“የመስቀል በዓል የጣዖት በዓል ነው” ያለውን ግለሰብ ፍርድቤቱ በነጻ መልቀቁ ቅሬታ መፍጠሩን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የዎላይታ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ገለፁ።

በሌላ በኩል አንድ የሀይማኖት አባት “መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ማንኛውንም የክርስቶስ ተከታይን የሚመለከት እንጂ አንድ ቤተክርስቲያን ወይም ግለሰብ በብቸኝነት የእኔ ነው በሚል በየትኛውም አካሄድ ማንንም መጠየቅ አይችልም” ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት በዎላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ አቶ መርክነህ መጃ የተባለ ግለሰብ ሰኞ መስከረም 5 ቀን 2017 ዓ.ም በግል የፌስቡክ ገጻቸው ላይ “የመስቀል በዓል እንግዲያውስ እስከተነሳ ድረስ እንነጋግርበት” በማለት በመጻፋቸው፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዎላይታ ሀገረ ስብከት ክስ መስርቶ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስከበር ግለሰቡን በሕግ ጥላ ሥር እንዲቆይ በማድረግ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ግለሰቡ በዋስትና ተለቅቆ በውጭ ሆኖ ክሱን ሲከታተል መቆየቱን ያብራሩት የዎላይታ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ቦክቻ ኤንጋ፣ “በመጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም የወረዳው ፍ/ቤት በዋለው ችሎት ተከሳሹን በነጻ ማሰናበቱን በመግለጹ ሀገረ ስብከቱ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርበን ሳለ የቤተ ክርስቲያን መብት አልተከበረም ሉዓላዊነቷም ተደፍሯል” በሚል ይግባኝ ማለቱን ለተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል አሳውቀዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ ግለሰቡ “በዚህ በዓል እግዚአብሔር አይደለም የሚከበረው” ያሉ እና “ገና ከመነሻው የጣኦት አምልኮ የተካተተበት ነው” በማለት በማኅበራዊ ገጻቸው ያስተላለፉ ሲሆን ይሄንንም በምሳሌ ብለው ሲያስረዱ “እንደሚሉት ንግሥት እሌኒ መስቀሉን በእሳት ጭስ ተመርታ ካገኘች በኋላ የምስጋና ጭስ ላስገኛት አካል አቅርባለች በማለት ለጭሱ የሚያመልኩም አሉና፡፡” በሚል ቢያስተላልፍም የወረዳው ፍ/ቤት በነጻ በመልቀቁ ቅሬታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
“ግለሰቡ በማንአለብኝነት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰሱ ቅርሶች ያስመዘገበቺውን ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ በዓል የሆነውን የመስቀል ደመራ በዓልን ጣኦት ማምለክ ብሎ የጥላቻ ንግግር ማድረጉ መንግስት በልዮ ትኩረት ሊከታተለው እንደሚገባ እያስገነዘብን በቀጣይ ፍትህ እንደምናገኝ በልበ ሙሉነት እየተማመንን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የተጠየቀ መሆኑን እገልጻለሁ” በሚልም የሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ቦክቻ በዛሬው ዕለት በግል ማህበራዊ ሚዲያ ያስተላለፉትን መልዕክት የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተመልክቷል።
አንድ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውጪ የሆነውን ሀይማኖት የሚከተልና ስማቸውን ለመጥቅስ ያልወደዱት ሀይማኖት አባት ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው እንደገለፁት “ቤተክርስቲያንቷ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበችው የመስቀል ክብረበዓል አከባበርን እንጂ የመስቀሉ ባለቤት በመሆን አይደለም፣ መስቀል ክርስቶስ የተሰቀለበት ስለሆነ ጉዳዩ ማንኛውንም የክርስቶስ ተከታይን የሚመለከት እንጂ አንድ ቤተክርስቲያን ወይም ግለሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ በብቸኝነት የእኔ ነው በሚል በየትኛውም አካሄድ መጠየቅ አይችልም” ብለዋል።
እኚህ የሀይማኖት አባት አክለውም “ምናልባት ተከሶ ነበረ የተባለው ግለሰብ ስለመስቀል ከመናገሩ ውጪ ከሳሽ የነበረ ቤተክርስቲያንን በስም ጠርተው ያንቋሸሸ እንደሆነ በህግ ሊጠየቅ ይችላል እንጅ በአለም ውስጥ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የመላው ክርስቶስ ተከታይ የሆነው በሙሉ እኩል የሚመለከት “መስቀል” በተመለከተ የሰጠው አስተያየትና ሀይማኖታዊ አስተምሮ በየትኛውም መመዘኛ የባለቤቱ የክርስቶስ ተጠያቂነት ቢሆን እንጂ ሌላ በባለቤትነት የሚመለከተው የለም” በሚልም አብራርተዋል።
የዎላይታ ዞን የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቶ መርክነህ መጃ የተባለ ግለሰብን በነጻ ለማሰናበት በሰጠው ውሳኔ ላይ “በሀይማኖታዊ አስተምህሮ ማስታወቂያ ነው ተብለው የተለቀቀ መሆኑን ሲገልፅ በክሱ ላይ ግን የቀረበው በቀጥታ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት መስቀል በዓል የሀሰት ወሬ በመረጃ የተሰራጨ ተብሎ የቀረበው ሀሳብ የክሱ የ0አቃቤ ህግ ማስረጃ እንዳሉት ያላስረዳ እንደዋናነት ከተያዘው ከሚዲያ ስርጭት ጋር ያልተዋሄደ በመሆኑም ያልተገናኘም ስለሆነ የዐቃቤ ህግ ማስረጃም እንደ ክሱ ከጥርጣሬ በላይ ያላስረዳ ሲሆን የተከሳሽ መከላከያ ማስረጃ ከጥርጣሬ በላይ ያስረዳ ሆነው ከሳሽ አቃቤ ህግ በመቃወሚያ ክርክር ላይ በወንጀል መቀጫ ህግ ቁ 4 ላይ በጠቀሰውም ሆነ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባወጣው አዋጅ ቁ 1185/2012 አንቀጽ 6(1) መሠረት ጉዳዩ ተከሳሽን በህግ እንደማያስጠይቀው አስረድተዋል።



ፍርድቤቱ አክለውም ሲያስረዳ “አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ወይም እንደ ሀሰተኛ መረጃ ተወስዶ ማሰራጨት የማይከለክለው የሃይማኖታዊ አስተምህሮ አካል እንደሆነ ስለሚገልጽ ተከሳሽ በሚዲያው ላይ ያሰራጨው የሃይማኖታዊ አስተምህሮት በመሆኑ እንዲሁም የተከሳሽ መከላከያ ማስረጃም አስፍተው በማስረዳት የዐቃቤ ህግ ማስረጃን ያስተባበለ በመሆኑ በወንጀል መቀጫ ሠ/ሕ ቁ 149/2 መሠረት ተከሳሹን በነፃ ለቅቀናል” ማለቱን ከሰነዱ ለማረጋገጥ ችለናል።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏