1000056935

ቀደም ሲል በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ የነበሩ ህዝቦችን ያቀፈ አዲስ ተቋም ‘ራይዝ’ (RISE – Right, Inclusion, Solidarity & Equality) በይፋ መቋቋሙን አስታውቋል።

ተቋሙ ትላንት እሁድ ሜይ 18 ቀን 2025 በዓለም ዙሪያ በተደረገ በይነመረብ ስብሰባ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ለበርካታ ወራት በጊዜያዊ ኮሚቴ ሲዘጋጅ እንደቆየ ተገልጿል።

‘ራይዝ’ ምሁራንን፣ የተጽእኖ ፈጣሪዎችን፣ የፖለቲካ ልሂቃንን እና የማህበረሰብ ወኪሎችን ያቀፈ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህን ህዝቦች ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ያለመ ነው።

በተለይም ተቋሙ የፖለቲካ ውክልና ማጣት፣ የመብቶች እና ጥቅሞች መገፈፍ እንዲሁም የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ችላ መባላቸውን በፅኑ ይቃወማል።

ተቋሙ ከተቋቋመ በኋላ ባወጣው ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ ላይ የሚከተሉትን ቁልፍ ጉዳዮች አንስቷል፦

በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉትን ጦርነቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ መንግስት ከሃይል አማራጭ ውጭ የሰላማዊ መፍትሄዎችን እንዲፈልግ አሳስቧል።

በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩትም የህዝቦችን መብቶች የሚጎዱ አንቀጾች እንዳሉ ጠቁሞ፣ እውነተኛ ብሔራዊ መግባባት ሲፈጠር ዝርዝር ግኝቶቹን እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

የሁሉም ህዝቦች የራስን በራስ የማስተዳደር መብት መከበር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥቷል።

መንግስት ትኩረቱን በመሰረተ ልማት ላይ እንዲያደርግና ፋይዳ በሌላቸው የልማት ፕሮጀክቶች ህዝብን ከማፈናቀል እንዲቆጠብ አሳስበው በተለይም ባለፉት 7 አመታት በአካባቢው የልማት ስራዎች መስተጓጎላቸውን አንስቷል።

የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እያነሱት ላለው የኑሮ ውድነት ጥያቄ መንግስት በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል።

መንግስት ከኤርትራ ጋር ሊያደርገው ያሰበውን የባህር በርን አስመልክቶ የሚደረገውን ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ አውግዟል፤ ሰላማዊ የውይይት አማራጮች ቅድሚያ እንዲያገኙ አሳስቧል።

ህዝቦች የወንድማማችነት ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩና በጋራ ጥቅሞቻቸው እንዲቆሙ በመጠየቅ በዓለም ዙሪያ ያሉ ምሁራንና የተጽእኖ ፈጣሪዎች ‘ራይዝን’ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል።

በመጨረሻም ተቋሙ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችና ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን በማረጋገጥ በቀጣይነትም የጋራ አጀንዳዎችን ይዞ እንደሚቀርብ የገለፀ ሲሆን፣ ሁሉም እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WT ሚዲያ👏

Ethiopia #SouthEthio