1000056077

By Journalist Natnael Gecho

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ እና ጋሞ ዞኖች የፖሊዮ ቫይረስ መገኘቱ ተገልጿል።

በክልሉ ዎላይታ ዞን ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ዋጭጋ ቡሻ ቀበሌ የ5 ዓመት ዕድሜ ያለው ልጅ የፖሊዮ ቫይረስ እንደተገኘበት ተረጋግጧል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ ክልል ጋሞ ዞን ሰላምበር ውስጥም አንድ የ6 ዓመት ዕድሜ ያለው ልጅ የፖሊዮ ቫይረስ የተገኘበት እንደሆነ WT ለማረጋገጥ ችሏል።

ናሙናው ወደ ፌደራል ላቦራቶሪ ተልኮ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ዛሬ ውጤቱ ለየዞኖቹ ጤና መምሪያዎች እና ለሶዶ ዙሪያ ወረዳ እና ሰላምበር ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ተገልጿል።

WT ሚዲያ ይህንን መረጃ ከተለያዩ ታማኝ ምንጮች ያገኘ ሲሆን፣ ከሁለቱም ዞኖች ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዳይረክተር አቶ ምንተሰኖት መልካ በስልክ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ በ WT ሚዲያ ተጠይቀው ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ መውሰድ ትችላላችሁ” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዚህ ውጪ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከሁለቱም ዞኖች የጤና ባለስልጣናት ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት አልተቻለም። ተጨማሪ መረጃዎች እንደደረሱን ወዲያውኑ እናሳውቃለን።

WT ሚዲያ ከዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት (WHO) የኢትዮጵያ ቢሮ ድረ ገጻቸው ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው እአአ በ1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የፖሊዮ ወረርሽኞች የተከሰተ ሲሆን በወቅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በቫይረሱ ተይዘው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የክትባት ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ በሽታው በእጅጉ ሊቀንስ ችሏል።

የአፍሪካ አህጉር እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2020 ከፖሊዮ ነፃ መሆኗን በይፋ የታወጀ ሲሆን በኢትዮጵያ የዱር ፖሊዮ ቫይረስ ለመጨረሻ ጊዜ የተከሰተው እ.ኤ.አ. ጥር 2014 ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ ምንም አይነት የዱር ፖሊዮ ቫይረስ ጉዳይ አልተመዘገበም።

ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ፈጣን ምላሽ በመስጠት ተጨማሪ ምርመራዎችን በማድረግ እና አስፈላጊውን የክትባትና የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ቫይረሱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ይህ አሳሳቢ ዜና እንደሚያሳየው የፖሊዮ ቫይረስን ለመከላከል እና ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ቀጣይነት ያለው መሆን እንዳለበት ነው። በተለይም የክትባት መርሃግብሮችን በጥብቅ በመተግበር እና በሽታው ከተከሰተም ፈጣን ምላሽ በመስጠት ህብረተሰቡን መጠበቅ ያስፈልጋል።

እንደ መረጃው ከሆነ በህፃናት ላይ የፖሊዮ ቫይረስ የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት የጡንቻ ድክመትን አልፎ ተርፎም ዘላቂ የሆነ ሽባነትን ያስከትላል፣ ይህም በአብዛኛው በእግሮቹ ላይ ይታያል። በከባድ ሁኔታዎች ደግሞ ለመተንፈስ የሚያገለግሉትን ጡንቻዎች ሽባ በማድረግ ለሞት ሊዳርግ ይችላል። ፖሊዮ ከያዘ በኋላ የሚድንበት ምንም ዓይነት መድኃኒት እንደሌለ ማወቅ ጠቃሚ ነው። ሆኖም ግን በክትባት አማካኝነት በሽታውን መከላከል ይቻላል። By Journalist Natnael Gecho

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WT ሚዲያ👏

#Ethiopia #southethiopia