1000055742

በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሠባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት 112 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተነገረ።

በሌላ በኩል በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት ትምህርት ያልጀመሩ እንዲሁም ተማሪዎቻቸውን የዘንድሮ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውን የማያስፈትኑ በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

የቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ እየሩስ መንግሥቱ በክልሉ በአጠቃላይ 685 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊዋ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የዘንድሮውን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚያስፈትኑ ትምህርት ቤቶች 470 ብቻ ናቸው ብለዋል።

አክለውም ሰላም ባለባቸው አከባቢዎች በሚገኙ ት/ቤቶች የሚገኙ 99ሺህ 880 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተመዝግበዋል ማለታቸውን የጀርመን ድምጽ በዘገባው አስደምጧል።

ከ አስ ጋር ቆይታ ያደረገ አንድ በሰሜን ጎጃም ዞን የሚገኝ የ12ኛ ክፍል ተማሪ በበኩሉ በክልሉ ሠላም እስኪመጣ አማራጭ ያለውን ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግሯል።

“… ወጥተን ገጠር ቁጭ ብለናል፣ ምን እናደርጋለን፣ ከቤተሰብ ጋር ሆነን ልማት ነገር እናለማለን፣ በመስኖ ልማት ለጊዜው ሽንኩርት እያለማሁ ነው፣ ትምህርቱማ በዚህ ሰዓት የለም፡” ማለቱን አስደምጧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው የክልሉ አከባቢዎች የሚገኙ እና ተማሪዎቻቸውን የሚያስፈትኑ ት/ቤቶች ተማሪዎቻቸው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በመስራት ላይ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

ለአብነትም ሰቆጣ ከተማ በሚገኘው ዋግ ስዩም አድማስ ወሰን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት መንግሥቱ አረጋ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

“በተቃራኒ ሽፍት ሳይቀር ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ነው” ያሉት መምህሩ፣ አክለውም የተሻለ ዝግጅት ያላቸው ተማሪዎችም ሌሎችን እያገዙ ነው ብለዋል፡፡

የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ነጋልኝ ተገኝ በበኩላቸው ወቅታዊው የክልሉ የሠላም ሁኔታው በዞኑ ትምህርት ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ጠቁመው፣ ሆኖም ለአገራዊ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ቀደም ባሉት ዓመታት በየዓመቱ ከ150 ሺህ እስከ 180ሺህ ተማሪዎችን የማስፈተን አቅም እንደነበረው በዘገባው ተካቷል፡፡

በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት አለመጀመራቸው ይታወቃል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም. 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ቢያቅድም የተመዘገቡት ከ2 ሚሊዮን እንደማይበልጡ መግለጹ አይዘነጋም።

ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል በሰላም እጦት ችግር በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙት 996 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተከፈቱት 86ቱ ብቻ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ በክልሉ ሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኙ 565 ትምህርት ቤቶች መካከል መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ የጀመሩት 192 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።

በተጨማሪም በክልሉ በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ስር በሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ስጋት ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደት መቋረጡን መምህራን እና የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ዋቢ አድርገን ዘግበናል።

በክልሉ “ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁን በክልሉ ባለው ግጭት” ምክንያት ጉዳት የደረሠባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት 112 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማስታወቁን ዘግበናል።

የቢሮው ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር ዘመነ አበጀ በጦርነቱ እና በግጭቱ በርካታ ትምህርት ቤቶች መጎዳታቸውን ገልጸው፤ ለአብነትም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ጠቅሰዋል።

ቢሮው ባስጠናው ጥናት መሠረት “በአጠቃላይ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ወደ አገልግሎት ለመመለስ ያገለግላል የተባለው 112 ቢሊየን ብር ትምህርት ቤቶችን ከመገንባትና መጠገን በተጨማሪ ተጓዳኝ የትምህርት ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ነው ብለዋል” ሲል አስ ዘግቧል።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

#Ethiopia #አማራ #ፋኖ