ስድቦች ዉስጥ እንኳን ዉሃ የሚቋጥሩ ቁም ነገሮች አሉ።
ከንግግሮቹ ዉስጥ የሐገሪቷን ችግር ጥልቀት የሚረዳበትን መንገድ ማስተዋልም ይቻላል።
ሰዉዬ ንግግር እና ቃላት ሰንጠቃ ብቻ አይደለም የሚችለው የሚናገራቸዉ ነገሮች ዉስጥ substance አለ፣ የሐሳቦቹ የጥራት ደረጃም መሳጭ ነው።
ሌላዉ የአቶ ጌታቸዉ አስገራሚ ባህሪ፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ላይ ከስልጣን ከተነሱ በኃላ ብዙ ወዳጅ የነበሩ ሰዎች ጭቃ ሲለጥፉ ወዲ ረዳ ያንን መንገድ አልመረጠም፣ ለነገሩ ሎጂክ እና እዉቀት የዘለቀዉ አዕምሮ ምክንያታዊ ነው። በግልጽ እንቅፋት የነበሩ ነገሮችን ጠቅሶ እዉቀት ያለዉና ሚዛናዊ ሰዉ መሆኑን አስመሥክሯል።
በትግራዩ ጦርነት ወቅት በብዙ የሞት ደጆች ያለፈዉ ጌች፣ የፕሪቶሪያን ስምምነት ለመፈራረምም ግምባር ቀደም ተደራዳሪ ከሚባሉ ሰዎች መሐል ነበር። በሐገራችን ፖለቲካ ተሳትፎ፣ አንዳንዶች ኣርዓዶም፣ ሳኒታይዘር እያሉ በቅጽል ስም እስኪጠሩት በደረሰበት፣ ከአላማጣ እስከ አላባማ፣ ከመቐለ እስከ አዲስ አበባ፣ የሕይወት ጎዳና ብዙ ዉጣ ዉረዶችን አሳልፉልና ወደ መጽሐፍ ቢቀይረዉ ታሪኩ ብዙ ቁምነገሮች የታጨቁበት ጠቃሚ ይመስለኛል።
በቅርቡ አንድ ሚዲያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን አንድ ጥያቄ ጠየቃቸዉ፣ “እርሶዎ ያለፉበትን የሕይወትና የአስተዳደር ጉዞ በመጽሐፍ መልክ የማጋራት ሁኔታስ እንዴት ያዩታል የሚጠይቁ ሰዎችስ የሉም ወይ?” እርሳቸውም ሲመልሱ “መጽሐፍ መጻፍ ይቻላል መቼ እንዴት የሚለዉን መመለስ ይጠይቃል እንጂ፣ መጻፍ ከባድ ነገር አይደለም ግን ያማረ መጽሐፍ ሆኖ እንዲወጣ የተወሰነ ምርምር መካሄድ አለበት። ዝም ብሎ ማረሚያ ቤት ቁጭ ብሎ የሚጽፉት አይነት ዲስኩር መጻፍ ይቻላል” ብለዋል።
ጨምረውም “እኔ እንደዛ አይነት ጽሑፍ እንዲጻፍ አይደለም የምፈልገው። እኔ የምፈልገዉ ትክክለኛ የአጻጻፍ ሥርዓት ተከትሎ ምርምር ተካሂዶበት፣ ምንም አይነት የ data መጣረስ በሌለበት፣ የ information መጣረስ በሌለበት፣ ልትጠቅስ የምትችልበት ማጣቀሻም ኖሮ ነው። ዲስኩር ቀላል ነው፣ በአንድ ሳምንት ጨክነህ ቁጭ ካልክ 200፣ 300፣ 400፣ 500 ገጽ መጻፍ ትችላለህ። ያ ጽሑፍ አይደለም። Research እንዲካሄድ ጥረት እያደረግኩኝ ነው ያለሁት። የራሱን ጊዜ ወስዶ ይጻፋል የሚል ተስፋ ነው ያለኝ።” ብለው ነበር።
አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በመጽሐፎቻቸዉ መግቢያ ላይ “ይህ መጽሐፍ ለጥናታዊ ሥራ ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም” እያሉ እንዳሻቸዉ ለመዘላበድ እንዲመቻቸዉ እያስቀመጡ እንደሚጽፉ ልብ ይሏል።
ታዲያ ወዲ ረዳ ከዚህ አንጻር ደረጃዉን የጠበቀ መጽሐፍ ማበርከት እንደማይከብደዉ ይታወቃል፣ ጥሩ ብዕረኛ እንደሆነም የአዲስ ነገር ጋዜጣ አንባቢዎች ይመሰክራሉ፣ እናም ሚዛን የሚደፋና ለሌሎች ፖለቲከኞች መማሪያ የሚሆን መጽሐፍ መጻፍ የሚችል ይመስለኛል።
በተለይ በወቅቱ ተነባቢ በነበረዉ አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ጌታቸዉ የተከተለዉ የመጋፈጥ ስልት ኢሕአዴግ፣ ጋዜጠኞች ከሚያስር በተጠናከረ ሁኔታ ቢገፋበት የሚሻል መንገድ የነበረ ይመስለኛል። ከዚህ ባለፈ አቶ ጌታቸዉ ረዳ እድሜዉም ብዙ ያልገፋ ከመሆኑ ባለፈ ያለዉ እምቅ የፖለቲካ አቅም፣ ልምድና እዉቀት መባከን የለበትም የሚል እምነት አለኝ።
ስለዚህ የተሻለ ነጻነት ያለዉ ሹመት ከተገኘ፣ አልያም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት ካልሆነም በግል በመወዳደር የፓርላማ አባል በመሆንም ቢሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ መቆየት ያለበት ሰዉ ይመስለኛል። በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ፓብሊክ ሌክቸሮችን በሐገር ዉስጥ ሆነ ዉጪ ቢሰጥ ደግሞ መሳጭ የሚሆን ይመስለኛል። ለወዲ ረዳ መልካሙን ሁሉ እንመኝለታለን።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
Ethiopia #southethiopia #Amhara #oromo #Tigray #Wolaita
ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።