1000057159

By Journalist Natnael Gecho

በህገወጥ የማዕድን ንግድ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ የቀድሞ ኃላፊ አቶ ዳዊት ገበየሁ፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት በ50 ሺህ ብር ዋስ ከእስር መለቀቃቸው ተነግሯል።

ይህ ውሳኔ የመጣው በፌዴራል ደረጃ ሲካሄድ በነበረው ሰፊ ምርመራ እና በርካታ ሚሊዮን ብሮች በተለያዩ ባንኮች መገኘቱ ከተገለጸ በኋላ ነው።

አቶ ዳዊት ገበየሁ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ በህገወጥ መንገድ መርኩሪ የተባለ ማዕድን ለመሸጥ ሲደራደሩ ከአራት ሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህ ክስተት ከዚህ በፊት በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በተዘገበው መሰረት በቦሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ በእጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላም ፍርድ ቤት ቀርበው የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው በእስር ላይ እንደቆዩ ይታወቃል።

ምርመራው እየሰፋ በሄደበት ወቅት አዋሽ ባንክ 87 ሚሊዮን ብር እና ዳሽን ባንክ 112 ሚሊዮን ብር ከተጠርጣሪዎቹ አካውንት ውስጥ ማግኘታቸው ይፋ ሆኖ ነበር።

በአጠቃላይ በስድስት ባንኮች ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገንዘቦች የማጣራት ሂደት እንደቀጠለ ምንጮች ገልጸው ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዚዳንት በጽሁፍ በሰጡት መግለጫ አቶ ዳዊት ገበየሁን ከሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊነት ከስልጣናቸው ማንሳታቸውን ይፋ አድርገው ነበር።

የክልሉ መንግስትም ግለሰቡ “ከኃላፊነታቸው ተነስተው በህግ መጠየቅ አለባቸው” የሚል ጽኑ አቋም መያዙን አረጋግጦ ነበር።

አሁን ላይ አቶ ዳዊት በዋስ የተለቀቁ ቢሆንም የፌዴራል ፖሊስ ምርመራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚጠበቅ ሲሆን ክስተቱ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተጀመረው ምርመራ ወዴት እንደሚያመራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚታይ ይሆናል።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WT ሚዲያ👏

Ethiopia #SouthEthio