By Journalist Natnael Gecho
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትግራይ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ወጣቶችን ያገለለ አድሎአዊ የሥራ ቅጥር አሰራርን ይቅርታ ጠይቆ በአስቸኳይ እንዲያርም ተጠየቀ።

አየር መንገዱ በቅርቡ ለሰልጣኞች አይሮፕላን ሜካኒክስ ባወጣው የቅጥር ማስታወቂያ ላይ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ የትግራይ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ወጣቶች ያገለለ አድሎአዊ የሥራ ቅጥር አሰራርን ማውጣቱን “ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች” የተሰኘ ድርጅት አድሏዊ አሰራርን በፅኑ አውግዟል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውቶሞቲቭ ወይም የምህንድስና ሰርተፍኬት ለያዙ ወጣቶች ክፍት የሥራ እድል እንዲያመለክቱ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ማስታወቂያ በኦንላይን ያወጣው የማመልከቻ ማዕከላቱ የሚገኙት በተመረጡ ልዩ ልዩ ክልሎች ማለትም በዝርጋታው በማዕከላዊ፣ በምዕራብ፣ በምስራቅ፣ በሰሜን ምዕራብ ብቻ ሆኖ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን እና ፖሊ-ቴክኒኮችን ማለትም መቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ እና ራያ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ፖሊ-ቲክኒኮች ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እና ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን ሳይካተቱ ቀርቷል ብሏል።
ይህ ድርጊት ኢትዮጵያ የተጣለባትን አገራዊ እና አለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ግዴታዎችን በግልፅ የሚጥስ መሆኑንም ድርጅቱ በመግለጫው አሳውቋል።
“ድርጊቱ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸውን በአለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን የሆነውን የእኩልነት እና የስራ መብቶችን የሚጥስ አደገኛ ተግባር ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ያጸደቀችው በዘር፣ በብሔር፣ ወይም በክልል ደረጃ በሥራ ስምሪት ላይ የሚደረገውን አድልዎ የሚከለክል ነው” በሚል ድርጅቱ ካወጣው መግለጫ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተመልክቷል።
በመሆኑም “ይህ አድሎአዊ የሥራ ቅጥር አሰራርን በትግራይ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች ከመላ አገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች ጋር በእኩል የሥራ እድል እንዳያገኙ ያለምክንያት እንዳይወዳደሩ የሚከለክል ሆኖ ለወጣቶቹ ወሳኝ የሥራ እድል የሚነፍግ፣ ክልላዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መገለልን የሚያጠናክር፣ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስታዊ የእኩል ዜግነት እና አድሎአዊ ያለመሆን ቃል ኪዳን የሚጥስ እና ትግራይ በድህረ ጦርነት የምታደርገው የማገገም ጥረትን የሚጎዳና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል” ብሏል።
በተጨማሪም በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም በድህረ የ2015 ፕሪቶሪያው ስምምነት በትግራይ ተወላጆች ላይ ላደረሰው አድሎአዊ የአገልግሎት አሰጣት እና የዋጋ ተመን በፌዴራል ፍርድ ቤት ተጠያቂ ተደርጎ እንደነበርና የእርምት እርምጃ እንደወሰደ አስታውሷል።
አሁንም በትግራይ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ወጣቶች ላይ ተመሳሳይ አድሎአዊ ድርጊቶች መደጋገም የተቋማዊ አድሎአዊ አሰራርን የሚያመለክት ሲሆን በኢትዮጵያም ሆነ በአለም አቀፍ ህግ የተደነገገውን ፀረ-አድሎአዊ አሰራርን የሚጻረር ተግባር በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አድሎአዊ የሥራ ቅጥር ድርጊት አንጻር፣ ድርጅታችን ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የሚከተሉትን የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በጽኑ ይጠይቃል ብሏል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቅጥር ማስታወቂያው በአስቸኳይ በማሻሻል በትግራይ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ ለወጣቶች ተደራሽ የሆኑ የማመልከቻ ቦታዎችን ወይም የዩኒቨርሲቲ ማዕከላት ወይም ኦንላይን አፕሊኬሽን ፖርታል እንዲያሳውቅ እና ከሚያዝያ 20 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ያስቀመጠውን የማመልከቻ ጊዜ ማሻሽያውን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ጊዜው እንዲያራዝም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የህዝብ እንባ ጠባቂ አድሎአዊ አሰራርን በገለልተኝነት መርምረው ግኝቱን በይፋ እንዲያሳውቁ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የፍትህ ሚኒስቴር ሁሉም የመንግስት የልማት ድርጅቶች በቅጥር ልማዶች ውስጥ ከአድልዎ የጸዳ ግዴታዎች መከበራቸውን እንዲያረጋግጡም ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ድርጅት በመግለጫው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደፊት ተመሳሳይ የቅጥር ይሁን የሌላ አይነት አድሎአዊ አሰራር እንዳይፈጽም በገለልተኛ አካል ክትትል የሚደረግበት ሁሉን አቀፍ የእኩልነት የሥራ ስምሪት ፖሊሲ በመውጣት የረጅም ጊዜ ተቋማዊ ማሻሽያ እንዲያደርግና ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ እንዲያደርግም አሳስበዋል።
በመጨረሻም ድርጅቱ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፈጸመውን የመብት ጥሰጥ አምኖ ፍትሃዊ እና አካታች አሰራርን በመከተል ይቅርታ እንዲጠይቅና ይህን አድሎአዊ አሰራር እና የሥራ ቅጥር ሰርዞ የተገለሉትን ወጣቶች አካቶ ማስተካከያ የማያደርግ ከሆነ ግን ጉዳዩ ወደ ሕግ የምንወስደው መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን” ብሏል።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏