“የወልቃይት ጉዳይ ምን እያለማመደ ነው ?…

በትግራይ ክልል በተነሳዉ ጦርነት ሰበብ የአማራ ክልል ኃይሎች የትግራይን 40% መሬት ነባሩን የአስተዳደር ወሰን ጥሰዉ በመግባት መያዛቸው፣ የራሳቸዉንም አዲስ አስተዳደር ማቋቋማቸዉ ይታወሳል።
ነገር ግን ይህንን እጅግ ብዙ ደም የፈሰሰበትን አስከፊ ጦርነት ለማስቆም፣ በሕወሓት እና የፌደራል መንግስት መሐከል በተደረገዉ የፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ከመከላከያ ሠራዊት ዉጪ የሆኑ ኃይሎች ከነባሩ የትግራይ ክልል ግዛት እንደሚወጡ እና ይሄም የፌዴራል መንግስት ኃላፊነት መሆኑ ተቀምጧል።
ስምምነቱ ከተፈረመ ሁለት ዓመታት ቢያልፈዉም፣ እስካሁን የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፣ መዋቅሩን በነባሩ መላዉ ትግራይ የዘረጋበትና ተፈናቃዮች የተመለሱበት ሁኔታ ሊፈጠር አልቻለም። ጉዳዩ አወዛጋቢ ነገሮች ቢኖሩትም በተለይ የአማራ ክልል መንግስት እና ሚዲያዎች በሕገወጥ መንገድ የተቋቋሙና በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ተቀባይነት የሌላቸዉን አካላት ሕጋዊ አድርገዉ ማቅረባቸዉ ግራ የሚያጋባ ነው።
ጭራሽ ከሰሞኑ የተከዜ ዘብ የተባለ የታጠቀ ኃይል በሚመረቅበት ቦታ የመከላከያ ሰዎች መገኘታቸዉ ነገሩን የበለጠ አወዛጋቢ አድርጎታል።
በኢትዮጵያ ዉስጥ ባሉ ክልሎች መሐከል ከአስተዳደር ወሰን፣ ከማንነት፣ ከአስተዳደራዊ መዋቅር ጋር ተያይዞ ብዙ ዉዝግብ አለ። ነገር ግን እነኝህን ዉዝግቦች ከሕገመንግስቱና ከተጨማሪ የሰላማዊ የትግል መሥመር ዉጭ መፍትሔ አመጣለሁ ማለት ሐገር አፍራሽ፣ ግጭት ቆስቋሽ አካሄድ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
የአማራና የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ ተቀራራቢ ቋንቋና ባህል፣ ብዙ የጋራ ታሪክም ያለዉ ነው። ድሮም አብሮ ኖሯል፣ አሁንም ሆነ ወደፊትም አብሮ ከመኖር ዉጪ አዋጭ የሆነ አማራጭ የለዉም። ስለዚህ የሁለቱም ሕዝቦች የፖለቲካ ኃይሎች አካሄድ ልዩነቶችን የሚያጠብ እንጂ የሚያሰፋ መሆን የለበትም።
የአማራው ሕዝብ በወልቃይት ጉዳይ ላይ ጥያቄ ሊኖረዉ ይችላል ያ ምንም ችግር የለዉም፤ ነገር ግን በጉልበት የፌደራል መንግሰት ሽፋን ሰጥቶ እንኳን ቢመለስ ነገሩ በጣም የማይበርድ እሳት በትግራይ ከማጫሩም በላይ፣ በተቀረዉ የኢትዮጵያ ክፍልም ብዙ ቀዉስ የሚፈጥር ነው።
ለምሳሌ በቅርቡ የኦሮሚያና የሱማሌ ክልል ፓርቲዎች በድሬዳዋና ሞያሌ ጉዳይ ላይ ቃላት መለዋወጣቸዉ ይታወሳል። እኛ እንደ አንድ ሐገር ዜጋ ችግሮቹ በሕገመንግስታዊና ሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት እስኪፈቱ ቀድሞ በነበሩበት የአስተዳደር መንገድ እየተዳደሩ እንዲቀጥሉ ከማድረግ ዉጪ አማራጭ ያለን አይመስለኝም።
የዎልቃይት ጉዳይ በጉልበት ከተፈታ የድሬዳዋና የሞያሌ ጉዳይ ላይ አንዱ የጉልበት አማራጭ ከተከተለ ሐገር እንዴት ሊተራመስ እንደሚችል ማሰብ ይቻላል።
በቅርቡ የኦሮሚያ ፓርቲዎች አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል አካል ነች የሚል መግለጫ ማዉጣታቸዉ ይታወቃል፣ አቋም መያዛቸዉ ችግር ባይኖረዉም በጉልበት እናስፈጽም ካሉ ግን ነገሩ ሐገር አፍራሽ አካሄድ መሆኑ ግልጽ ነው።
ስለዚህ ዎልቀይት ያሉ አማሮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው የተለዬ የፌደራል መንግስት ከለላ እንዲደረግላቸዉ ቢጠየቅም ተገቢ ነው፣ በአካባቢው ከተደረገዉ ከባድ ጦርነት አንጻር፤ ከዛ ባለፈ ግን በጉልበት ከአንድ ክልል ግዛት መንጠቅ፣ ሐገሪቷን ወደሌላ የግጭት አዙሪት የሚከት ነው።
ሌላው ደግሞ የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር መሬቱን መልሶ ተረክቦ መዋቅሩን በመዘርጋት ተፈናቃዮች ከመመለስ በተጨማሪ ለዎልቃይት ነዋሪ አማሮች የተለዬ ከለላ እንደሚያደርግ መብታቸዉን ሳይሸራረፍ እንደሚያስከብር በሚያወጣቸዉ መግለጫዎች ላይ መግለጽ አለበት።
የአካባቢው ነዋሪ ወደ ቀደመ ሰላሙና ወደ አብሮ መኖር እንዲመለስ እቅድ አዘጋጅቶ መግለጽ አለበት። የሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሕዝብን የበለጠ ማቀራረብ ላይ ያተኮሩ መሆን አለባቸዉ።
በተለይም የአማሮቹ የባህልና ቋንቋ መብት የሚከበርበት፣ ከተቻለ በትግራይ የአስተዳደር መዋቅር ዉስጥም በቋንቋቸው የሚገለገሉበት መንገድ ሊመቻችላቸዉ ቃል መግባት አለበት።
በአማራ ክልል የፖለቲካ ኃይሎች በኩል ደግሞ፣ የአንድና ሁለት ወረዳ መሬት ለሺህ ዘመናት አብሮ የኖሩ የአማራና የትግራይ ሕዝብ ልጆችን ሕይወት ብቻ ሳይሆን ጊዜም ከዚህ በላይ መብላት እንደሌለበትና ለአጠቃላይ ሐገራዊ ፖለተካ ም እንቅፋት ሆኖ መዝለቁ ማንንም ተጠቃሚ እንደማያደርግ መገንዘብ አለባቸዉ።
ከዚህ በተጨማሪ በመላዉ የአማራ ክልል አሁን ላይ ያለዉን ግጭት ለማስቆም በላቀ ትኩረት ቢሰሩ የበለጠ መልካም ነው። አማራ በሁመራ ብቻ ሳይሆን በመቐለ እና አክሱምም ይኖር ነበር፣ ወደፊትም በዚህ አስተሳሰብ ነው ፖለቲካዉ መቃኘት ያለበት። አማራም በትግራይ ይኖራል፣ ትግራዋይም በአማራ ክልል ይኖራል፣ ወደፊትም ከዚህ ዉጪ አማራጭ የለም።
ሌላዉ የአማራ ክልል ፖለተካ ዎልቃይትን እንደ አንድ ጥያቄ እንጂ ብቸኛና የሕልዉና ጥያቄ አድርጎ ማየት የለበትም፣ ሕዝቡ ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችም አሉትና። ይሄ ጉዳይ ከዚህ በላይ ለአማራ ክልል ሰላም መደፍረስ ምክንያት መሆን የለበትም፣ አንድና ሁለት ወረዳ ሐገር ማሳጣት የለበትም።
የፌደራል መንግስት ደግሞ እስካሁን በግልጽ እንደታዬዉ ትግራይን እንደጠላት ማየቱን በማቆም የፕሪቶሪያን ስምምነት በሙላት ለመተግበር የበኩሉን ቢወጣ መልካም ነው፣ ሐገር በሕገመንግስታዊ መንገድ ከዚህ ቅርቃር መዉጣት አለባት። በተለይ የትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸዉ እንዲመለሱ በከፍተኛ ትኩረት ሊሰራ ይገባል።”
በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ የተጠናቀረ ልዩ ዘገባ ነው።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
ወልቃይ የአማራ ናት!!