1000053171

“አድሏዊ አሰራሮች የጨረቃ ክልል በማድረጉ ወትሮም የታፈነዉ የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ መልሶ ወደ አደባባይ መምጣቱን አይቀሬ ያደርጋል”

በብዙ ዉዝግብ ታጅቦ፣ በተለይ በዎላይታ ዞን ሕዝበ ዉሳኔ ተደግሞ፣ በዋዜማዉ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባሰራጨዉ ዉጤት በሚያዛባ ዘገባ ታጅቦ የተመሰረተዉ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕገመንግሥቱ እስካሁን ለሕዝቡ ይፋ አለመደረጉ ማወዛገቡን ቀጥሏል።

ስለ ጉዳዩ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያነጋገረው አንድ የክልሉ ተወላጅ ምሁር፣ ሕዝብ ሕገመንግሥት ይፋ ካልተደረገ፣ ሕዝቡ መብትና ግዴታዉን በክልል ደረጃ ሊገነዘብ አይችልም፣ ከሚያስተዳድረዉም አካል ጋር ሊናበብ አይችልም ብሏል። አክለዉም የሕገመንግስቱ መደበቅ ሌሎች ጥርጣሬዎችንም እንደሚፈጥር፣ ሕዝቡም አንዳች ሸፍጥ ቢኖር ነው የተደበቀዉ እያለ እንደሚያስብ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሕገመንግሥት በክልሉ ሕዝብና መንግስት መሐል ያለ ዉል ስለሆነ ይፋ መደረግ እንዳለበት አንስተዋል።

ሌላ አንድ የደቡብ ኢትዮጵያን ክልል ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ሰው ስለጉዳዩ ጠይቀናቸዉ፣ በቀድሞ ደ/ብ/ብ/ሕ/ክ ተመስርቶ ከ10 ዓመት በላይ መረጋጋት ርቆት የቆየዉን ክልል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ርዕሰ መሥተዳደርነት መጥተዉ ማረጋጋትና ወደልማት መሥመር ያስገቡት የክልሉን ሕገመንግሥት በማሻሻል መሆኑን ገልጸዋል።

ሕገመንግሥቱም የስልጣን ክፍፍልና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጡ ክልሉ መረጋጋቱን ጠቅሰዋል። ሕገመንግሥቱ ታትሞ መሰራጨት እንዳለበት አንስተዉ፣ የበለጠ የተሻለ የነበረዉ ግን ረቂቁ ቀድሞ ለሕዝብ ተለቆ ቢተች ጥሩ እንደነበረ አንስተዋል።

በተጨማሪም በኢህአዴግ ጊዜ የክልል ሆነ የፈደራሉ ሕገመንግሥት በደቡብ በብዛት እንደሚገኝ፣ ታትሞም በስፋት ይሰራጭ እንደነበረ፣ በገበያም በቀላሉ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የክልሉ ሕገመንግሥት ታትሞ አለመሰራጨቱ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንደሚያጭር ጠቁመዉ፣ ለምሳሌ በቅርቡ ዎላይታ ሶዶና ሌሎች ሁለት ከተሞች ሪጂኦፖሊታን ሲደረጉ፣ የራስን እድል በራስ የመወሰኑን፣ የፈደራሉ ሕገመንግሥት ላይ የተጠቀሰዉን የብሔሮችን መብት በሚጥስ መልኩ ተጠሪነታቸዉ ለክልሉ መደረጉ፣ ከክልሉ ሕገመንግሥት ጋር ይጋጫል ወይስ አይጋጭም የሚለዉን ማወቅ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

ሌላዉ ደግሞ በፈደራልም ሆነ፣ በክልሉ፣ የክልሉ አካል የሆኑ ዞኖች ፍትሐዊና ሚዛናዊ ዉክልና ማግኘት እንደሚገባቸዉ፣ በኢኮኖሚም ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መኖር እንዳለበት ያም በሕገመንግስቱ መጠቀስ እንዳለበት አንስተዋል። አሁን ግን ብዙ ነገሮች ግራ ያጋባሉ፣ ነገሮች በምን እንደሚመሩ ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በክልሉ አድሏዊ የፌደራል ጣልቃ ገብነት በስፋት እንደሚታይ አንስተዉ፣ ለምሳሌነት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኮሪደር ልማቱን፣ በክልሉ ከተሞች ክልሉ በግልጽ መስፈርት በራሱ ወስኖ ሲመራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንድ ከተማ በፈቃዳቸዉ በብቸኝነት ገንዘብ በመስጠታቸዉ ሌሎቹ በራሳቸዉ አቅም እየዳከሩ ነው ብለዋል።

ሌላዉ ምሳሌ በተመሳሳይ ያለ ክልሉ ግልጽ ና ፍትሐዊ መሥፈርት በፈቃዳቸዉ የሁለተኛ ደረጃ ከተማ እንደመረጡ በስብሰባዎች ላይ ማሳወቃቸዉን፣ እነዚህም ነገሮች በዎላይታ ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ የብሔር ጭቆና መሆኑንም ገልጸዋል።

የክልሉ ሕገመንግሥት የተደበቀዉ ምናልባት መሬት ላይ ያለዉን ሁኔታ ከሕግ ዉጪ በመቀየር፣ አንዳንድ አደገኛ ማሻሻያዎችን አድርጎ ይፋ ለማድረግ እንደሚጠረጥሩ ገልጸዉልናል።

መሰል አድሏዊ አሰራሮች ክልሉን የጨረቃ ክልል እንዳደረጉት ጠቁመዉ፣ በተለይ ወትሮም የታፈነዉ የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ መልሶ ወደ አደባባይ መምጣቱን አይቀሬ ያደርጋልም ብለዋል።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

#Ethiopia #southethiopia

ተ